1 ጥቅምት 2024, 14:29 EAT
በሲዳማ ክልል፤ ደቡባዊ ሲዳማ ዞን ዳራ ወረዳ ከሰኔ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ጅቦች በተከታታይ ባደረሱት ጥቃት አስር ህጻናትን ጨምሮ 12 ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ እና አምስት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ።
የጅብ ጥቃቶቹን ተከትሎ የወረዳው ነዋሪዎች ባደረጓቸው ዘመቻዎች ከ40 በላይ ጅቦች መገደላቸውም ተገልጿል።
በሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ የጅብ ጥቃት በተከታታይ ማጋጠም የጀመረው ካለፈው ሰኔ ማገባደጃ ጀምሮ መሆኑን የወረዳው መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ማቲዮስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በወቅቱ አጎራባች በሆነው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲላ ዙሪያ ወረዳ የጅብ መንጋ በሰዎች ላይ ጉዳት አድርሶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ መልካሙ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ በጅቦቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ወደ ዳራ ወረዳ “መፍለሳቸውን” ገልጸዋል።
እንስሳትን ነጥቆ በመብላት የጀመሩት ጅቦች ከሰኔ 22/2016 ዓ.ም. አንስቶ በሰዎችም ላይ ጥቃት ማድረስ እንደቀጠሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል።
እስካሁን ድረስ ወረዳው ካሉት 24 የከተማ እና የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በሰባቱ ውስጥ በጅቦች ጥቃት እንደተፈጸመ ገልጸዋል።
የዳራ ወረዳ ሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባይነህ አመሎ በበኩላቸው የጅብ ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉ ቀበሌዎች “ለከተማ ቀረብ ያሉ” እንደሆኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጅቦቹ አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቱን የሚያደርሱት በህጻናት ላይ እንደሆነም አቶ አባይነህ ገልጸዋል።
የወረዳው መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ መልካሙ እንደሚያስረዱት ከሰኔ ወር ጀምሮ ጅቦች በ17 ሰዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል።
ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ 15 ያህሉ የተፈጸሙት በህጻናት ላይ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መልካሙ፤ ጉዳት ደርሶባቸው የተረፉት አምስቱ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በጅብ የተበሉት አስር ህጻናት ከአምስት እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ከህጻናቱ ባሻገርም ሁለት አዋቂ ሰዎች በጅብ መበላታቸውን የሚያስረዱት አቶ መልካሙ፤ በአጠቃላይ 12 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን አመልክተዋል።
አብዛኛዎቹ ህጻናት ጥቃት የደረሰባቸው ውሃ ለመቅዳት እና ልብስ ለማጠብ ወደ ወንዝ በወረዱበት ወቅት እንዲሁም ከብት በማገድ ላይ እያሉ እንደሆነም አስረድተዋል።
ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያነሱት የወረዳው ሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባይነህ በበኩላቸው ጅቦች “በጠራራ ፀሃይ” ጥቃት እያደረሱ ያሉት “አድፍጠው” እና “ሌሎች ሰዎች ባሉበት” ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል።
አቶ አባይነህ፤ “የ14 ዓመት ልጅ ከእናቷ ጋር በምትሄድበት ነው ገንጥሎ የጣላት። እናትየው ለማዳን ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም አልቻለችም። ከአቅሟ በላይ ሆኖ ነው የጎዳት። ልጅቷ በጩኸት እና በሕዝቡ [ጥረት] ቢገድላትም ሳይበላት አስከሬኗ ተገኝቶ ተቀብሯል” በማለት ከጥቃቶቹ አንዱን አስታውሰዋል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ መልካሙ እንደሚናገሩት በወረዳው የመጨረሻው የጅብ ጥቃት የተፈጸመው መስከረም 12/ 2016 ዓ.ም. ነበር።
“[ጅብ] እሁድ ቤተ ክርስቲያን ፕሮግራም ሄዳ እየተመለሰች፤ ከቤተሰቦቿ ወደ ኋላ ቀርታ እየመጣች ያለችን ህጻን የበላበት ሁኔታ ነው ያለው። የሰባት ዓመት ልጅ እንደሆነች ነው ጤና ባለሙያዎች መረጃ የሰጡን” ሲሉ ጥቃቱን አስታውሰዋል።
አቶ መልካሙ ባለፈው ሳምንት ምንም ጥቃት እንዳልደረሰ ቢናገሩም የወረዳው ሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባይነህ እንዲሁም ሁለት የወረዳው ነዋሪዎች ባለፉት ቀናት ሌሎች ጥቃቶች መድረሳቸውን ገልጸዋል። ይሁንና ከሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊውም ሆነ ከነዋሪዎች የተገኙት መረጃዎች ልዩነት ያላቸው ናቸው።
አቶ አባይነህ እና አንድ ነዋሪ እሁድ መስከረም 19 2017 ዓ.ም. አንዲት ታዳጊ በጅብ ተበልታ ህይወቷ ማለፉን ተናግረዋል። ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው በዕለቱ ጥቃት የደረሰባት ታዳጊ ተርፋለች ብለዋል።
በዳራ ወረዳ ያጋጠመውን ተከታታይ የጅብ ጥቃት ተከትሎ በወረዳው አስተዳዳሪ የሚመራ ግብረ ኃይል መቋቋሙን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ገልጸዋል። በየአካባቢው “ሚሊሻ እና ፖሊሶች የያዘ ሮንድ” እንዲቋቋም መደረጉንም ጠቅሰዋል።
“በስፋት ጫካ ያለበት አካባቢ እንዲመነጠር፣ [ጅብ] የሚኖርበት ጉድጓድ አካባቢ እንዲደፈን እንዲሁም ደግሞ በሃይማኖት መሪዎች እና ሽማግሌዎች ህጻናት ከአካባቢው ወጥተው እንዳይሄዱ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እንዲሰራ ነው የተደረገው” ሲሉ ጥቃቱን ለማስቀረት የተደረጉት ጥረቶች ዘርዝረዋል።
የወረዳው አስተዳደር እየወሰደ ካላቸው እርምጃዎች በተጨማሪ የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉት “የአጸፋ እርምጃ” ከ40 በላይ ጅቦች መገደላቸውን አቶ መልካሙ አስረድተዋል። በዚህ ዘመቻ ላይ ህብረተሰቡ ባህላዊ መሳሪያዎች የሚገልጹት ኃላፊው፤ “በጠመንጃ” የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
“ምናልባት በዚህ ሳምንት ያገኘነው ሰላም ከቀጠለ ቀጠለ፤ ካልቀጠለ ግን የጸጥታውን አካል በሰማራት ጭምር ይህ ነገር ቀጣይነት እንዳይኖረው እና በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲያከትምለት እርምጃ የመውሰዱ አግባብ በወረዳው አስተዳዳሪ እየተገመገመ [ነው]” ብለዋል።