October 4, 2024 – Konjit Sitotaw

የአማራ ፋኖ በጎጃም የዞን ዋና ከተማ ወደሆነችው ፍኖተ ሰላም ዘልቀው ገብተዋል። የፋኖ ኃይሎች መከላከያ እና አድማ ብተናን ከከተማዋ አስወጥተው ወደካምፕ እንዲገባ አድርገውታል ተብሏል። በዚህም በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ፋኖዎች እንደሚንቀሳቀሱ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም ፋኖዎች ሺንዲ ወንበርማም ይዘው አድረዋል!
የፋኖ ኃይሎች ማንኩሳ ከተማ ገብተዋል። የዞን ከተማ የሆነችው ፍኖተ ሰላም ውስጥ ሁሉም እንቅስቃሴ ቆሟል (ትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም፣ ሱቆችና ሆቴሎች ዝግ ናቸው፣ የሰዎች እንቅስቃሴም ተገድቧል)። ፍኖተ ሰላም ከተማ አቅራቢያ ወደ ገራይ መስመር ከባድ ውጊያ አለ። ቀደም ሲል የፋኖ አደረጃጀቶች ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ በአማራ ክልሉ በርካታ አካባቢዎች መንገዶች ዝግ መሆናቸው ታውቋል።
የአማራ ፋኖ በጎጃም ጅጋ ከተማ ገብተዋል። የአድማ ብተናና የመከላከያን ካምፕ አካባቢ ከጠዋት 2 ሰዓት የጀመረ ውጊያ ቀጥሏል; በቡሬ ወረዳ በቁጭ ከተማም ከባድ ውጊያ እየተደረገ ነው። በተለይ ቡሬ በር፣ ጃሞ እና ሽንዲ መወጫ ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ቡሬ ከተማ ደግሞ እንቅስቃሴ ተገድቧል።
ብልጽግና የሚያደርገው ነገር ለሰሚውም ግራ ነው። ሰሞኑን አማራ ክልል ከተሞች ላይ የሚፈጽመው የእስር ዘመቻ ኮታ ተጥሎ “ይህን ያህል ሰው ከዚህ ከተማ ማሰር አለብን” ተብሎ እየተፈጸመ ያለ ነው። የየአካባቢው አፋኞች አምጡ የተባሉትን ኮታ ለመሙላት በወረቀት ዝርዝር አውጥተው ያድናሉ። በዚህ መንገድ በየከተማው በርካታ ሰው ታስሯል።
ለምሳሌ ሰሜን ወሎ ላሊበላ ከተማ የታሰሩት አብዛኞቹ በአካባቢው ተሰሚነት ያላቸውና፣ ብልጽግና የሰላም ኮንፈረስ እያለ ባዘጋጃቸው መድረኮች የተናገሩ፣ ግድያና አፈሳ መፍትሔ አያመጣም በሚል ሀሳባቸውን የገለጹ ናቸው። የተጣላ አስታራቂ ሽማግሌዎች ናቸው በብዛት የታሰሩት። ታሳሪዎች ሌሊት ከከተማው ወደአልታወቀ ቦታ ተወስደዋል ተብሏል።
ደሴ እና ወልዲያ ደግሞ በርካታ የኦርቶዶክስ አገልጋዮች የታሰሩባቸው ከተሞች ናቸው። ባሕር ዳር መሉዓለም የባህል ማዕከል የእስረኛ ማከፋፈያ ሆኗል ሲሉም ምንጮች ገልጸዋል። በከተማዋ የሚያዙ ሰዎች ሙሉዓለም ከተወሰዱ በኋላ ወደ ጣቢያዎች ይበተናሉ። ብዙ ሰዎች ከታሰሩባቸው ጣቢያዎች መካከል ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ዋናው ሆኗል።
የተሰጣቸውን ታሳሪ ኮታ ያላሟሉ አፋኞች ግምገማ ይደረግባቸዋል ተብሏል።
