
ከ 5 ሰአት በፊት
ሩዋንዳ ውስጥ በማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቀናት ውስጥ ቢያንስ የስምንት ሰዎችን ሕይወት ማለፉን የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ይህ በጣም ተላላፊ የሆነው በሽታ ከኢቦላ ጋር ተመሳሳይ ነው። ምልክቶቹም ትኩሳት፣ የጡንቻ ህመም፣ ተቅማጥ፣ ማስታወክ እና አንዳንዴም ከፍተኛ የደም መፍሰስ ሲሆን በአጣዳፊ ለሞት ሊያበቃ የሚችል ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማርበርግ በቫይረስ ተይዘው ለሞት ተዳርገዋል። ከሞላ ጎደል ሁሉም የሞቱት አፍሪካ ውስጥ ነው።
የማርበርግ ቫይረስ ምንድን ነው፣ ምን ያህልስ አደገኛ ነው?
የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ የማርበርግ ቫይረስ ከሚያጠቃቸው ሰዎች መካከል በአማካይ ግማሹን ይገድላል። ቀደም ሲል በተከሰቱት የበሽታው ወረርሽኞች ከተያዙት መካከል ከ 24 እስከ 88 በመቶ የሚሆኑትን ታካሚዎች ገድሏል።
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 1967 በጀርመን ማርበርግ እና ፍራንክፈርት እንዲሁም በሰርቢያ ቤልግሬድ በተከሰቱት ወረርሽኞች ሲሆን፣ 31 ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ሰባቱ በበሽታው ምክንያት ለህልፈት ተዳርገዋል።
ወረርሽኙ የተከሰተው ከኡጋንዳ ወደ አውሮፓ በተወሰዱ የአፍሪካ አረንጓዴ ዝንጀሮዎች ምክንያት ነበር።
ከዚያ ወዲህ ግን ቫይረሱ ከሌሎች እንስሳት ጋርም ተያይዟል።

ቫይረሱ በሰዎች መካከል በስፋት የሚሰራጨው የለሊት ወፎች በብዛት ባሉባቸው ዋሻዎች እና የማዕድን ማውጫ ስፍራዎች ውስጥ ለረዥም ጊዜ በቆዩ ሰዎች ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የማርበርግ ቫይረስ በሚከተሉት አገራት ውስጥ ተከስቷል፡-
- ኢኳቶሪያል ጊኒ
- ጋና
- ዲሞክራቲክ ኮንጎ
- ኬንያ
- ደቡብ አፍሪካ
- ኡጋንዳ
- ዚምባቡዌ
እአአ በ 2005 በአንጎላ ወረርሽኙ ተከስቶ ከ300 በላይ ሰዎችን ገድሏል።
በተቀረው ዓለም ግን ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ በማርበርግ ቫይረስ የሞቱት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው። አንደኛው በአውሮፓ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ አሜሪካ ነው።
ሁለቱም ግለሰቦች ኡጋንዳ ውስጥ የሚገኙ ዋሻዎችን ጎብኝተው ነበር ተብሏል።
በርካታ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙት የት ነው?
እንደ ጤና ባለሙያዎች ከሆነ ቫይረሱ በሩዋንዳ መከሰቱ የተረጋገጠው እአአ በመስከረም 2024 መጨረሻ ላይ ነው።
ቫይረሱ በሩዋንዳ ሲገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ ምንጩ እስካሁን አልታወቀም።
የሩዋንዳ ጎረቤት ሆኑት ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ በ2017 እና 2023 የማርበርግ ወረርሽኝ እንደተገኘ ሪፖርት አድርገው ነበር።
ሩዋንዳ ውስጥ በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ 300 ያህል ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው።
በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠባቸው መካከል አንዳንዶቹ የጤና ባለሙያዎች ናቸው።
ሩዋንዳ ወረርሽኙን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ በሚል የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎችን፣ የመመርመሪያ መሳሪያዎችን እና የግል መከላከያ መሳሪያዎችን እየላከ ነው።
የማርበርግ ቫይረስ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?
ቫይረሱ በድንገት ሲጀምር፡
- ትኩሳት
- ከባድ የራስ ምታት
- የጡንቻ ህመም ይኖራል።
ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ ሌሎች ምልክቶች ይከተላሉ፡
- ቀጭን ተቅማጥ
- የሆድ ህመም
- ማቅለሽለሽ
- ማስታወክ
የዓለም ጤና ድርጅት “በዚህ ደረጃ ያሉ የታካሚዎች ገጽታ ‘ሙት-የሚመስሉ’፣ የጎደጎዱ ዓይኖች፣ ስሜት አልባ ፊት እና ከፍተኛ ድካም ያሳያሉ” በማለት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ክፉኛ እንደሚጎዱ አመልክቷል።
ብዙ ሰዎችም ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው ደም ይፈሳቸዋል። አንዳንዶቹ በከፍተኛ ደም መፍሰስ እና በድንጋጤ ምክንያት ምልክቱ በጀመራቸው ከስምንት እስከ ዘጠኝ ቀናት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሕይወታቸው ያልፋል።

የማርበርግ ቫይረስ እንዴት ይተላለፋል?
የአፍሪካ አረንጓዴ ዝንጀሮዎች እና አሳማዎች ቫይረሱን ሊሸከሙት ይችላሉ።
የግብፅ የሌሊት ወፍም ብዙውን ጊዜ ቫይረሱን ትሸከማለች።
በሰዎች መካከል ደግሞ ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች እና በተበከለ የልብስ ንክኪ ይተላለፋል።
ሰዎች ካገገሙ በኋላም ደማቸው ወይም የዘር ፈሳሻቸው ውስጥ ለብዙ ወራት ቫይረሱ ተላላፊ በሚሆንበት ደረጃ ላይ ሆኖ ሊቆይ ይችላል።
እንዴትስ ሊታከም ይችላል?
ምንም እንኳን ሙከራዎች እየተደረጉ ቢሆንም ለቫይረሱ የተለየ ሕክምና ወይም ክትባት የለም።
ለሕክምና የሚያገለግሉ የተለያዩ የደም ውጤቶች፣ መድኃኒት እንዲሁም የበሽታው መከላከያ መንገዶች እየተዘጋጁ ናቸው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አመልክቷል።
ዶክተሮች ሆስፒታል ለሚገኙ ህሙማን ብዙ ፈሳሽ በመስጠት እና የፈሰሰውን ደም በመተካት ህመሙን ማስታገስ ይችላሉ ይሆናል።
እንዴት በቁጥጥር ስር ሊውል ይችላል?
ጋቪ የተሰኘ ዓለም አቀፍ የጤና ተቋም እንዳለው አፍሪካ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከጫካ በአደን የሚገኝ ሥጋን ከመመገብ መቆጠብ አለባቸው።
እንዲሁም ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ከአሳማዎች ጋር ያላቸውን ንክኪ ማስወገድ እንዳለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት መክሯል።
ቫይረሱ የያዛቸው ወንዶች የህመሙ ምልክቶች ከታዩ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ወይም የዘር ፍሬያቸው ሁለት ጊዜ ቫይረሱ እንደሌለበት እስኪረጋገጥ ድረስ በግንኙነት ወቅት ኮንዶም መጠቀም ይኖርባቸዋል።
በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን የሚቀብሩ ሰዎችም አስከሬኑን ከመንካት መቆጠብ አለባቸው።
