ዲዲ

ከ 2 ሰአት በፊት

ሴቶችን ለወሲብ ንግድ በማዘዋወር ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው አሜሪካዊው ራፐር ዲዲ (ሾን ዲዲ ኮምብስ) የፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት 11ኛ ክስ ቀረበበት።

11ኛዋ ከሳሽ ታሊያ ግሬቭስ ስትሆን እአአ በ2001 ዲዲ እና የግል ጠባቂው አደንዛዥ መድኃኒት ሰጥተው እንደደፈሯትና ድርጊቱንም በቪድዮ እንደቀረፁት ተናግራለች።

ዲዲ ላይ የቀረቡት ክሶች ከ1990ዎቹ የጀመሩ ናቸው።

ራፐሩ ወንጀሎቹን አልፈፀምኩም ሲል አስተባብሏል።

ዲዲ የተከሰሰው በምንድን ነው?

የ54 ዓመቱ ድምጻዊ የታሠረው ባለፈው ሳምንት ኒው ዮርክ ውስጥ ነበር።

በማጭበርበር፣ በመመሣጠር፣ በአስገዳጅ የወሲብ ንግድ እንዲሁም ለወሲብ ንግድ ሰዎችን በማዘዋወር ተከሷል።

የፌደራል መንግሥት ዲዲን የከሰሰው “የወንጀል ሰንሰለት በመዘርጋት” ሲሆን፣ “ሰዎችን በዝብዟል፣ አስፈራርቷል፣ በአካባቢው ያሉ ሴቶችን በማስገደድ ወሲብ ፈጽሟል፣ ድርጊቱን እንዲሸፍኑም አስገድዷል” ተብሏል።

አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀም፣ ሰዎችን በማስገደድ እንዲሁም ዝናውን በመጠቀም “ሴቶችን በማማለልና በመበዝበዝ” ተከሷል።

በሎስ አንጀለስ፣ ማያሚ ያለው ቤቱ ላይ ፍተሻ ሲደረግ መሣሪያ፣ ጥይት እንዲሁም በወሲብ ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል 1,000 ጠርሙስ ‘ሉብሪከንት’ ተገኝቷል።

ለዲዲ ይሠሩ የነበሩና አሁን ክሱ ውስጥ የተካተቱ ምስክሮች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ተጨማሪ ክሶች ሊከፈቱ እንደሚችሉም ይጠበቃል።

ድምጻዊና ፕሮዲውሰሩ ዲዲ ጥፋተኛ እንዳልሆነ ሲገልጽ ጠበቃው ደግሞ “ምንም ክስ የማያስፈራው ጠንካራ ሰው” ብለውታል።

ብሩክሊን በሚገኘው አደገኛ ወንጀለኞች በሚታሰሩበት ሜትሮፖሊታንት ዲቴንሽን ሴንተር በቁጥጥር ሥር ይገኛል።

እስር ቤቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ “አሰቃቂ” ስለሆነ በዋስ እንዲወጣ ጠበቆቹ ቢሞክሩም ፍርድ ቤት ከልክሏል።

ጥፋተኛ ከተባለ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስር ይጠብቀዋል።

የቀድሞ ፍቅረኛው ካሲ ቬንቱራ ለዓመታት “በብዝበዛ፣ በጥቃትና የወሲብ ንግድ” ውስጥ እንዳቆያት ገልጻ ከከሰችው በኋላ ብዙ ክሶች ቀርበውበታል።

በፍርድ ቤት ጉዳዩ እልባት ቢያገኝም ሲኤንኤን በ2016 ካሲ ላይ ዲዲ ድብደባ ሲፈጽም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል አውጥቷል።

ዲዲ “ድርጊቴ አስቀያሚ ነበር” ሲል ድብደባ መፈጸሙን አምኗል።

ዲዲን የከሰሱት እነማን ናቸው?

በራፐሩ ላይ የቀረቡ ሌሎች ክሶች ቀጣዮቹ ናቸው።

ጆይ ዲከርሰን-ኒል- ካሲ ካበረታታቻት በኋላ ጆይ ክስ ከፍታለች። በ1991 የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለች ዲዲ አደንዛዥ ዕፅ ሰጥቶ እንደደፈራት ተናግራለች። ድርጊቱን በቪድዮ ቀርጾ ለበቀል እንዳዋለውም ገልጻለች። ዲዲ ግን ክሱ ‘ገንዘብ ለማግኘት ያለመ ነው’ ብሏል።

ሊዛ ጋርድነር- ዲዲ ከድምጻዊ ኮነር አሮን ሃል ጋር በመሆን በመጠጥ ገፋፍተው ወሲብ እንድትፈጽም እንዳስገደዷት ተናግራለች። በወቅቱ 16 ዓመቷ ነበር። በነጋታው ዲዲ ራሷን እስክትስት ድረስ እንዳነቃት ገልጻለች። የዲዲ ጠበቃ ክሱን አጣጥለዋል።

ጄን ዶው- በዚህ መጠሪያ ክሷን ያሰማችው ሴት የ17 ዓመት ታዳጊ ሳለች የቀድሞው የባድ ቦይ ሪከርድስ ኃላፊ ሀርቪ ፒሬ እና ሌላም ሰው በቡድን እንደፈሯት ተናግራለች። ዲዲ ግን ክሱ ገንዘብ ለማግኘት ያለመ ነው ብሏል።

ሮድኒ ‘ሊል ሮድ’ ጆንስ- ፕሮዲውሰርና ቪድዮግራፈሩ ሮድኒ፣ የዲዲን አልበም የሠራ ባለሙያ ነው። ዲዲ ሕገ ወጥ ሰንሰለት በመዘርጋት አደንዛዥ ዕፅ በማምረት፣ በግዳጅ የወሲብ ንግድና፣ የወሲብ ቪድዮ ምርት እንደተሰማራ ተናግሯል። ተዋናዩ ኩባ ጉዲንግ ጁንየር ያለ ፈቃዱ እንደነካውም ገልጿል።

ግሬስ ኦማርካጋ- በዲዲ ቤተሰብ ስም ባለ መርከብ ላይ ሠርታለች። ዲዲ እና ልጁ ክርስቲያን ‘ኪንግ’ ኮምብስ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሱባትና በመርከቡ ላይ ታዋቂ ሰዎች የተጋበዙበት የወሲብ ንግድ እንደተካሄደ ገልጻለች።

ክሪስተል ሜከኒ- 22 ዓመቷ ሳለ በ2023 ከፋሽን ሳምንት በኋላ አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀም ዲዲ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባትና የሞዴልነት ሥራዋን እንዳትቀጥል ጫና እንዳሳደረ ተናግራለች።

ኤፕሪል ላምፕሮስ- በ1994 ዲዲን ከተዋወቀች በኋላ በ2000 መባቻ “አራት አስፈሪ የወሲብ ድርጊቶች” እንደተፈጸመባት ተናግራለች።

አንድርያ ኢንግሊሽ- የወሲብ ፊልም ሠሪዋ እንዳለችው ዲዲ በኒው ዮርክና ማያሚ ፓርቲዎች ላይ “ለወሲባዊና የንግድ ጥቅም” አውሏታል።

ዳውን ሪቻርድስ- ዲዲ የሰበሰባቸው ሰዎች ጥቃት ሲፈጽሙ ያየት ሲሆን ዲዲ የቀድሞ ፍቅረኛው ካሲ ላይ ያደረሰውን ብዝበዛ እንዳትናገር እንዳስፈራራት ተናግራለች።

ታሊያ ግሬቭስ- ዲዲ እና ጠባቂው ጆሴፍ ሸርማን አደንዛዥ ዕፅ በመስጠት እንደደፈሯትና ድርጊቱን በቪድዮ እንደቀረጹ ተናግራለች።