የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ

ከ 9 ሰአት በፊት

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአህጉረ አፍሪካ የምታሳድረው ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መጥቷል።

በአህጉሪቱ ላይ ጫና ለማሳደር ገንዘብ ፈሰስ ማድረግን ጨምሮ ሌሎችንም መንገዶች ትጠቀማለች።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ቅድሚያ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲን ታራምዳለች። በተለይም በአፍሪካ ቀንድ እና የሳህል ቀጣና ከሌሎችም አገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነቶችን ፈርማለች።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ ንግድ እና ከመንግሥታት ውጪ የሆኑ ታጣቂዎችን ማሰማራትም ይጠቀሳል።

ባለፉት አሥርታት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ሆናለች።

የምጣኔ ሃብት ፍላጎት አላት። ቀጠናዊ ጫና መፍጠርም ትሻለች።

በነዳጅ ሃብት የተትረፈረፈችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የመካለከያ እና ወታደራዊ ፍላጎም አላት።

በዋናነት የሚጠቀሰው በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ያላት ፍላጎት ነው።

የየመን ሁቲ አማጽያን በቀይ ባሕር ላይ በቅርቡ ጥቃት ሲሰነዝሩ ነበር። በአፍሪካ ቀንድ እና የሳህል ቀጣና ያለው አለመረጋጋት ጨምሯል።

እነዚህ ክስተቶች ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የጀርባ በር ዲፕሎማሲ እንዲሁም ከመንግሥታት ውጪ ካሉ ኃይሎች እና ከታጣቂዎች ትስስር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ናቸው።

ማሳያ ሆኖ የሚጠቀሰው ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ስምምነት መፈረሟ እንዲሁም ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ድጋፍ መስጠቷ ነው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለነገሩ ይፋዊ ዕውቅና ባትሰጥም አልያም ይፋዊ መግለጫ ባይወጣም፣ በአፍሪካ ኃይል የመሆን አዝማሚያዋ በጉልህ ይታያል።

ጉዳዩ አወዛጋቢ ቢሆንም እንኳን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጣልቃ መግባቷ እና የምጣኔ ሃብት ፍላጎቷን ለማስጠበቅ መሞከሯ አልቀረም።

በዚህ አህጉረ አፍሪካ ላይ ጫና በማሳደር ጉዞ እንደ ቻይና ያሉ ዓለም አቀፍ ተገዳዳሪ ኃይሎችም አሉ።

ጫና የማሳደር ፍላጎቱ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ መልሶ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ አለ። አካባቢያዊ-ፖለቲካዊ አንድምታውም ይጠቀሳል።

ከእነዚህ መካከል በአፍሪካ ሊፈጠር የሚችለው አለመረጋጋት አንዱ ነው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከተለያዩ ግጭቶች ጋር በተያያዘ እንደ “ጠላት” መፈረጇም ተያይዞ ይነሳል።

ማሳያ የሚሆነው ከአል-ቃኢዳ ጋር ትስስር ያለው አል-ሻባብ ሲነሳ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ስም መጠቀሱ ነው።

የኤምሬትስ ተቋማት ኣሉባቸው የአፍሪካ አገራት

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ገበያ፣ ኢንቨስትመንት እና ፕሮጀክቶች እንዲጨምሩ አድርጋለች። እአአ ከ2006 ጀምሮ በወደቦች አካባቢ ያለው እንቅስቃሴም ከፍ ብሏል።

ዓለም አቀፍ ኃይሎች አፍሪካ ላይ ጫና ለማሳደር ሩጫ ከመጀመራቸው በፊት ነው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሚናዋ እንዲጎላ ጥረት የጀመረችው።

አፍሪካ በተፈጥሮ ሃብቷ ማለትም በነዳጅ፣ በማዕድን እና በግብርና ውጤት ዕምቅ ጥሪቷ ምክንያት ዓይን በዝቶባታል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለምጣኔ ሃብት ቅድሚያ የሚሰጥ ፖሊሲ ታራምዳለች። ነዳጅ ላይ የተመሠረተውን ምጣኔ ሃብቷን በሌሎች የሃብት ምንጮች ለመደገፍ የምታደርገው ጥረት አንድ አካል ነው።

በአህጉሪቷ ባሉ ግጭቶች ገለልተኛ ለመሆን ትሞክራለች።

ነገር ግን የምጣኔ ሃብት እና የወደብ ተጠቃሚነትን ከግምት በማስገባት ወታደራዊ እንዲሁም የመከላከያ ስምምነት መፈራረሟ አልቀረም።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ ቀንድ እና በሳህል ቀጣና ሽብርተኝነትን፣ እስላማዊ አክራሪነትን እና የባሕር ላይ ዘረፋን በመዋጋት ጣልቃ ትገባለች።

እአአ በ2015 በየመን በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምረት ውስጥ እጇ ገብቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ከውጭ ሆኖ ከመደገፍ ወደቀጥተኛ ወታደራዊ ጫና መጥታለች።

እአአ በ2019 በሳዑዲ ከሚመራው ጥምረት በከፊል ወጥታ “ከሁቲዎች ጋር ተቀናቃኝ የሆኑ ታጣቂዎችን” መደገፍ ጀምራለች።

በሰብአዊ ድጋፍ በኩል አፍሪካ ላይ ጫና ለማሳደር የሚደረገው ሙከራም ተጠቃሽ ነው። በወደቦች ላይ የገንዘብ ፈሰስም ታደርጋለች።

የወደብ መሠረተ ልማትን ለማሻሻል ድጋፍ ሰጥታለች። በዚህም አካባቢያዊ-ፖለቲካዊ ሚናዋ የጎላ ሆኗል። በተያያዥም በአፍሪካ ገበያ እና ግብዓት ያላት ድርሻም ጨምሯል።

ኢንቨስትመንት

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአፍሪካ በኢንቨስትመንት አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ከሦስት እስከ አንደኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ቻይና፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ ናቸው።

ከባሕረ ሰላጤው አገራት የትብብር ማዕከል ውስጥ በአፍሪካ ቀዳሚዋ ኢንቨስት አድራጊ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ናት።

በአፍሪካ ያለውን 1.5 ቢሊዮን የሚሆን ሕዝብ ፍላጎት ለመሸፈን በኃይል አቅርቦት፣ በወደብ ልማት፣ በማዕድን፣ በግብርና፣ በመሠረተ ልማት እና በቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፎች ኢንቨስት ተደርጓል።

እአአ በ2022 የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ አራተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ነበራት። 60 ፕሮጀክቶችም ተዘርግተዋል።

ቀዳሚዎቹ ሦስት አገራት አሜሪካ (93 ፕሮጀክቶች)፣ ፈረንሳይ (78 ፕሮጀክቶች) እና ዩናይትድ ኪንግደም (64 ፕሮጀክቶች) ናቸው።

ኤፍዲአይ ማርኬትስ የተባለው ተቋም ባወጣው መረጃ፣ የአፍሪካን የካፒታል ፍሰት በ49.9 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የሠራተኞች ቅጥርን በ18,600 ሰዎች በቀዳሚነት የምትመራው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ናት።

ሰብል በማልማት፣ በምግብ እና በመጠጥ አቅርቦት፣ በስኳር እና በሌሎችም ጣፋጮች አቅርቦት ኢንቨስትመንቷ ጨምሯል።

የባሕረ ሰላጤው አገራት ካለባቸው የለም መሬት ውስንነት አንጻር የቀጠናውን የምግብ ደኅንነት ለማረጋገጥ አፍሪካን የምግብ ቅርጫት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ማሳያ ነው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የአፍሪካን ንግድ ለመሳብም ትሞክራለች። እአአ በ2022 በዱባይ ዓለም አቀፍ ቻምበር የተመዘገቡት 26,420 የአፍሪካ ተቋማት ናቸው። ቻምበሩ በጆሃንስበርግ፣ በናይሮቢ፣ በማፑቶ እና በአክራ ቢሮዎች አሉት።

ይህም የ6.5 በመቶ ዕድገት እንዲመዘገብ አስችሏል።

የዱባዩ ጀባል አሊ አውሮፕላን ማረፊያ የእስያ እና የአፍሪካ ድልድይ የሆነውም በዚህ መንገድ ነው።

የዲፒ ወርልድ የወደብ እንቅስቃሴ
የምስሉ መግለጫ,የኤምሬትስ ግዙፉ የወደብ አስተዳደር ተቋም ዲፒ ወርልድ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ይንቀሳቀሳል

ወደብ

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ወደብ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ “ወደቦችን በመጠቀም አፍሪካ ላይ ያላትን ጫና እያጠነከረች ነው።”

መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው ዲፒ ወርልድ እና አቡ ዳቢ ያለው አቡ ዳቢ ፖርትስ ግሩፕ ዋነኛ የወደብ ጉዳይ አሳላጭ ናቸው።

ሁለቱም ተቋማት ከልዑላውያን ቤተሰብ ጋር ትስስር እንዳላቸው ይታመናል።

ከወደብ በተጨማሪ ሌሎች መሠረተ ልማቶች እና የምጣኔ ሃብት ቀጠናዎች ላይ ኢንቨስት ታደርጋለች።

ዲፒ ወርልድ እአአ ከ2006 ጀምሮ የወደብ አስተዳደር ኃላፊነት እየወሰደ ነው።

የጂቡቲ ዶራሌህ የኮንቴይነር ተርሚናል አንዱ ነው። እአአ 2018 ላይ ጅቡቲ መልሳ ማስተዳደር ጀምራለች።

የሞዛምቢክ ማፑቶ የኮንቴይነር ተርሚናል ሌላው በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሥር ያለ ነው።

ሌሎች በዲፒ ወርልድ ሥር ያሉ ወደቦች ቀጣዩቹ ናቸው።

አልጀርስ ወደብ እና ደጀን ደጀን ወደብ (አልጄሪያ)፣ ሶካና ወደብ፣ ዳካር ወደብ፣ ኒያንዴ ወደብ (ሴኔጋል)፣ በርበራ ወደብ (ሶማሊላንድ) ቦሳሶ ወደብ (ፑንትላንድ)፣ ኪጋሊ ወደብ (ሩዋንዳ)፣ ሉዋንዳ ወደብ (አንጎላ)፣ ባናና ወደብ (ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ) እና ኮማቲ ወደብ (ደቡብ አፍሪካ)።

የአፍሪካ ወደቦች ኢንቨስትመንትን የተቀላቀለው አቡ ዳቢ ፖርትስ ግሩፕ እአአ በ2016 ማስተዳደር የጀመራቸው ወደቦች ደግሞ ካስማር ወደብ (ጋያና)፣ አቡ አማና ወደብ (ሱዳን)፣ ሳፋጋ ወደብ (ግብፅ) ፖይንቲ ኖይር (ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ) እና ዳሬ ሰላም ፖርት (ታንዛኒያ) ናቸው።

ማዕድን እና ሕገ ወጥ ዝውውር

ሲኤንቢሲ እንዳለው፣ ያለፈው ግንቦት 35 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ወርቅ ከአፍሪካ በሕገ ወጥ መንገድ ወጥቷል።

ከዚህም ከ80 በመቶ እስከ 85 በመቶ የሚሆነው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ደርሶ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ተሠራጭቷል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወርቅ ከሚያስገቡ አገራት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ይህም ከአፍሪካ በምታስገባው ወርቅ ምክንያት ነው። እአአ በ2014 ከተገኘው 22.82 ቢሊዮን ዶላር በላቀ ሁኔታ በአውሮፓውያኑ 2022 ዓመት 57.1 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል።

በዋነኛነት ወርቅ የሚገኘው ከማሊ፣ ከጋና፣ ከዚምባብዌ፣ ከጋያና፣ ከሱዳን እና ከኒጀር ነው። እነዚህም ውጊያ ያለባቸው አገራት ናቸው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በብረት እና በሌሎችም ማዕድናት ላይም ኢንቨስት ታደርጋለች።

ብረት “አነስተኛ ኃይል የሚጠይቅ፣ አነስተኛ የካርበን ልቀት ያለውና አረንጓዴ” የኃይል ምንጭ መሆኑ ይገለጻል። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወደ ታዳሽ ኃይል የምታደርገው ሽግግር እና የመከላከያ ዘርፏ አካልም ነው።

በናይጄሪያ የኒዮቢም ማዕድን፣ በዛምቢያ የኮፐር፣ ቲን፣ ታንታኪየምና ታንግስተን ማዕድን፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቲን፣ ታንታሊየም፣ ታንግስተን እና ወርቅ እንዲሁም በሞሪታንያ ብረት በማውጣት ውስጥ ተሳታፊ ናት።

ወታደራዊ ድጋፍ

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በንግድ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በባሕር በር እና በአካባቢያዊ-ፖለቲካዊ ረገድ ያላት ፍላጎት ከአፍሪካ ቀንድ እና ከሳህል ቀጣና ጋር እንድትቀራረብ ምክንያት ሆኗል።

ከሶማሊላንድ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ፈርማለች። ወታደሮችንም ታሠለጥናለች። በበርበራ ወደብ የምታደርገው እንቅስቃሴ ወደቡን ወደ ቀጠናዊ መዳረሻ ለመቀየር ያለመ ነው።

በሕዝብ ቁጥር ከአህጉሪቱ ሁለተኛ ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋርም ትስስር አላት።

እአአ በ2010 ኤምባሲ ከከፈተች በኋላ በ2013 የዱባይ ቻምበር ቢሮን ከፍታለች።

ይህ ቢሮ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወታደራዊ ትብብርን በማጠንከር የአፍሪካ “በር” ተደርጎ ይወሰዳል።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጎን እንደቆመች እና ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ከጀርባ ሆና እንደገፋፋች ይነገራል።

በከፊል ራስ ገዝ በሆነችው የሶማሊያዋ ፑንትላንድ ግዛት የባሕር ላይ ዘራፊዎችን እና አሸባሪዎችን በመዋጋት ድጋፍ ትሰጣለች።

በሱዳን ጦርነት ውስጥም እጇ አለ። ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሣሪያ ለማስገባት የቫግነር ቅጥረኛ ተዋጊዎችን ተጠቅማለች የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

ሞሪታንያ፣ ማሊ እና ቻድን ጨምሮ ከሳህል አገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነት ፈርማለች።

በእነዚህ ቀጠናዎች ያላት ሚና ከአረብ አገራት አጋሯ ከሆኑት ግብፅ እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር አቀያይሟታል።