

ለወባ ታማሚዎች ሕክምና ሲደረግ
ዜና በፀጥታና በበጀት እጥረት ምክንያት ወረርሽኞችን መቆጣጠር አዳጋች ሆኗል ተባለ
- በወባ 5.9 ሚሊዮን ሰዎች ሲያዙ 1,023 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል
በበጀት እጥረትና በተራዘሙ ግጭቶች የእንቅስቃሴ ገደብና ተያያዥ ተግዳሮቶች ምክንያት የወባ፣ የኮሌራና የኩፍኝ ወረርሽኞች እየተባባሱ መሆናቸው ተገለጸ፡፡ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን፣ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጧቸው የዚህ ሳምንት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ5.9 ሚሊዮን በላይ የወጣ ወረርሽኝ ተጠቂዎች መመዝገባቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ 1,023 ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡
የወባ ተጠቂዎች ቁጥር በባለፉት አራት ወራት በእጥፍ መጨመሩ ተሰምቷል፡፡ ከጠቅላላው የወባ ተጠቂዎች ውስጥ ግማሹ (50 በመቶ) በኦሮሚያ፣ 17 በመቶ በአማራ፣ ዘጠኝ ከመቶ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ስድስት በመቶ በደቡብ ኢትዮጵያና ቀሪው አምስት ከመቶ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ተመዝግቧል፡፡
እስካለፈው ሳምንት ድረስ 25,000 ያህል ሰዎች በኮሌራ መያዛቸውን፣ 234 ሰዎች መሞታቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ኮሌራ በብዛት በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሲዳማ ክልሎች እየተስፋፋ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በተለይ በአማራ ክልል ባለው ተገማች ያልሆነ የፀጥታ ሁኔታ የተነሳ ሕይወት አድን ሥራዎችን መሥራት አልተቻለም፡፡ በግጭቶች ምክንያት በክልሉ ያሉ የሕክምና መስጫ ተቋማትም መውደማቸውን ገልጿል፡፡ ሁኔታዎች ባሉበት ከቀጠሉ የኩፍኝን ጨምሮ ወረርሽኞች ሊባባሱ እንደሚችሉ ተንብየዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በበኩሉ በአማራና በኦሮሚያ በተለይ በጉጂ፣ ቦረናና ሌሎች አካባቢዎች በፀጥታ ምክንያት የሕይወት አድን ሥራዎችን ማከናወን እንዳልተቻለ ገልጿል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ካለው አሥጊ የፀጥታ ሁኔታ በተጨማሪ በክልሎች ተጓጉዞ የክትባት መድኃኒት ለማድረስ የተሽከርካሪ እጥረት መኖሩን፣ ወሳኝ የሆኑ መድኃኒቶች እጥረት እንዳለ፣ እንዲሁም የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት መኖሩን ኢንስቲትዩቱ አትቷል፡፡ በተለይ በክልሎች የውኃ ማከሚያ መድኃኒቶች እጥረት መፈጠሩንም ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በወረርሽኞች የተያዙ 6.7 ሚሊዮን ሰዎች በ980 ወረዳዎች ውስጥ እንዳሉ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ በአጠቃላይ ከ187 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን፣ እስካሁን የተገኘው ግን 27 ሚሊዮን ዶላር (14.4 በመቶ) ብቻ ነው ብሏል፡፡
