
Byአንባቢ
September 29, 2024

በየሀብከ ብርሃኔ ጥላሁን
የመስቀል በዓል መከበር ከጀመረ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል። በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና ባህላዊ ትውፊቶች ደምቆና አሸብርቆ የሚከበር በመሆኑም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል ቀዳሚው ለመሆን ችሏል።

በቤተ ጉራጌ መስቀል የአንድ ቀን በዓል አይደለም፡፡ ከአሥር ቀናት በላይ የሚወስድ ልዩ የደስታ በዓል ነው፡፡ መስቀል በቤተ ጉራጌ በአቡነ ዜና ማርቆስ ዘመን ወንጌልን ከማዳረስ ጋር በተደረገ ሐዋርያዊ ጉዞ በተፈጸመ ገቢረ ተዓምራት ምክንያት እንደተጀመረ ገድላቸው ይናገራል፡፡ በዓሉ በጉራጌዎች ዘንድ የተለየ የአከዋወን ሥርዓት አለው።
ከመስከረም 12 በፊት የጉራጌ ተወላጆች፣ ከመላው የአገሪቱ ክፍል ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ይተማሉ፡፡ ከወጣቶች በሰው እስከሚደገፉ አዛውንቶች ድረስ የመስቀል ሰሞን አገር ቤት የመግባታቸው ነገር አያጠያቅም፡፡ መስቀል በጉራጌ ሃይማኖታዊ በዓል፣ የመተጫጫ ወቅት፣ የቤተሰብ የዘመድ አዝማድ መጠያዬቂያ፣ የእርቅና የአንድነት ዓውድ ስለሆነ መች በደረሰ እየተባለ በናፍቆት የሚጠበቅ በዓል ነው፡፡ በቤተ ጉራጌ በዓሉ እስከ መስከረም 23 ቀን ድረስ ይቆያል። ሁሉም ቀናት የራሳቸው የሆነ ስያሜ፣ ትርጓሜና ሥርዓት አላቸው።
መስከረም 13 ‹ወሬት ያህና› በተሰኘው የበዓል መክፈቻ መሰናዶ ሰሞነ መስቀል ይጀመራል፡፡ ወሬት ያህና ጉጉት እና ናፍቆት የፈጠረውን እንቅልፍ አልባ ቀን የሚዘክር ቃል ነው፡፡

ይሄው ቀን «ወልቀን» ተብሎ ሲጠራ ትርጓሜውም የሴቶች ቀን በመባል ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ሴቶች ጎመንና ዓይብን በማዘጋጀት፣ ደዋወሸት የሚባለውን ማባያ ቆጮ ተጠቅመው አጠቃላይ የቤተሰቡ አባላት ለየራሳቸው በተዘጋጀላቸው «ጣባ» አማካይነት ይመገባሉ። ጣባዎቹ ተሰቅለው ከተቀመጡበት ለመስቀል በዓል ብቻ የሚወርዱ ሲሆን፣ በቤተሰቡ ልክና በየስማቸው የተዘጋጁ ናቸው። ተለይቶ የማይሰጠው ባልና ሚስት ለሆኑ ብቻ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው።
መስከረም 14 «ደንጌሳት» በመባል ሲጠራ የልጆች ወይም የሕፃናት ቀን ይባላል። ይኸውም ልጆች በትንሹ በሠፈር አካባቢ ደመራ ደምረው የሚጫወቱበት ቀን ነው።
የእርድ ዋዜማ ሲሆን የልጆች የደመራ፣ የሴቶች የአይቤና ጎመን ቀንም ይባላል፡፡ ደመራው ካለቀም በኋላ አባቶችና እናቶች ይመርቃሉ። በዚህ ቀንም እንደመጀመሪያው ሁሉ በቤት ውስጥ ጅባ እና እንጮት ተነጥፎ ‹ደዋወሸት› ይሰጣል። ቤቶች የሚሰነዳዱበት የእንፋሎት ቆጮ የሚቀርብበት ቀንም ነው፡፡
መስከረም 15 ‹ጨርቆስ› ወይም ‹ወኸምያ› በመባል የሚጠራ ሲሆን፣ የእርድ ቀን በመባልም ይነገራል። ዕለቱ እርድ የሚፈጸምበት በመሆኑ የሚታረደው በሬ ሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ ሽማግሌዎች ስለአገር ሰላምና በዓሉን በተመለከተ እያነሱ ይመርቃሉ። መልካም ምኞታቸውንም ይገልጻሉ። የቤተሰቡ አባላትም ሦስት ጊዜ ‹‹ኬር ይሁን›› በማለት ምርቃቱን ይቀበላሉ። ትርጉሙ ሰላም ይሁን ማለት ነው። በእዚህ ባህላዊ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲመርቁ የሚጋበዙት ሴቶች ወይም ወንዶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ለማሳረጊያነት የሚሆነውን ምርቃት ሁሌም የሚመርቀው ወንድ እንጂ ሴት አይሆንም።
መስከረም 16 አንደኛ ‹ምግይር› ወይም የደመራ ቀን ይባላል፡፡ በየቤቱ ጥዋት የሕፃናት፣ ማታ ደግሞ የአባቶች ደመራ ይለኮሳል፡፡ በዚህ ዕለት ከብቶች ከቤት አይወጡም፡፡ ሁለተኛ ‹የብርንዶ› ወይም የክትፎ ቀን ይባላል። የጉራጌን ባህላዊ የአመጋገብ ሥርዓትን ከሚያመላክቱ መሠረታዊ ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የክትፎ አመጋገብ ሥርዓት ነው። ቀኑ ለየት ያለና ትኩረት የሚሰጠው ዕለት ሲሆን፣ በዚህ ቀን ትልቁ ደመራ የሚደመርበትና ጎረምሶችና ልጃገረዶች በባህላዊ ጭፈራ የሚተያዩበት ቀንም እንደሆነ ይነገራል።
መስከረም 17 ‹ንቅባር› ወይንም ትልቁ በዓል ነው፡፡ ዘመድ አዝማድ ሻኛ አስመርቆ በጋራ የሚቋደስበት፣ ጎረቤት በአንድ ሆኖ ሲስቅ ሲያወካ የሚውልበት የማኅበረሰብ መሰብሰቢያ ቀን ነው፡፡ ዕለቱ ‹ከሰል› በመባልም ይጠራል። በዚህ ቀን ሁሉም የቤተሰብ አባላት ደመራው ወደተደመረበት ቦታ በመሄድ ከሰሉን እየረገጡ የሚሻገሩበትና ዘመኑ መልካም ዘመን እንዲሆንላቸው የሚማጸኑበት ነው፡፡ ከሰል መጥፎው ወይም ጥሩ ያልነበረው ነገር የጠፋበትና ብርሃን የታየበት ዕለት ማብሰሪያ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ የራሱን ዕቅድ ይዞ ለመልካም ነገር የሚነሳበትም ነው ይባላል።
ከመስከረም 18 እስከ 23 ‹የጀውጀው› የሚባለው ሥርዓት ይቀጥላል፡፡ የጀውጀው የመተያያ ቀን ሲሆን ባለትዳሮች ስጦታና መመረቂያ ይዘው ወደ ወላጆቻቸው ቤት በማቅናት የሚጠይቁበት ነው፡፡
የመዝጊው በዓል ‹አዳብና› ይባላል፡፡ አዳብና ጎረምሶችና ልጃገረዶች የጭፈራ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት፣ የወደፊት የትዳር ተጣማሪያቸውን የሚያዩበት፣ የሚያጩበት በዓል ነው፡፡
በቤተ ጉራጌ በጉጉት ከሚጠበቁ የወጣት ወንዶችና ልጃገረጆች ጨዋታዎች መካከል አዳብና አንዱና ዋነኛው የባህል ጨዋታ ነው። ይህ የወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ጨዋታ ከመስቀል ደመራ ዕለት ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5 ቀን ድረስ በየገበያ ሥፍራዎችና በየደብሩ በደማቅ ሁኔታ ይቀጥላል።
አዳብና ከመድረሱ በፊት ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች በተለያየ መንገድ አዳብናን ለማክበር ይዘገጃጃሉ። ያላገቡ ወጣት ወንዶች፣ የቡሔ ዕለት በየአባቢያቸው ባለ ሰፊ መስክ ላይ ደመራ (ምጅር) ያቆማሉ። በዛው ክረምቱ ማለፉንም ጅራፍ በመተኮስ ያበስራሉ። ሆያ ሆሄም በመጨፈር አዳብና ጨዋታ ላይ ልባቸው ለከጀላት ኮረዳ ስጦታ ገዝቶ (ሎሚ፣ ማስቲካ) ለመስጠት ገንዘብ ያጠራቅማሉ።
ልጃገረዶችም በበኩላቸው በአዲስ ዓመት ዋዜማ ቀን ‹‹አዬ አዬ ሆ አዬ አዬ ሆ አዬ ንብለ›› እያሉ እንጊጫ በመንቀልና ለአዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ በመጨፈር ለአዳብናቸው ገንዘብ ያጥራቅማሉ፡፡ የአዳብና ዕለት አምሮ ለመታየት አዲስ ልብስና ጌጣጌጣቸውን ያዘጋጃሉ፣ ፀጉራቸውን በልዩ ሁኔታ ይሠራሉ።
ወንዶችም፣ ሴቶችም ከአዲስ ዓመት (አክራሚ) ዋዜማ ቀን ጀምሮ መስቀል እስኪደርስ ድረስ በየአካባቢው ባቆሙት ደመራ (ምጅር) ምሽት ምሽት ተሰብስበው ይጨፍራሉ። ይህ አዳብና ከመድረሱ በፊት ጓደኝነታቸው የሚያጎለበቱበት አዳብና የት የት እንደሚሄዱ የሚቀጣጠሩበት ጊዜ ነው። እንዲሁም ታዳጊ ልጆች አጨፋፈሩን የሚማሩበትና ልምድ የሚወስዱበት ጊዜም ጭምር ነው።
አዳብና የተለያዩ የጨዋታ መልኮች ቢኖሩትም፣ ወንዶችና ልጃገረዶች አብረው ክብ ሠርተው፣ ወንዶች በጉረሮ በሚያወጡት ልዩ ድምፅና በጭብጨባ፣ ልጃገረዶቹ በከበሮና በጭብጨባ፣ የተወሰኑት ወንዶችና ልጃገረዶች ደግሞ በክቡ መሐል በመግባትና በመጨፈር የሚያሳዩት ትርዒት ዋነኛው ነው።
የጨዋታውን የማስጀመሪያ ግጥም በማውጣት ወንዶቹም ልጃገረዶችም ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ወንዱ ከጨዋታው መሐል በፀባይዋና በመልኳ ቀልቡን የሳበችው ልጅ ካለች እንዲህ ብሎ ሊገጥም ይችላል።
‹‹በማለሲ ቂልጡ ወፊ ይንጊሊጡ፣ (2)
ዚ የማና ቅንጡ እጅዲ ያረጡ፤››
ትርጉም፦ በትሿ ዋርካ ወፏ ትዘፍናለች፣
የማናት ልጅቷ ቅንጡ የሆነች፤
‹‹የቱሉ እንቁቦሆም ቶናም ጡብየኢ፣(2)
የአቢዲ ዲሞፍተር የመስሉ ላባኢ፤››
ትርጉም፦
እንደ ጋራ እንጉዳይ ቁጭ ብለዋል ጡቶችዋ፣
የአባቴን ዲሞፍተር ይመስላል ዳሌዋ፤
ግጥሞቹ ቅኔ ለበስ በሆነ መልኩ አድናቆት፣ ሽሙጥና ወቅታዊ ሁኔታዎችንም ያነሳሳሉ። አዳብና ላይ ወንዶች ተሳታፊዎች ‹አጋት› የሚባል ሌላ ጨዋታም ጨምረው ይጫወታሉ። በመጀመሪያ አንድ ተጫዋች ከፊት ለፊት ቀጥ ብሎ ይቆማል። ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ በግምት ከ20 ሜትር ላይ በመንደርደር የቆመውን ተጫዋች ከእጁ በስተቀር ትክሻውና ጭንቅላቱ ሳይነካ ዘሎ ያልፋል።
ተጫዋቹ ጭንቅላቱን ሳይነካ ማለፍ ካቃተው፣ እሱ በተራው ቋሚ ይኾናል። ማለፍ ከቻለ ግን ቆሞ የነበረው ተጫዋች ትክሻ ላይ ወጥቶ በመቀመጥ ሎሚ ወደ ላይ ይወረውራል። ሎሚዋን ተሻምቶ የያዘ ሰው የሚቀጥለው ዘላይ ተጫዋች ይሆናል። አዳብናው ሞቅ በሚልባቸው አካባቢዎች የፈረስ ጉግስም ሊኖር ይችላል።
አዳብና ጨዋታ ፥ ወንዶችና ልጃገረዶች ለትዳር አጋርነት የሚተጫጩበት ወቅትና ቦታ ነው ማለት ይቻላል። ወንዱ በጨዋታው መሐል ቀልቡ ያረፈባትን ኮረዳ (ቀንዠ) ካየ፣ ከኮረዳዋ በኋላ በኩል ሄዶ ቀሚሷን በያዘው አለንጋ መታ ያደርጋታል። በዚህ ጊዜ ኮረዳዋ ቀሚሷን በአለንጋ የገረፋት ጎረምሳ እንደመረጣትና እንደወደዳት በመረዳት ትሽኮረመማለች። አንዳንዴም ጭራሹኑ ልታለቅስ ትችላለች።
ወንድዬውም በዚህ ብቻ አያበቃም። የወደዳትን ልጃገረድ (ቀንዠ) ቀስ ብሎ በጓደኞቿ በኩል ሎሚ ወይም ማስቲካ ይልክላታል። ከተቀበለች እሷም ወደዋለች ተስማምታለች ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ወንድዬው የትዳር አጋሩ እንድትሆን ከፈለገ፣ ጎሳዋንና (በጉራጌ የጋብቻ ሥርዓት ተመሳሳይ ጎሳ ስለማይጋባ) አካባቢዋን ካጣራ በኋላ፣ እንድትለመንለት (እንድትታጭለት) ለቤተሰቦቹ ይናገራል።
ቤተሰቦቹም ወደ ልጅቷ ቤተሰብ ሽማግሌ ይልካሉ። የሽማግሌዎቹ ልመና ተቀባይነት ካገኘ፣ በዛው ዓመት ጥሎሽ (ቸግ) ይጣላል። ቸግ ከጣለ በኋላ የጋብቻ ጥያቄው ሕጋዊ ሆነ ማለት ነው። ምን አልባት በሠርግ እስኪጋቡ ድረስ በእጮኝነት ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ሊቆዩ ይችላሉ። እስከ ሠርጉ ዕለት ድረስ በየዓመቱ አዳብና ላይ እየተገናኙ ይጫወታሉ፣ ስጦታ ይሰጣጣሉ። ልክ በሠርግ ከተጋቡ በኋላ በዓመታቸው የመጨረሻውን አዳብና አክብረው አዳብና መሔድ ያቆማሉ።
ሁሉም የብሔረሰቡ አባላት የሚሳተፉበት የመስቀል በዓል የሚያካትታቸው ክንውኖች ካለ ምርቃትና መልካም ምኞቶች አይደመደሙም፡፡ የዕድሜ ባለፀጎች ‹‹የአገራችንን ዳር ዳር ለጠላት እሳት፣ ለሕዝቦቿ መሃሏን ገነት ያድርግልን›› ከሚለው ምርቃት ጀምሮ ሰው፣ ከብቱ፣ ጋራ እና ሸንተረሩ ሰላምና ልምላሜ፣ በረከትና ፀጋ እንዳይለየው ይመረቃል፡፡ ታዳሚውም የአባቶችን ምርቃት እየተከተለ ‹‹አሜን!›› ይላል፡፡
(ማጣቀሻዎቼ፡ ዘፀአት ቱቼ ያልታተመ ዳሰሳ ጥናት፣ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በራሪ ወረቀት፣ መሠረት የማኅበራዊ ገጽ ጽሑፍ)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
