የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፥ በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራውን የህወሓት ቡድን አስጠነቀቁ።
ፕሬዜዳንቱ በማስጠንቀቂያቸው ” ቡድን ” ሲሉ የጠሩት ሃይል የወረዳና የከተማ የህዝብ ምክር ቤቶች ለመረበሽ እየሄደበት ያለው ርቀትና በማድረግ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ማቆም አለበት ብለዋል።
መስከረም 14/2017 ዓ.ም በፕሬዜዳንቱ ፊርማ ተፈርሞ ለሁሉም የወረዳና የከተማ ም/ቤቶች የተፃፈው የማስጠንቀቅያ ደብዳቤ ” የህዝብ ምክር ቤቶች የትግራይ ጊዚያዊ መንግስትና የህዝቡ አካል እንጂ የህወሓት መዋቅር አለመሆናቸው አውቆ ‘ ቡድኑ ‘ የራሱ መሳሪያ ለማድረግ እያካሄደ ያለውን መሯሯጥና ውንብድና ማቆም አለበት ” ይላል።
ስለሆነም ምክር ቤቶቹ የመንግስትና የህዝብ መዋቅር መሆናቸው በማመን ‘ ቡድኑ’ ምክር ቤቶቹ በመጠቀም ያልደገፉትንና ሃሳቡ ያልተቀበሉት የመንግስት ሹመኞች ጥላሸት ለመቀባትና ከሃላፊነት ለማውረድ የሚያደርገው ጥረት መቆም አለበት ሲል አስጠንቅቋል።
ምክር ቤቶቹም ይህንን የመንግሰትና የፓለቲካ ድርጅት የሚቀላቅል ህገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ማውገዝ አለባቸው ብሏል።
” ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ህግና ስርዓት ለማስከበር ሲባል ወደ ህጋዊ ተጠያቂነት መሸጋገር የግድ ይሆናል ” በማለት አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት ከቀናት በፊት የጊዚያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ያወጣውን የአቋም መግለጫ የሚቃወም መግለጫ አውጥቷል።
በዶ/ር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት መስከረም 14/2017 ዓ.ም ያወጣው ባለ 4 ነጥብ የተቋውሞ መግለጫ ፤ ” ጊዚያዊ አስተዳደሩ ጊዚያዊ ስራዎች ለመስራት መቋቋሙ ተዘንግቶ ከተቀመጠለት የቆይታ የጊዜ ሰሌዳ በላይ እንዲቆይና ራሱን ወደ ተሟላ የመንግስት ሃላፊነት ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት ፀረ ዴሞክራሲና ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ” ብሏል።
ምንም እንኳን ” ኢ-ህገመንግስታዊ ” ብሎ ቢገልጽም የአገር ወይም የክልሉ ህገ-መንግስት አንቀፆችን አላጣቀሰም።
የእነ ዶ/ር ደብረፅዮን ቡድን ” ጊዚያዊ አስተዳደሩ የተሰጠው ተልእኮ ወደ ጎን በመተው ህወሓት ለማፍረስ ፣ ሰራዊት ለማዘዝና የመንግስትና ህዝብ ሃብት በመጠቀም የትግራይ ህዝብ አንድነት ለመበተን እየሄደበት ያለውን የተሳሳተ መንገድ ሊያቆም ይገባል ” ሲል አሳስቧል።