ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች እና የሞቃዲሾ ወደብ ከጀርባቸቸው
የምስሉ መግለጫ,የጦር ማሳሪያው የገባበት የሞቃዲሾ ወደብ እንዲሁም የሶማሊያ እና የግብፅ ፕሬዝዳንቶች

ከ 3 ሰአት በፊት

ካለፈው እሁድ መስከረም 12/2017 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ የሞቃዲሾ ወደብ ዝግ ሆኖ መቆየቱን የወደቡ ሠራተኞች ይናገራሉ።

ነገር ግን የግብፅ የጭነት መርከብ ወደ ወደቡ ደርሳ ጭነቷን እስክታራግፍ ድረስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ፈጽሞ አላወቁም ነበር።

በወደቡ የተራገፉት የጦር መሳሪያዎች በከባድ መኪና ተጭነው እና እየተጎተቱ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ሲተላለፉ ነበር፣ የወደቡ መደበኛ እንቅስቃሴ የተስተጓጎለበት ምክንያት ለሞቃዲሾ ነዋሪዎች ግልጽ የሆነው።

ከዚህም አልፎ በርካታ ነዋሪዎች ወደ አገሪቱ የገቡትን የጦር ማሳሪያዎች የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ቀርጸው በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ አጋርተዋል።

ይህም ጉዳይ ከአገሬው አልፎ በአካባቢው አገራት ብሎም በዓለም መገናኛ ብዙኃን መነጋገርያ ሊሆን በቅቷል።

በሞቃዲሾ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢም ከባድ የጦር ማሳሪያዎቹ በሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ ሲጓጓዙ ከተመለከቱት ሰዎች መካከል አንዱ ነው።

በከባድ ወታደራዊ መኪኖች ላይ የተጫኑ እሸጎች እና በመኪና የሚጎተቱ ከባድ መሳሪያዎች በወቅቱ ጎዳና ላይ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በስፋት የተመለከቱት ነው።

የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች መርከቧ ጭነቷን የምታራግፍበት ወደብ እና በዙሪያው የሚገኙ መንገዶችን ዘግተው የነበረ ሲሆን፣ መሳሪያዎቹን የጫኑ መኪኖች ወደ መከላከያ ሚኒስቴር እና ወታደራዊ ካምፖች ሲያመሩ እሁድ እና ሰኞ ዕለት መንገዶቹ ተዘግተው መቆየታቸውን ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሰኞ ከሰዓት በኋላም የጦር ማሳሪያዎቹ ምንጭ በቅርቡ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት የደረሰችው ግብፅ መሆኗን እንዲሁም የመሳሪያዎቹ ዓይነት የተመለከቱ መረጃዎች በስፋት መውጣት ጀመሩ።

ይህም መጀመሪያ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ከዚያም ኢትዮጵያ በግብፅ ለሶማሊያ መንግሥት የተሰጠው የጦር ማሳሪያ ወትሮም ባለመረጋጋት ውስጥ የሚገኘውን የአፍሪካ ቀንድ ቀውስ የሚያባብስ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ስለጦር መሳርያዎቹ የሚታወቀው

ከባድ የጦር መሳሪዎችን የጫነችው የግብፅ መርከብ ሞቃዲሾ ወደብ ደርሳ ጭነቷን ማራገፏ ከተሰማ እና በጎዳናዎች ላይ ከታየ በኋላ በቀጠናው ያለው ውጥረት ዳግም መነጋገርያ ሆኗል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሶማሊያ የደኅንነት ባለሥልጣናት በእርግጥም ከግብፅ የተላኩት ጦር መሳሪያዎች በሞቃዲሾ ወደብ ተራግፈው ወደ መዳረሻቸው በተሽከርካሪ መወሰዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር ሞሐመድ ኑር የጦር መሳሪያዎቹን ድጋፍ ሳይጠቅሱ በደፈናው ግብፅ ለአገራቸው እያደረገች ስላለው ድጋፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አመስግነዋል።

ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ግብፅ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ግብፅ ለሞቃዲሾ ወታደራዊ ድጋፍ ስታደርግ በአጭር ጊዜ የአሁኑ ሁለተኛው እና ከፍተኛው ነው።

ግብፅ እሁድ ዕለት ለሶማሊያ የቀረበችው ወታደራዊ ድጋፍ ፀረ አውሮፕላን እና ፀረ ታንክ ከባድ የጦር መሳሪያዎች እንዳሉበት ሮይተርስ የዜና ወኪል የወደቡን ባለሥልጣናት እና የአገሪቱን የደኅንነት ኃላፊዎች ጠቅሶ ዘግቧል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሶማሊያ አንድ ባለሥልጣን ደግሞ የጦር መሳሪያዎቹ ፀረ አውሮፕላን ሚሳኤሎች፣ መድፎች እና ሌሎች አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች መሆናቸውን አረጋግጠው፤ በቀጣይም ሶማሊያ ከግብፅ ታንኮችን እንደምትጠብቅ አመልከተዋል።

በሶማሊያ የደኅንነት እና ወታደራዊ ጉዳይ ላይ ትንታኔ የሚሰጡት ኮሎኔል አብዱላሂ አሊ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ሞቃዲሾ ውስጥ የታዩት “በከባድ መኪኖች ላይ የተጫኑት ከባድ ጦር መሳርያዎች የመከላከያ ኃይሉ ሊጠቀምባቸው የሚችላቸው ናቸው” ብለዋል።

ወታደራዊ መኮንኑ ጨምረውም የሶማሊያ መንግሥት ጦር ምንም እንኳ ከዚህ ቀደምም እንዲህ ያሉት የጦር መሳሪያዎች የነበሩት ቢሆንም፣ አሁን ግን የበለጠ ወታደራዊ አቅሙን እና አቋሙን ያጠናክሩለታል በማለት ተጨማሪ መሆኑን አመልክተዋል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ግብፅ ለሶማሊያ የሰጠቻቸው የከባድ ጦር መሳሪያ አቅርቦቶች መጀመሪያ በሲ-130 ወታደራዊ የጭነት አውሮፕላኖች ከገባው ጋር ሲነጻጸር በዓይነት እና ብዛት የተለየ እና ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል።

የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ዕለት “የሶማሊያን ጦር አቅም ለመደገፍ እና ለማጠናከር ያለመ የግብፅ ወታደራዊ ድጋፍን የያዘ ጭነት ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ደርሷል” በማለት የጦር ማሰሪያዎቹን ወደ ሶማሊያ መላካቸውን አረጋግጧል።

ሚኒስቴሩ ይህ የግብጽ ድጋፍ ሶማሊያ ደኅንነቷን እና መረጋጋቷን ለማረጋገጥ፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንዲሁም ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ያለመ ነው ብሏል።

ምንም እንኳን አሁን ጉዳዩ ይፋ የወጣ ቢሆንም የሶማሊያ መንግሥት ግን እስካሁን በይፋ ከግብፅ በኩል የተሰጠውን የወታደራዊ ከባድ የጦር ማሳሪያዎችን መረከቡን የሚያረጋግጥ መግለጫ አልሰጠም።

የተቀሰቀሰው ቁጣ

ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከሶማሊያ ራሷን ለይታ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ግብፅ ለሶማሊያ ያስታጠቀቻቸውን ከባድ የጦር ማሳሪያዎችን በተመለከተ ቁጣዋን እና ተቃውሞዋን በመግለጽ ቀዳሚዋ ናት። ሶማሊላንድ የጦር መሳሪያ አቅርቦቱ በቀጣናው አሳሳቢ ሁኔታ ይፈጥራል ብላለች።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ከግብፅ ወደ ሞቃዲሾ የገቡት ከባድ የጦር መሳሪያዎች ውስብስብ የደኅንነት ፈተና ያለበትን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ጥልቅ ስጋት እንደተፈጠረ ገልጿል።

አክሎም የሞቃዲሾ አስተዳደር እነዚህን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ከባድ የጦር መሳሪያዎች በተገቢው ሁኔታ የመያዝ አቅም ስለሌለው አልሻባብን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አንጃዎች እጅ በመግባት አሳሳቢ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል በማለት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

ኢትዮጵያም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በኩል በስም ያልጠቀሱትን “የውጭ ኃይሎች” ወደ ሶማሊያ የሚያስገቧቸው የጦር መሳሪያዎች “በአሸባሪዎች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ” የሚል ስጋቷን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ ኒው ዮርክ ላይ ገልጸለች።

አምባሳደሩ ይህንን ያሉት የግብፅ የጭነት መርከብ ፀረ አውሮፕላን ሚሳኤሎች፣ መድፎች እና ሌሎች አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች ሞቃዲሾ ውስጥ ባራገፈች ማግስት ሲሆን “በውጭ ኃይሎች [ለሶማሊያ] የሚደረግ የመሳሪያ አቅርቦት የተዳከመውን የፀጥታ ሁኔታ ይበልጥ እንደሚያባብስ እና በአሸባሪዎች እጅ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል” ተናግረዋል።

ሶማሊያ – የኢትዮጵያ እና የግብፅ የፍጥጫ መድረክ

ኢትዮጵያ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከዳር ያደረሰችውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን የውሃ መጠን ይቀንስብኛል የምትለው ግብፅ፤ ከኢትዮጵያ ለዓመታት በግድቡ የውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ዙሪያ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረግ ብትጥርም ሳይሳካላት ቀርቷል።

የግድቡ ግንባታ እና የውሃ ሙሌት ከዓመት ዓመት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ውጥረት እያባባሰው ባለበት ጊዜ ነበር ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ የፈረመችው።

ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመስጠት፣ በምላሹ ደግሞ ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን እንደ አገር እውቅና ለመስጠት ነው የተስማሙት።

ይህ ደግሞ ከሶማሊያ በኩል ያገኘው ምላሽ ቁጣን እና ተቃውሞ የተቀላቀለበት ነው።

ስምምነቱ ከአንድ ግዛቷ ጋር የተደረገ በመሆኑ ሉዓላዊነቷን የሚጥስ ነው በማለት ውድቅ እንዲሆን ብትወተውትም ከኢትዮጵያ በኩል ዝምታን እንዲሁም ከሶማሊላንድ በኩል ደግሞ ሳይቀለበስ ተግባራዊ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ውዝግብ በኢትዮጵያ ላይ ጫናን ለመፍጠር እየተጠቀመችበት ያለችው ግብፅ ወዲያው ነበር ምላሽ የሰጠችው።

ግብፅ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ከመደገፏ በተጨማሪ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምትሰጥ በመግለጽ ወደ ፍጥጫው ሰተት ብላ ገብታለች።

በዚህ ያላበቃች ግብፅ ነሐሴ ወር ላይ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነትን ተፈራርማ፣ ከሳምንታት በኋላ በሁለት ወታደራዊ የጭነት አውሮፕላኖች ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ወደ ሞቃዲሾ አስገብታለች።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ተቃውሟቸውን በይፋ አሰምተዋል።

ኢትዮጵያ የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ መታየታቸውን ተከትሎ “የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እንርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት” ስታስታውቅ፣ የሶማሊላንድ መንግሥትም በበኩሉ በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ ግብፃውያንን አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አዟል።