ሔለን ተስፋዬ

September 25, 2024

በጂቡቲ የሚገኘው ሆራይዘን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ

በጂቡቲ የሚገኘው ሆራይዘን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ የሚሰጠው አገልግሎት አቅም በመቀነሱ ምክንያት፣ ከጂቡቲ በተጨማሪ በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ በኩል ነዳጅ ለማስገባት ምክረ ሐሳብ ቀርቦ የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው።

በጂቡቲ የሚገኘው ሆራይዘን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ የሚሰጠው አገልግሎት አቅም መቀነሱ፣ በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦት ላይ መስተጓጎል እየፈጠረ መሆኑን፣ በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ጥናት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ  ለሪፖርተር ገልጸዋል።

‹‹መንግሥት ነዳጅ የመግዛት ችግር የለበትም፤›› ያሉት አቶ ለሜሳ፣ ነገር ግን ሆራይዘን የተባለው የጂቡቲ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ከተገነባ 18 ዓመታት የሞላውና አንድም ጊዜ ጥገና ተደርጎለት ስለማያውቅ የሚሰጠውን አገልግሎት መቀነሱን አስረድተዋል።

በጂቡቲ በኩል ያለውን የአገልግሎት አቅም መቀነስ ሲያስረዱም፣ ‹‹ለምሳሌ በቀን አሥር ሚሊዮን ሊትር ናፍጣ እንፈልጋለን፣ ነገር ግን ከጂቡቲ ተጭኖ የሚወጣው የነዳጅ መጠን እየቀነሰ ነው። በቀን ከሚያስፈልገን አሥር ሚሊዮን ሊትር ውስጥ በቀን እየወጣ ያለው ቢበዛ ስምንት ሚሊዮን ሊትር ነው፤›› ብለዋል። 

ይህንን ችግር ለመፍታት ሌሎች አማራጭ ወደቦችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል ያሉት አቶ ለሜሳ፣ የጂቡቲ ወደብ ማስተናገድ የሚችለውን ያህል መጠን ነዳጅ በጂቡቲ በኩል እንዲገባ፣ የተቀረው ደግሞ አማራጭ ተፈልጎ በሌላ ወደብ እንዲገባ ተወስኖ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።

‹‹በዚህም መሠረት የሶማሌላንድ በርበራ ወደብ ምቹና በቂ አገልግሎት መስጫ ፋሲሊቲዎች ያሉት መሆኑ በጥናት ተለይቶ፣ ወደቡን የመጠቀም ምክረ ሐሳብ ለመንግሥት ቀርቦ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው፤›› ብለዋል። 

በጂቡቲ ወደብ ያለው ችግር ካልተፈታ በሚቀጥለው ዓመትም በነዳጅ አቅርቦት የሚስተዋለው የመስተጓጎል ችግር እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 

በጂቡቲ ካለው ችግር በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ለሚታየው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል መንስዔ እንደሆነ የጠቀሱት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያካሄደ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ያፈረሳቸውን ነዳጅ ማደያዎች በፍጥነት ለመተካት ታሳቢ አድርጎ አለመንቀሳቀሱን ነው።

እስካሁን በተካሄደው የኮሪደር ልማት ስምንት ማደያዎች ሲፈርሱ ስለምትክ ማደያዎች አለመታሰቡን የጠቆሙት አቶ ለሜሳ፣ በዚህም ምክንያት በከተማው መሀል ነዳጅ ማደያ እየጠፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስካሁን በተካሄደው የኮሪደር ልማት ከቦሌ እስከ መገናኛ ድረስ ሦስት ማደያዎች (ቦሌ ኖክ፣ ቦሌ ብራስ ቶታልና ኒያላ ሞተርስ ኖክ) መፍረሳቸውን፣ ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ ድረስም ሦስት ማደያዎች እንዲሁም ካዛንቺስና ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ ፊት ለፊት የነበሩት ማደያዎች እንደፈረሱ አስረድተዋል። 

‹‹ነዳጅ ማደያዎች ከመሀል ከተማ እየጠፉ ነው። ለምሳሌ ከአራት ኪሎ እስከ ስድስት ኪሎ ምንም ማደያ የለም፡፡ ፒያሳ አካባቢ አንድም ማደያ የለም። ከቦሌ እስከ መገናኛ፣ እንዲሁም። ከኡራኤል እስከ ቦሌ ድረስ አንድም ማደያ የለም፤›› ብለዋል። 

ስለዚህ የከተማ አስተዳደሩ ማደያዎችን ሲያፈርስ ለተመሳሳይ አገልግሎት የሚውል ቦታ በዚያው አካባቢ ማዘጋጀት እንደነበረበት፣ ይህንንም ለከተማ አስተዳደሩ ማሳወቃቸውንና እስካሁን የመፍትሔ ምላሽ እንዳልተሰጠ ገልጸዋል።

እስካሁን በተካሄደው የኮሪደር ልማት የፈረሱትን ማደያዎች ጨምሮ በአጠቃላይ በኮሪደር ልማቱ 17 ማደያዎች እንደሚፈርሱም ጠቁመዋል።

ለአዲስ አበባ ከተማ በቀን 1.6 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ሰሞኑን የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ከሱሉልታ መጠባበቂያ ዴፖ በሃያ የነዳጅ ቦቴዎች ቤንዚን እንዲከፋፈል ማድረጉ ተሰምቷል።

በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ ሥርጭት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሞኘ ለኢቲቪ በሰጡት አስተያየት፣ ለተፈጠረው ችግር ሌሎች ምክንያቶችን አቅርበዋል።

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ነዳጅ ለመቅዳት የሚታየው ረጃጅም የተሽከርካሪዎች ሠልፍ በምን ምክንያት እንደተፈጠረ ለማጣራት ባለሥልጣኑ ባለሙያዎችን መድቦ ባደረገው ዳሰሳ የችግሩ ዋነኛ መንስዔ፣ ነዳጅ ይጠፋል በሚል ምክንያት በዕለቱ መቅዳት የማያስፈልጋቸው አሽከርካሪዎች ሳይቀሩ በየማደያው ነዳጅ ለመቅዳት መሠለፋቸው ነው።

ለአዲስ አበባ ከተማ በቀን እስከ 1.6 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እየቀረበ በመሆኑ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንደሌለ፣ ነገር ግን ሁሉም የነዳጅ ማደያዎች በአንድ ቀን እኩል አቅርቦት ሊኖራቸው እንደማይችል አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ 120 ማደያዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ አብዛኞቹ ማደያዎች አራት ማሽኖች ቢኖሯቸውም አንዳንዶቹ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በአንድ ማሽን ብቻ መሆኑ ለሠልፉ መበራከት ሌላኛው ምክንያት መሆኑንም አክለዋል።

በተጨማሪም የችግሩን ሌሎች ምክንያቶች ለማወቅና ለመፍታትም ባለሥልጣኑ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከ770 ሺህ በላይ የቤንዚን ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን፣ ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጡት ደግሞ 120 ማደያዎች ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።