የእስራል አየር ኃይል አውሮፕላን በሰሜናዊ እስራኤል ሲበር

ከ 2 ሰአት በፊት

የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በአገራቸው እየተፈጸመ ያለውን የእስራኤል የአየር ጥቃት “እልቂት” ሲሉ ገለጹ። እስራኤል ለሁለት ቀናት በታጣቂው የሄዝቦላህ ቡድን ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሆስፒታሎች ተጎጂዎችን ለማስተናገድ እየታገሉ ነው ተብሏል።

ሰኞ ዕለት በጥቃቱ ከተገደሉት 550 ሰዎች መካከል ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ሲቪሎች መሆናቸው “ግልጽ” ነው ሲሉ ዶክተር ፊራስ አቢያድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስራኤል በበኩሏ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ዒላማዎችን መምታቷን ገልጻ፤ ቡድኑ በመኖሪያ አካባቢዎች የጦር መሳሪያ ደብቋል ስትል ከሳለች።

የእስራኤል ጦር ማክሰኞ ጥቃቱን በመቀጠል የሄዝቦላህ የሮኬት ቡድን መሪን ገድሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ታጣቂ ቡድኑ ሊባኖስን ወደ “ገደል” እያመራት ነው ብለዋል።

ሄዝቦላህ ወደ ሰሜን እስራኤል ከ300 በላይ ሮኬቶችን በመተኮስ በሰጠው ምላሽ 6 ሰዎች ቆስለዋል ሲል ጦሩ አስታውቋል።

ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን ለማቀዝቀዝ ፍላጎት ያላቸው ባይመስሉም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ግጭት “ለማንም አይጠቅምም” እና “ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ማምጣት አሁንም ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው “ሊባኖስ ሌላኛዋን ጋዛ ስትሆን ዓለም ሊቀበለው አይችልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በጋዛ ጦርነት ምክንያት በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል በተቀሰቀሰው ድንበር ተሻጋሪ ጦርነት አብዛኛዎቹ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሁለቱም አገራት የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

ሄዝቦላህ ሃማስን በመደገፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እና በጋዛ የተኩስ አቁም እስካልመጣ ድረስ ወደ ኋላ እንደማይልም ተናግሯል። ሁለቱ ቡድኖች በኢራን የሚደገፉ ሲሆን በእስራኤል፣ በእንግሊዝ እና በሌሎች አገራት ደግሞ በአሸባሪነት ተፈርጀዋል።

ሰኞ ዕለት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ እና በምስራቃዊው የቤአካ ሸለቆ የፈጸመችው የአየር ድብደባ በ2006 ሄዝቦላህ እና እስራኤል ለመጨረሻ ገዜ ወደ ጦርነት ከገቡ ወዲህ የአገሪቱ እጅግ አስከፊው ቀን ሆኖ ተመዝግቧል።

አቢያድ ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከተገደሉት 558 ሰዎች መካከል 50 ህጻናት፣ 94 ሴቶች እና በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ከ50 በላይ ሆስፒታሎች አንድ ሺህ 835 ቁስለኞችን ተቀብለው በማከም ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።

በኋላ ላይ ሚንስትሩ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የተከሰተውን ነገር “እልቂት” ሲሉ ገልጸውታል።

“ወደ ድንገተኛ ክፍል የመጡትን ሰዎች ብትመለከቷቸው ሲቪሎች መሆናቸው ግልጽ ነው። እስራኤላውያን እንደሚሉት ተዋጊዎች አይደሉም” ብለዋል።

“የእኛ አምቡላንሶች ወደ ሆስፒታሎች ስለመጧቸው ስለ ጥቃቱ ሰለባዎች እናውቃለን። መደበኛ ሥራቸውን ሲከውኑ የነበሩ ሲቪሎች ነበሩ” ሲሉ ተናግረዋል።

አቢያድ አሁን ያለውን ሁኔታ እአአ በ2006 በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ከነበረው ጦርነት ጋር በማነጻጸር “በተለይም ሲቪሎች ኢላማ የሚደረጉበት መንገድ ካየነው የበለጠ ጨካኔ የተሞላበት ጦርነት እየተመለከትን ነው” ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ሰኞ ዕለት በተደረጉ ጥቃቶች የሞቱት ሰዎች ቁጥር አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግን የጣሱ ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል።

የእስራኤል ጦር የሊባኖስ ነዋሪዎች ሄዝቦላህ የጦር መሳሪያ ካከማቸባቸው ህንፃዎች አጠገብ ካሉ አካባቢዎችን ለቀው እንዲወጡ የላከውን የድምጽ እና የጽሑፍ መልዕክት በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ቃል አቀባይዋ ራቪና ሻምዳሳኒ “አካባቢዎቹን ማጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆን በሚገባ እያወቁ ሲቪሎች እንዲሸሹ መንገር ምንም አይጠቅምም” ሲሉ መልሰዋል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስራኤል ጥቃት ለማምለጥ ወደ ሰሜን አቅጣጫ መሸሽ መጀመራቸውን ተከትሎ በደቡባዊ ሊባኖስ ያሉ መንገዶች ለሁለተኛ ቀን ተጨናንቀዋል። አንድ ሰዓት ብቻ ይወስዱ የነበሩ ጉዞዎች 12 ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ እየጠየቁ ነው።

ቤይሩት ውስጥ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ ቢቢሲ ያገኛቸው የ65 ዓመቷ መርየም፤ ከ12 ዘመዶቿ ጋር በአንድ ትንሽ መኪና ሌሊቱን ሙሉ መጓዛቸውን ተናግረዋል።

“ተሰባስበን ወጣን። ቤታችንን መልቀቅ አልፈለግንም፣ ምክንያቱም ቤትን መልቀቅ ከባድ ነው። ከልጆቻችን ጋር እዚህ የደረስነው ለሊት አስር ሰዓት ነው። የሸሸነው በልጆቻችን ምክንያት ነው” ብለዋል።

የሄዝቦላህ ሮኬቶች በንብረት እና በአካል ላይ ጉዳት አድርሰዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የስለላ ጣቢያን በጎበኙበት ወቅት፣ እስራኤል የተፈናቀሉትን ዜጎቿን ሰሜናዊ ድንበር አካባቢ ወደሚገኙ ቤታቸው የመመለስ የጦርነት ግቧን እስክታሳካ ድረስ “ሄዝቦላህን መምታቷን ትቀጥላለች” ብለዋል።

በተጨማሪም የሊባኖስ ህዝብ “ጦርነቱ ከእናንተ ጋር አይደለም” በማለት አስጠንቅቀው፤ የሄዝቦላህ መሪ የሆኑት ሀሰን ናስራላህ ደግሞ “ወደ ጥልቁ ገደል እየመራችሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ሳሎን ውስጥ ሚሳኤል እና ኩሽና ውስጥ ሮኬት ካለባቸውን ቤቶች ለቃችሁ እንድትወጡ ትላንት ተናግሬ ነበር። ሳሎን ውስጥ ሚሳኤል፣ ኩሽና ውስጥ ሮኬት ያለው ቤት ከእንግዲህ በኋላ አይኖረውም” ብለዋል።

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ በምሽት መግለጫቸው እንደተናገሩት ሄዝቦላህ ደቡባዊ ሊባኖስን እና የቤአካ ሸለቆን ወደ “ጦርነት ቀጠና” ቀይሯል። በዚህም የእስራኤል አየር ኃይል ማክሰኞ ድረስ ዒላማዎችን መምምታቱን ቀጥሏል።

ሃጋሪ አክለውም የሄዝቦላ ሚሳኤል እና ሮኬት ክፍል ኃላፊ ኢብራሂም ኩባይሲ ማክሰኞ ከሰአት በኋላ በቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች በደረሰ የአየር ጥቃት ተገድለዋል ብለዋል። አብረዋቸው ከነበሩት መካከል ቢያንስ ሁለት ሌሎች አዛዦች መገደላቸውንም አስታውቀዋል።

ኩባይሲ “የሚሳኤል ጥቃቶችን በመሰንዘር ቁልፍ ሰው ነበር። በእስራኤል ግዛት ላይ ለሚደርሱ ተከታታይ ጥቃቶችም ተጠያቂ ነበር” ሲሉ አክለዋል።

ኩባይሲ በጥቃቱ “መሰዋቱን” ሄዝቦላህ በቴሌግራም ገጹ አረጋግጧል።

የሊባኖስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ደግሞ “ጠላት እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት” በቤይሩት ጎቤይሪ መንደር የሚገኙ ሁለት ፎቆችን በከፊል ሲወድሙ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል 15 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

ሄዝቦላህ ተዋጊዎቹ ከ12 በላይ በሚሆኑ የእስራኤል ከተሞች፣ ወታደራዊ ካምፖች እና የፈንጂ ማምረቻዎች ላይ ሮኬቶች መተኮሳቸውን ገልጿል። የእስራኤል ጦር የሳምሶን ክፍልን ለመምታት አዲስ ዓይነት ሮኬት ጥቅም ላይ ማዋሉንም ገልጿል።

በሰሜናዊ እስራኤል ቀኑን ሙሉ የማስጠንቀቂያ ደወል መሰማቱ የቀጠለ ሲሆን የእስራኤል የሮኬት መከላከያ የሆነው የአይረን ዶም መከላከያ ስርዓት ወደ ሰማይ ሲወነጨፍ ታይቷል።

300 ከሚሆኑ ሮኬቶች ጥቂቶቹ ወድቀው በስድስት ሰላማዊ ዜጎች እና ወታደሮች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን እና አብዛኛዎቹ ጉዳቶች ቀላል መሆናቸውን ሃጋሪ ገልጸዋል።