ዜና
የሕወሓት ሊቀመንበር ከእሳቸው በተቃራኒ የቆሙ አመራሮችን መውቀስ ጀመሩ

ልዋም አታክልቲ

ቀን: September 25, 2024

‹‹ተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ የያዘውን ቂም እኔ ላይ እንጂ የትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲወጣ አልፈቅድም››

ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሕወሓት ሊቀመንበር

‹‹እኔ በማንም ላይ የያዝኩት ቂም የለም›› 

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈጠሩ ልዩነቶችን በማስታወስ፣ በአሁኑ ጊዜ ከእሳቸው ተቃራኒ የቆሙ የሕወሓትና የትግራይ ጦር ከፍተኛ አመራሮችን በአደባባይ መውቀስ ጀመሩ።

ከሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ በፊት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አስከትሎ በስተመጨረሻ በፕሪቶሪያው ስምምነት የተገታው የትግራይ ጦርነት እንዲገመገም የቀረበውን ጥያቄ  ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ውድቅ በማድረግ፣ ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄዳቸው ከእሳቸው ተቃራኒ በቆሙ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሲተቹ እንደነበር ይታወሳል።

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደው የፓርቲውን የሊቀመንበርነት ሥልጣኑን እንደገና ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ከእሳቸው በተቃራኒ የቆሙ የሕወሓትና የትግራይ ጦር ከፍተኛ አመራሮችን ‹‹ሥልጣን ለመቆጣጠር ሲያሴሩ ነበር፤›› በማለት ሰሞኑን በአደባባይ ሲተቹ ተደምጠዋል።

ሕወሓት የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁነቶችን አስመልክቶ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ሕዝባዊ ውይይቶችን ከሐሙስ መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እያካሄደ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ በሊቀመንበሩ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ሰብሳቢነት ባለፈው ቅዳሜ በመቀሌ ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ይገኝበታል።

በመቀሌው ውይይት በትግራይ ያለውን ፖለቲካዊ ክፍፍል አስመልክቶ ከሕዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣  በሕወሓት ውስጥ የፖለቲካ ልዩነት መፈጠር የተለመደ መሆኑን፣ ለአብነትም ሕወሓትን ከመሠረቱት ሰዎች መካከል አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ድርጅቱ መጠናከር በጀመረበት የትጥቅ ትግል ወቅት በነበራቸው ልዩነት መሰናበታቸውን አስታውሰዋል። 

ነገር ግን ‹‹ህንፍሽፍሽ›› ተብሎ የሚጠራው የ1993 ዓ.ም. የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ፖለቲካዊ ክፍፍልን ተከትሎ ቂም የቋጠሩ አካላት አሁን ድርጅቱን ለማፍረስ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን፣ ከእነዚህም መካከል ዋነኛው ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳይ እንደሆኑ በይፋ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅቱ በሕወሓት ውስጥ ሥር የሰደደው የሥልጣን ሽኩቻ መታየት የጀመረው በሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት ወቅት መሆኑን የጠቆሙት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹ፃድቃን ተከዜ አካባቢ ውጊያ ላይ በነበርንበት ወቅት ደብረ ጽዮን በሱዳን በኩል ከአገር መውጣት አለበት እስከ ማለት ደርሶ ነበር፤›› ሲሉ በመቀሌው ሕዝባዊ ውይይት በይፋ ተናግረዋል፡፡ 

በጦርነቱ ወቅት ሥልጣንን ለመቆናጠጥ ሲባል ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተፈጥረው እንደነበር ያወሱት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹ከጦርነቱ ማን በሕይወት ተርፎ ይመለሳል የሚለው እንኳን ባልታወቀበት ሁኔታ ማስተካከያ እናድርግ የሚል ውትወታ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ 

ጦርነቱ ሲያበቃ እንዲባረሩ ተወስኖባቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን መሆናቸውንም አስረድተዋል።

‹‹በክልሉ አንፃራዊ ሰላም መታየት ከጀመረ በኋላ ፃድቃንን በተመለከተ ተወያይተን በጦርነቱ ወቅት ውድ ሕይወቱን ስለሰጠ፣ በአንድ ድክመት ምክንያት ልናባርረው አይገባም ብለን ከአምስት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ሦስታችን ብቻ ይቆይ፣ የሆነ ኃላፊነት ሊሰጠው ይገባል ብለን ወሰንን፡፡ ሌሎቹ ይውጣ፣ ይባረር ብለው ነበር፡፡ ሕይወቱን አሳልፎ ስለሰጠ ጥፋቱ ይሻርለት ብለን ነው ያቆየነው እኛ ነን፤›› ብለዋል፡፡ 

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው ከሕወሓት፣ ከምሁራን፣ ከፀጥታ አካላትና ከተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችን አካቶ መሆኑን ያስታወሱት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባል የሆኑት በትግራይ ምሁራን ተወክለው እንደሆነ ገልጸዋል። 

‹‹እኛም አጉል ከሚሆን ኃላፊነት ይኑረው አልን፣ ነገር ግን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኃላፊነት እንዲሰጠው አልነበረም ያሰብነው፤›› ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹እንዳላችሁት ፃድቃን ቂመኛ ነው፣ ቂሙን ነው እየተወጣ ያለው፡፡ ግን ደግሞ ቂሙን ከፈለገ እኔ ደብረ ጽዮን ላይ እንጂ የትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲወጣ አልፈቅድም፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ 

ጦርነቱ እየተካሄደ በተለይም የትግራይ ኃይል ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተደራድሮ ሰላም የማውረድ ሐሳብ ተነስቶ እንደነበር አስታውሰው በወቅቱ፣ ‹‹ከማን ጋር ልንደራደር ነው? ያለቀ ጉዳይ ነው ሲሉ የነበሩ እንደ ፃድቃን ያሉ ሰዎች፣ ዛሬ ተገልብጠው ሕወሓት ጦረኛ፣ እነሱ ደግሞ ሰላም ፈላጊ እንደሆኑ ያስመስላሉ፤›› ብለዋል።

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ይህንን ከመናገራቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለትግራይ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ ሰጥተው የነበሩት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ በሕወሓት አመራር ላይ ያልሻረ ቂም እንዳላቸው ተደርገው እንደሚታዩና እንደሚታሙ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

እሳቸው በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹እኔ ከማንም ጋር ቂም የለኝም፣ ቂም ይዟል የሚል ካለ ይምጣ፤›› ብለው ነበር።

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በመቀሌ በነበራቸው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳንም ወርፈዋል።

‹‹ጌታቸው ራሱ ከኤርትራ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝቶ በየሚድያው እየዞረ ሕወሓት ከኤርትራ ጋር እየሠራ ነው ይላል፤›› በማለት የተቹት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹አቶ ጌታቸው ሕወሓት ክዶኛልና የፌዴራል መንግሥትን አግዘኝ እያለ ነው፡፡ ሁሉንም ተናግሬ መዘርገፍ ፈልጌ አይደለም፣ ግን ጌታቸው ውሸት መናገሩን ካላቆመ፣ እኔም እውነታውን መናገሬን እቀጥላለሁ፣ እንዲያውም እጨምርለታለሁ›› ሲሉም ተደምጠዋል።

‹‹ሁሉንም ነገር ተናግሮ መዘርገፍ ተገቢ ነው ብዬ ባላምንም፣ ብዙ ነገር አውቃለሁና ከዚህ በኋላ መነገር ያለበትን ለሕዝብ ከመናገር ወደኋላ አልልም፣ አቶ ጌታቸው በየሚዲያው እየዞረ ብዙ እያለ ነው፣ ነገሮችን ገልብጦ መናገሩን ከቀጠለ እኔም እውነቱን እናገራለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የፕሪቶሪያውን ስምምነት በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ስምምነቱን ለመፈጸም የተወከለው ልዑክ ተኩስ የማስቆም ኃላፊነት ብቻ ተሰጥቶት ሳለ ስለጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታ ተነጋግሮና ፈርሞ መመለሱን ተናግረዋል፡፡ 

ይህንን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የማቋቋም ሐሳብ በፌዴራል መንግሥት በኩል እንዳልነበር፣ ሐሳቡ የተነሳው ከትግራይ ተደራዳሪዎች መሆኑን እንደተናገሩ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ለውይይቱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ 

‹‹በዚህ ደረጃ ኃላፊነት ማን ሰጣችሁ ሲባሉ ተኩስ ለማስቆም ኃላፊነት ሰጥታችሁናል ብለው ነው የሞገቱን፣ ብዙ ጥፋት እያጠፉ ነው፡፡ ይህ አደገኛ አካሄድ ነው፤›› ብለዋል።

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ከሰሞኑ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የፕሪቶሪያው ስምምነት የሕወሓትና የፌደራሉ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መሆኑን፣ አደራዳሪዎቹም በአንክሮ የሚመለከቱት ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል። አፈጻጸሙንም የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎችም አጋር አካላት እየተከታተሉት እንደሆነ፣ ይህም የውሉ አቅጣጫ በአንድ ወገን እንዲቀየር ተደርጓል የሚለውን ክስ ውድቅ የሚያደርግ እንደሆነ በመጠቆም ከሕወሓት በኩል የሚነሳውን ወቀሳ አጣጥለውታል።