ከ 9 ሰአት በፊት
የኬንያ ፓርላማ የሕዝብ እንደራሴዎች የአገሪቱን ምክትል ፕሬዝዳንት ከሥልጣናቸው ለማውረድ የሚያስችላቸውን ሕጋዊ ሂደት ጀመሩ።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሪጋቲ ጋቻጉዋ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ የሚደግፉ የፓርላማው አባላት ሰኔ ወር ላይ በተካሄደው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ እጃቸው አለበት፣ በሙስና ውስጥ ተሳትፈዋል፣ መንግሥትን አጣጥለዋል እንዲሁም በጎሳ የሚከፋፍል ፖለቲካን ያበረታታሉ ሲሉ ይወነጅሏቸዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ ግን የሚቀርብባቸውን ውንጀላ ሁላ ያስተባብላሉ።
ብዙዎች ይህ የአሁኑ የአገሪቱ ምክር ቤት አባላት እርምጃ በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና በምክትላቸው ጋቻጉዋ መካከል ያለው መቃቃር ድምር ውጤት ነው ብለዋል።
ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 21/2017 ዓ.ም. የተሰበሰቡ የአገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ምክትል ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ለማውረድ የቀረበውን ሀሳብ በ291 የድጋፍ ድምጽ አሳልፈውታል።
ይህ የድጋፍ ድምጽ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ለማንሳት ለሚጀመረው ሂደት ከሚያስፈልገው 171 ድምጽ በላይ ነው።
ምክትል ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን የማውረድ ጥያቄው በቅርቡ የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ተቃዋሚዎች ከፕሬዝዳንቱ ፓርቲ ጋር በአንድ በመጣመራቸው በሁለቱም የኬንያ ምክር ቤቶች በቀላሉ ያልፋል ተብሎ ተገምቷል።
ነገር ግን ይህ መቼ እንደሚሆን ገና ቀን አልተቆረጠለትም።
- በሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ ከሰኔ ወዲህ 10 ህጻናት በጅብ መበላታቸውን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ1 ጥቅምት 2024
- በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጭንቀት፡ “የአራት ወር ልጄን ምን ላብላት?”1 ጥቅምት 2024
- ሙዝ በዳቦ እየበሉ ‘ፒኤችዲ’ የሚማሩ የዩኒቨርስቲ መምህራን ሰቆቃ30 መስከረም 2024
የምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ ከሥልጣን ይውረዱ የሚለው ጥያቄ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳይቀርብ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት አቤት ቢባልም ተቀባይነት አላገኘም።
በፕሬዝዳንቱ እና በምክትላቸው መካከል ያለው የሥልጣን ሽሚያ ኬንያ በከፋ የምጣኔ ሃብት እና የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ጊዜ በመንግሥት ውስጥ አለመረጋጋትን ይፈጥራል የሚል ስጋት አጭሯል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ ምክትላቸው ጋቻጉዋን የመረጡት በጠባብ ልዩነት ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋን ባሸነፉበት በአውሮፓውያኑ 2022 ምርጫ ዘመቻ ወቅት ነው።
ጋቻጉዋ የተመረጡት ማውንት ኬንያ ከሚባለው የአገሪቱ አካባቢ ሲሆን፣ አሁንም የማዕከላዊ ኬንያ ጠንካራ ድጋፍ እንዳላቸው ይናገራሉ።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ “ሁለት መቶ ተወካዮች የሕዝብን ፍላጎት ሊቀለብሱ አይችሉም” ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ ለፓርላማ የቀረበው ጥያቄ ለማለፍ ቢያንስ የብሔራዊ ምክር ቤቱን እና የሴኔቱን አባላት ሁለት ሦስተኛውን ድምጽ ማግኘት አለበት።
ምክትል ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ለማንሳት የቆረጡ የምክር ቤቱ አባላት ሃሳባቸው በአብላጫ ድምጽ እንደሚጸድቅ እርግጠኞች ናቸው።
ነገር ግን ምክትል ፕሬዝዳነት ጋቻጉዋም እንዲሁ በቀላሉ ሊበገሩ የሚፈልጉ አልሆኑም።
“ፕሬዝዳንቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱን ሊያስቆሟቸው ይችላሉ። ካልሆነ ግን እርሳቸውም አሉበት ማለት ነው” ሲሉ ከዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ በፊት ጋቻግዋ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረው ነበር።
በፕሬዝዳንት ሩቶ እና በጋቻጉዋ መካከል ያለው ቅራኔ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ወደ ተለያዩ አገራት ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት አየር ማረፊያ ተገኝተው ሽኝት ማድረግም ሆነ ሲመለሱ መቀበል ካቆሙ ከራርመዋል።