አንዲት ሕፃን ልጅ ለማንበብ ስትሞክር

ከ 2 ሰአት በፊት

በዓለማችን ከሶስት ሕፃናት አንዱ ቅርባቸው ያለ ነገር እንጂ አርቀው ማየት አንደማይችሉ አንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሠራ ጥናት አመለከተ።

አጥኚዎቹ እንደሚሉት የኮቪድ ወረርሽኝ በሕፃናት ዕይታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ ያለፈ ሲሆን ሕፃናት ወጣ ብለው ከመጫወት ይልቅ ስክሪን ላይ ብዙ ሰዓት ማሳለፋቸው ጎድቷቸዋል።

ራቅ ያለ የማየት ችግር አሊያም በሳይንሳዊ አጠራሩ ማዮፒያ ዓለማችንን የሚያሰጋት ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2050 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ይህ ችግር ሊከሰትባቸው ይችላል ሲል ጥናቱ ያስጠነቅቃል።

በጃፓን ካሉ ሕፃናት መካከል 85 በመቶው፣ በደቡብ ኮሪያ 73 በመቶው እንዲሁም በቻይና እና ሩሲያ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ማዮፒያ እንዳለባቸው ጥናቱ ይጠቁማል።

ፓራጓይ እና ኡጋንድ 1 በመቶ ብቻ ሕፃናት የማዮፒያ ተጠቂ ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አየርላንድ እና ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ 15 በመቶ ላይ ተቀምጠዋል።

ብሪቲሽ ጆርናል ኦፍ ኦፕታልሞሎጂ የተሰኘው የሕክምና ሕትመት ላይ የወጣው ሀተታ ከስድስቱም አህጉራት ከተውጣጡ 50 ሀገራት ያሉ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን በጥናቱ ዳሷል።

ከአውሮፓውያኑ 1990 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ማዮፒያ በሶስት እጥፍ መጨመሩን ቁጥሮች ያሳዩ ሲሆን ይህ የእይታ እክል ባለፉት 33 ዓመታት 36 በመቶ ጨምሯል።

አጥኚዎቹ እንደሚሉት ይህ ቁጥር መጨመሩ በግልፅ መታየት የጀመረው ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ነው።

ማዮፒያ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ሕፃናት ትምህርት መቅሰም ሲጀምሩ ሲሆን በተለይ የዓይን ዕድገት በሚያቆምበት 20ኛው ዕድሜ አካባቢ መባባስ ሊያሳይ ይችላል።

በምስራቅ እስያ ያሉ በርካታ ሰዎች በማዮፒያ ተጠቂ ናቸው። ለዚህ አንደኛው ምክንያቱ በዘረ-መል የሚተላለፍ የሚችል በመሆኑ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ስለሚወስዱት ነው።

እንደ ሲንጋፖር እና ሆንግ ኮንግ ባሉ ሀገራት ደግሞ ሕፃናት ገና በልጅነታቸው መፃሕፍት አሊያም ስክሪን ላይ ስለሚያፈጡ የዓይናቸው ጡንቻ መጨማደዱ ለማዮፒያ ሊያጋልጥ እንደሚችል ጥናቱ ያመላክታል።

ሕፃናት ከስድስት እስከ ስምንት ዓመት ዕድሜያቸው ትምህርት በሚጀምሩበት አህገሩ አፍሪካ ማዮፒያ ከእስያ ሲነፃፀር ሰባት እጥፍ ዝቅ ያለ ነው።

ጥናቱ እንደሚገምተው በአውሮፓውያኑ 2050 በዓለማችን ከሚኖሩ ታዳጊዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ማዮፒያ ሊኖርባቸው ይችላል።

ታዳጊ እና ወጣት ሴቶች ከታዳጊ እና ወጣት ወንዶች የበለጠ ለማዮፒያ ሊጋለጡ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ወደ ውጭ ወጥቶ የመጫወት ዕድላቸው የጠበበ ነው ይላል ጥናቱ።

ምንም እንኳ በ2050 እስያ በማዮፒያ ከሌሎች አህጉራት በ69 በመቶ ልትበልጥ ብትችልም እያደጉ ናቸው የሚባሉ አህጉራትም 40 በመቶ ሊደርሱ ይችላሉ ይላል።

አንዲት መነፅር ያደረገች ሕፃን ስክሪን ተጠግታ ስትመለከት

ልጄን እንዴት መጠበቅ እችላለሁ?

ሕፃናት በተለይ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ7-9 በሚደርስበት ወቅት በየቀኑ ቢያንስ ለሁለት ሰዓታት ወጣ ብለው ቢጫወቱ በማዮፒያ የመያዝ ዕድላቸው ይጠባል ይላሉ የዩኬ ባለሙያዎች።

ነገር ግን ልዩነት የሚፈጥረው የተፈጥሮ የፀሐይ ብርሀን ይሁን አሊያም ሕፃናት ራቅ ያለ ቁስ ለማየት የሚጠቀሙት የትኩረት መጠን ገና አልታወቀም።

“ያም ሆነ ይህ ሕፃናት ወጣ ብለው መጫወታቸው ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው” ይላሉ የዩኬ ኦፕቶሜትሪስትስ ኮሌጅ ክሊኒካል አማካሪ ዳንኤል ሀርዲማን ማካርትኒ።

አክለው ምንም እንኳ ቀድመው ቢመረመሩም ዕድሜያቸው ከ7-10 ያሉ ሕፃናት የዓይን ምርመራ ማድረጋቸው ተገቢ ነው ሲሉ ይመክራሉ።

ቤተሰብ መርሳት የሌለበት ነገር ማዮፒያ የሚተላለፍ መሆኑን ነው። እናት ወይም አባት ማዮፒያ ካለባቸው ሕፃናት የማዮፒያ ተጠቂ የመሆን ዕድላቸው በሶስት እጥፍ ይጨምራል።

ምንም እንኳ ማዮፒያ ሕክምና ባይኖረውም በመነፅር አሊያም በኮታክት ሌንስ ሊስተካከል ይችላል። ማዮፒያ ያለባቸው ሰዎችን ዕይታ የሚያስተካክል ልዩ ሌንስ ቢኖርም ዋጋው ከፍተኛ ነው።

ራቅ ያሉ ፅሑፎችን ለማንበበር መቸገር ለምሳሌ መማሪያ ክፍል ውስጥ ሰሌዳ ለማየት መቸገር፤ የኮምፒውተር ስክሪን አሊያም ተንቀሳቃሽ ስልክ በጣም ቀረብ አድርጎ መመልከት፤ ራስ ምታት እና ዓይንን ቶሎ ቶሎ ማሸት የማዮፒያ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።