September 24, 2024 – Konjit Sitotaw 

” እኔ ድርድር ያስፈልጋል በሰላም ይፈታ ስል ፤ እሱ ግን ‘ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው ? ‘ ነበር ያለው ” – ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር)

ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ፤ ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ስልጣን ለመጠቅለል በማቀድና የቆየ ቂም ለመወጣት በሚል ከሰሱ።

በደብረጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት መቐለን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ህዝባዊ የተባሉ ስብሰባዎች አካሂዷል።

በእነዚህ መድረኮች የፖርቲው አመራሮች ክፍፍል በስፋት ተነስቷል።

ህወሓትን ለማጥፋት፣ ስልጣን ለመጠቅለል የሚንቀሳቀሱ ተብለው የተገለፁ አመራሮች በስም እየተጠቀሱ ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው ተሰምቷል።

ቅዳሜ በመቐለ በተካሄደና የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮንን (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የፖርቲው አመራሮች እና የተመረጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የታደሙበት መድረክ ነበር።

በዚሁ መድረክ ደብረፅዮን (ዶ/ር) ፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤን፥ ስልጣን ለመጠቅለል በማቀድ፣ የቆየ ቂም በመወጣት እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በማንሳት እንዲሁም ከዚህ በፊት በይፋ ያልተሰሙ መረጃዎች በመግለፅ ሲተቹ ተደምጠዋል።

በንግግራቸው እርሳቸው የሚመሩትን ህወሓት ሰላም የማይፈልግ አድርጎ የማቅረብ የተሳሳተ ፍረጃ ከትግራይ ባለስልጣናት በኩል እየቀረበበት መሆኑ ገልጸው ” ይህ ውሸት ነው ” በማለት አጣጥለዋል።

ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ፤ ” ለምሳሌ በደቡባዊ ዞን በተደረገ መድረክ ጀነራል ጻድቃን እኛ ሰላም እንፈልጋለን፣ እነሱ የሚሹት ጦርነት ነው ሲል ሰምታችሁታል። በጦርነቱ ወቅት ደሴ ተሻግረን ሰሜን ሸዋ ስንጠጋ፥ ድርድር ያስፈልጋል ወይ ሲባል እኔ አዎን ያስፈልጋል ነው ያልኩት። በሰላም ሊፈታ ስለሚገባው። እሱ ግን ከማን ጋር ነው የምንደራደረው፣ ውጊያው አልቋል ሲል የነበረ ነው። አሁን ግን እኔ ሰላም ነኝ እነሱ ጦርነት ናቸው የሚፈልጉ ማለት ጀመረ ” ብለዋል።