በኤርትራውያኑ መካከል በተከሰተው ግጭት የወደሙ ተሽከርካሪዎች
የምስሉ መግለጫ,በኤርትራውያኑ መካከል በተከሰተው ግጭት የወደሙ ተሽከርካሪዎች

ከ 7 ሰአት በፊት

የኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት የካቲት በኤርትራውያን መካከል በተፈጠረው ግጭት ውስጥ ጉልህ ሚና ነበራቸው ባላቸው ተሳታፊዎች ላይ የእስር ቅጣት ወሰነ።

በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች ዘ ሄግ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ ተቃዋሚ ኤርትራውያን ተገኝተው በተሽከርካሪዎች፣ በሌሎች ንብረቶች እና በፖሊስ ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ ነው የግጭቱ አስተባባሪ እና ዋነኛ ተሳታፊዎች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ተይዘው ክስ የተመሰረተባቸው።

ትናንት ሰኞ መስከረም 13/2017 ዓ.ም. ብይን የሰጠው የአገሪቱ ፍርድ ቤት ዋነኛ የግጭቱ መሪ ነው በተባለው የ48 ዓመቱ ዮሐንስ አብረሃ ላይ የአራት ዓመታት እስር ሲፈርድ በሌሎች ላይ በተለያየ መጠን የወራት የእስር ቅጣት አስተላልፏል።

ፍርድ ቤቱ እንዲታሰሩ የወሰነባቸው ኤርትራውያኑ ስደተኞች በግጭቱ እና ግጭቱን ተከትሎ በንብረት ላይ ለተከሰተው ጉዳት ተጠያቂ ናቸው የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ክሱን እንደማይቀበሉት አሳውቀው ነበር።

ፖሊስ በሰጠው ማብራሪያ ሥነ ሥርዓቱ “በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች” አማካይነት የተዘጋጀ እና የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች ደግሞ ዝግጅቱን ለማደናቀፍ ወደ ስፍራው ጥሰው በመግባታቸው ግጭቱ መከሰቱን አመልክቷል።

ፖሊስ በተለያዩ የአሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት ውስጥ ፀረ ኤርትራ መንግሥት ተቃውሞዎችን የሚያካሂደው ብርጌድ ናሃመዱ የተባለው ቡድን መሪ ነው ያለውን ዮሐንስ አብረሃን ጨምሮ በሌሎችም ተከሳሽ ኤርትራውያን ላይ ፍርድ ቤቱ እንዲታሰሩ ወስኗል።

የኔዘርላንድስ መንግሥትን ባስቆጣው እና የአገሪቱን ዜጎች ባስደነገጠው በዚህ የኤርትራውያን ግጭት ውስጥ የተሳተፉ ናቸው ተብለው በፖሊስ ተይዘው የቆዩት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ የተመሰረተው ባለፈው ግንቦት እና ሐምሌ ወር ላይ ነበር።

ዮሐንስ ላይ የአራት ዓመታት አስር የተፈረደ ሲሆን፣ በሌሎቹ ላይ ከአራት አስከ 12 ወራት የሚደርስ እስር ተፈርዶባቸዋል። ነገር ግን እስካሁን በእስር ላይ የቆዩበት ጊዜ ከቅጣቱ ላይ የሚቀነስ እንደሚሆን ተነግሯል።

የተከሳሾቹ ጠበቆች የፍርድ ቤቱን ብይን ተቃወመው ይግባኝ እንደሚጠይቁ አሳውቀዋል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት ካሳ እንዲከፈል የቀረበውን ጥያቄ የተቀበለው ሲሆን፣ የተጠየቀው የካሳ መጠን ከ650,000 አስከ 700,000 ዩሮ የሚገመት ነው።

ግጭቱ በተከሰተበት ጊዜ ኤርትራውያኑ ድንጋይ፣ ርችት እና ሌሎች ነገሮችን በፖሊስ፣ በህክምና እርዳታ እና በእሳት አደጋ ሠራተኞች ላይ ድንጋይ ከመወርወራቸው ባሻገር ተሽከርካሪዎችን በእሳት አቃጥለዋል።

በኔዘርላንድስ ለረዥም ጊዜ ነዋሪ የሆኑት ኤርትራዊው አቶ ሐብቶም ዮሐንስ ባለፈው የካቲት የተካሄደው አደገኛ ግጭት የአገሪቱ ባለሥልጣናት በስደተኞች ላይ አሉታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረጉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኔዘርላንድስ ውስጥ ከ26 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች የሚኖሩ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የስደተኝነት ፈቃድ በአገሪቱ ያገኙ ናቸው። 4 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ የጥገኝነት ፈቃድ ያገኙት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ መሆኑን ‘ደች ኒውስ’ አመልክቷል።