1 ጥቅምት 2024, 07:04 EAT
የሊባኖስ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሳምንት ባለፈው የእስራኤል የአየር ጥቃት ከ1000 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
እስራኤል በሊባኖስ የአየር ድብደባ መፈጸሟን ቀጥላለች። የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉ በኋላ ደግሞ ነገሮች የበለጠ ሊባባሱ እንደሚችሉ ስጋት አንዣቧል።
እስራኤል በቀጣይ በእግረኛ ጦር ወረራ እንደምትፈጽም የገለጸች ሲሆን፣ የሄዝቦላህ ምክትል መሪ ወደ ግዛታቸው የሚገቡትን የእስራኤል ወታደራሮች ለመከላከል “ዝግጁ ነን” ብለዋል።
በሥራ ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት ሊባኖስ ውስጥ በየአቅጣጫው የተኩስ እና የፍንዳታ ድምጽ ይሰማል።
የአየር ጥቃቱ የሚያደርሰው ውድመት ስጋት ውስጥ ያጣላቸው ነዋሪዎች ከቤታቸው ውጪ ጎዳና ማደርም ጀምረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራት ዓለም እንደምትለው ከባድ ጥቃት ከሚፈጸምበት የሊባኖስ አካባቢ ወጥታ ባለፈው ቅዳሜ ወደ ዋና ከተማዋ ቤይሩት ገብታ ሐምራ የሚባል ቦታ ተጠልላ ነው ያለችው።
“ቤታችን ፊት ለፊት ነበር የተመታው። መስኮቱ ወዳደቀ። በድንጋጤ ምንም ነገር አልያዝንም። ቅያሪ ልብስ ራሱ አልያዝንም። ዝም ብለን ወጣን” ትለላች።
“የአራት ወር ልጅ አለችኝ። እሷን አንጠልጥዬ ወጣሁ። አሁን ሰው ጋር ተጠግተን ነው ያለነው” ስትልም አክላለች።
ትኖር የነበረው ከሱዳናዊ ባለቤቷ ጋር እንደነበር እና ከፍንዳታው በኋላ ግን ከቤታቸው ወጥተው ሰው ጋር ተጠግተው እንዳሉ ትናገራለች።
“ሰላም ይወርዳል ብለን ጠብቀን ነበር። ሰላም ግን የለም። እየባሰ መጣ። እግዚአብሔር ይጠብቀን” በማለት የተፈጠረባትን ስጋት ገልጻለች – ዓለም።
እየተፈጸመ ያለው ጥቃት በአገሪቱ ያለውን እንቅስቃሴ በማደናቀፉ የሥራ ቦታዎች ዝግ በመሆናቸው የዕለት ጉርስን ለመሸፈን የሚያስችል ሥራ ማግኘት ባለመቻላቸው ችግር ላይ ናቸው።
“ሥራ ቦታ ዝግ ነው። ሥራ ስንፈልግ የለም። የባለቤቴ ጓደኛ ቤት ነው ያለነው። የሚከራይ ቤት አላገኘንም። የሚያስጠጋቸው አጥተው መንገድ ላይ የተኙም አሉ።”
- ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ፡ በእስራኤል የአየር ጥቃት ስር በምትገኘው ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ25 መስከረም 2024
- ጎዳና ማደር የጀመሩት ሊባኖሳዊያን30 መስከረም 2024
- ከኢራን የሚጠበቀው አጸፋ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያንዣበበው ስጋት30 መስከረም 2024
ከአራት ዓመት በፊት የሊባኖስ የሠራተኞች ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ውስጥ በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
ነገር ግን ይህ አሃዝ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው በሊባኖስ ውስጥ ያሉትን የሚያመለክት በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ሕጋዊ ሳይሆኑ በአገሪቱ የሚሠሩ በመኖራቸው ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል።
በሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ፓስፖርት እና ስልክ አስመዝግቡ ሲል ባለፈው ሳምንት መግለጫ አውጥቷል።
እሷ ባትመዘገብም ወደ ኤምባሲው እንደደወለች ዓለም ገልጻ “ይሄ ሁሉ የሚደረገው ለውሸት እና ለማስመሰል ነው እንጂ ስልካችንን አያነሱም። ድምጽ ልከን መልሱልን ስንልም አልመለሱም” ስትል ቅሬታዋን ገልጻለች።
አክላም “እዚህ አገር እኛ ኤምባሲ የለንም። በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ያለነው። ምንም እያገዙን አይደለም። ለራሳቸውም ፈርተው እየተደበቁ ነው” በማለት ሁኔታውን ገልጻለች።
ባለፈው ሳምንት ቢቢሲ በሊባኖስ ስላሉ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ ዘገባ ለመሥራት የኢትዮጵያን ቆንስላ ጽህፈት ቤትን ወክለው እየሠሩ እንደሆነ ከገለጹ ባለሥልጣን ማብራሪያ ለማግኘት ቢሞክርም አዲስ አበባ ያለውን “የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አነጋግሩ” በማለት መረጃ መስጠት ኃላፊነታቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በጦርነቱ ምክንያት ሊባኖስን ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን እንዲመዘገቡ ሰኞ መስከረም 20/2017 ዓ.ም. ባወጣው ማስታወቂያ ጥሪ አቅርቧል።
ቆንስላው እንዳለው ከአገሪቱ የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያኑን ከሊባኖስ “የሚወጡበትን መንገድ ለማመቻቸት” ዝርዝር መረጃቸውን በመስጠት በተዘጋጁ የስልክ ቁጥሮች በኩል እንዲመዘገቡ ወይም በዋትስአፕ በኩል እንዲልኩ ጠይቋል።
“ምናለ አንድ ዳቦ ቢሰጡን?”
“የአራት ወር ልጅ አለችኝ። መንገድ ላይ ምንድን ነው የማበላት? ምንድን ነው የማጠጣት? ምናለ ቢያግዙን? ምናለ አንድ ዳቦ ቢሰጡን? ዳይፐር የለ፣ ወተት የለ . . . የሌላ አገር ዜጋ ለዜጋው እየደረሰ ነው። ለእኛ ማነው የሚደርሰው?” ስትል ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ዓለም ትገልጻለች።
ባለችበት ቦታ ልጅ ያላቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ትናገራለች።
አሁን በተጠለሉበት ቦታ ተኩስ እና ፍንዳታ ባይሰማም “እስከ መቼ የሰው እጅ እየጠበቅን እንኖራለን? እስከ መቼ ሰው ቤት እንቀመጣለን” በማለት ጭንቀቷን ትገልጻለች።
እሷ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ መውጣት ቢፈልጉም በአገሪቱ ከሚገኘው ቆንስላ መሥሪያ ቤት ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።
ባለፈው ሳምንት በቤሩት ሊባኖስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በሊባኖስ እና አካባቢው ያለው የፀጥታ ስጋት እና ውጥረት “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ” መምጣቱን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራው የጥንቃቄ መልዕክት ላይ ገልጿል።
ጥቃት ከተሰነዘረባቸው አካባቢዎች ውጡ የሚል መልዕክት መተላለፉን በማስታወስ “የት ነው የምንወድቀው? ስደት ላይ ነን? መንገድ ላይ ነው የምንተኛው?” ስትል ትጠይቃለች።
ከሊባኖስ መንግሥት በኩል ድጋፍ እንዳልተደረገላቸውም ታክላለች። ባዶ ሆቴል አግኘተው መጠለያ ያደረጉ የአገሬው ዜጎች ቢኖሩም፣ ያ ለስደተኞች የሚታሰብ እንዳልሆነ ትናገራለች።
“ኢትዮጵያውን መንገድ ላይ እየተኙ ነው። በዓይኔ አይቻቸዋለሁ” ትላለች።
ለዘጠኝ ዓመታት በሊባኖስ የኖረችው ዓለም፣ በሊባኖስ ያለው ቀውስ የሚቀጥል ከሆነ ወደ ኢትዮጵያ ከመመለስ ውጪ አማራጭ እንደሌላት አክላለች።
በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃት ሲበረታ አንዳንዶች ወደ ሰሜን ሊባኖስ እየተሰደዱ ነው።
ቢቢሲ በከተማዋ በተዘዋወረባቸው ጊዜያት ሁሉ ሰዎች ባገኙት ተሽከርካሪ እየተንጠላጠሉ ከጦርነቱ አካባቢ በመሸሽ ላይ ነበሩ።
ነዋሪዎችን በየጎዳናው ለመጠለል ተገደዋል።
የጦር ቀጠና በሆነችው ሊባኖስ ከሰኞ ጀምሮ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ታውጇል።
“ከሞትኩም እዚሁ ልሙት”
በደቡባዊ ሊባኖስ፣ ሳይዳ የምትገኘው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት እታገኝ ለቢቢሲ እንደገለጸችው፣ በፍርሃት እየኖሩ ነው።
የጉልበት ህመም እንዳለበት የምትናገረው እታገኝ፣ ጓደኞቿ እየረዷትና እሷም እየሠራች ኑሮን ትገፋ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን “ሁሉም ነገር ተዘግቶ ቤት ቁጭ ብያለሁ” ትላለች።
“የቤት ኪራይም የለም። ቁጭ ብለን ዓይን ዓይን ማየት ነው። በፍርሃት ነው የምንኖረው።”
በዕድሜ እና በጤና እክል ምክንያት ቀላል ሥራ ካልሆነ በስተቀር መሥራት እንደማትችል የምትገልጸው እታገኝ፤ ወደ አገር ቤት ለመመለስም በደቡብ ወሎ የሚገኙት ቤተሰቦቿ በጦርነት ምክንያት በመፈናቀላቸው ተስፋ የሚሰጥ አማራጭ እንደሌላት ታስረዳለች።
ወደ 20 ዓመታት ሊባኖስ እንደቆየች የምትናገረው እታገኝ “ያለው ነገር በሁሉም ቦታ የከፋ ነው” ትላለች።
የተኩስ ድምጽ በቅርብ ርቀት እንደሚሰማቸው እና በፍንዳታ ምክንያት መሬቱ እንደሚንቀጠቀጥ ገልጻለች።
የደቡባዊ ሊባኖስ ነዋሪዎች ወደ ቤይሩት ቢሸሹም፣ ይህ ግን ለእሷ አማራጭ እንዳልሆነ ትናገራለች። “ህመምተኛ ነኝ መሬት መተኛት አልችልም። ሽንት ቤት እንደልቤ መጠቀም አልችልም። ከሞትኩም እዚሁ ልሙት ብዬ ነው ያለሁት” በማለት ያለችበትን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግራለች።
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የጀመረችው ጥቃት ተስፋፍቶ በመዲናዋ ቤይሩት ላይም ያነጣጠረ መሆኑን በመግለጽ፣ በአገሪቱ ውስጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው የሚባል ቦታ እምብዛም እንደሌለ ታክላለች።
“የት እንደሚመታ አይታወቅም። ማለት የሚቻለው እግዚአብሔር ይጠብቀን ብቻ ነው” ትላለች።
በሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ፓስፖርት እና ስልክ አስመዝግቡ ሲል ያለፈው ሳምንት መግለጫ ቢያወጣም፣ እታገኝ በበኩሏ “የትኬት ብር አምጪ ቢለኝ እጄ ላይ ሳንቲም ስለሌለኝ. . . ኤምባሲውም መግለጫ ሲያወጣም ግልጽ አላደረገም። ተመዝገቡ ያለው አገራችን ለማስገባት ይሁን ግልጽ አይደለም። አልተመዘገብኩም” ስትል ያለችበትን ሁኔታ ገልጻለች።
ጥቃት የደረባቸው የደቡብ ሊባኖስ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ቢወጡም ባሉበት የቀሩ እንዳሉም ትናገራለች።
“ምን እንደሚሆን አናውቅም። መሄጃ የለንም። ሦስት ልጆች ‘ማዳሞቻቸው’ [አሠሪዎቻቸው] ውጡ፣ አንፈልጋችሁም ብለዋቸው ከእኔ ጋር ቁጭ ብለዋል” ስትልም አክላለች።
በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ለወራት የዘለቀው የድንበር አካባቢ ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ለይቶለት በርካታ የሌባኖስ አካባቢዎች በእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ጥቃት እየተፈጸመባቸው ነው።
በዚህም ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ደግሞ ነፍሳቸውን ለማዳን ቤታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል ሲሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
በቀጣይ ቀናት የእስራኤል እግረኛ ጦር ወደ ሊባኖስ እንደሚገባ እየተነገረ ሲሆን፣ ይህም ጦርነቱን የበለጠ ሊያባብሰው እንደሚችል ተሰግቷል።