ሲሳይ ሳህሉ

October 6, 2024

ቆይታ

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲን ለዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ 15 ዓመታት በፊት መንግሥት የግብርና ስትራቴጂዎችን ለመደገፍ፣ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የዘርፉን ዕድገት ማሳለጥ ራል ብሎ ቋቋመውን ተቋም እንዲመሩ ከመሾማቸው በፊት፣ በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ልማት ዘርፍን በመምራት ሚኒስቴር ደኤታ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ተቋምን በመምራት የኦክስፋም ቀጣናዊ ዳይሬክተር በመሆን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ አባልና በበርካታ ተቋማት በተለያዩ ደረጃ ላፊነትና በባለሙያነት አገልግለዋል፡፡ ማንደፍሮ ንጉሤ (/ግብርና ትራንስፎርሜሽን ደትንና አጠቃላይ የኢትዮጵያን ግብርና በተመለከተ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡– የኢትዮ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም እንዴት ተመምን እየ ነው?

ማንደፍሮ (/) አጀማመሩ የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነውን የግብርና ዘርፍ ምን ዓይነት ችግር አንቆ እንደያዘው ችግሩን አጥንታችሁ አቅርቡልኝ ተብሎ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስተዳደር ጊዜ ነበር፡፡ ጥናቱን ደግሞ ዓለም ላይ አሉ በተባሉ የግብርና እና የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተሰባስበው አካሄዱ፡፡ በጥናቱ ሰባት ምክረ ሐሳቦች ቀረቡ፡፡ በቀረቡት ምክረ ሐሳቦች መሠረት ግብርናውን እንዴት እናዘምነው የሚለው ማጠንጠኛ ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር ወደ ላይ ስንሄድ አቅም አለ፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ሲሄድ ሰው ያለውና ሥራው የሚከናወነው ታችኛው ቀበሌ በመሆኑ ትልቅ አቅም መገንባት ያለበት እዚህ ነው፡፡ መጀመሪያ የልማት ሠራተኞችን አቅም መገንባት፣ የእነሱ አቅም ሲገነባ የአርሶ አደሩን አቅምና ክህሎት በቀጥታ ማሳደግ፡፡ በቀበሌ ደረጃ ደግሞ ተቋማት መፍጠር፣ የገበሬ ማሠልጠኛ ማዕከላት ማቋቋም፣ በተዋረድ ከላይ ወደ ታችና ከታች ወደ ላይ የሚያገናኝና ግንኙነትን የሚያሳልጥ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ እንዲቀየስ ተደረገ፡፡ ከዚያ ደግሞ ሥራው የአንድ ጊዜ ብቻ እንዳይሆን በጽሑፍ እንዲታገዝና እየተሻሻለ ሊሄድ የሚችል የግብርና ኤክስቴንሽን ስትራቴጂ እንዲነደፍ ተደረገ፡፡ ምርምር የሚሠሩ ተቋማትና የምርምር ውጤት ወደ አርሶ አደር የሚሄዱበት፣ የምርምር ኤክስቴንሽንና አርሶ አደሮቹን የሚያገናኝ ድልድይ እንዲሆን የሚረዳ ተቋም እንዲቋቋም ተብሎ ሰባት ምክረ ሐሳቦች በጽሑፍ በወቅቱ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቀረበላቸው፡፡ ይህ ሲባል በወቅቱ የነበረውን የግብርና ሚኒስቴርና ከዚያ ጋር ተያይዞ እስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅር በመመልከት ይህንን ትልምና ምክረ ሐሳብ መሬት ማውረድ ይቻላል? ወይስ አይቻልም? በሚል ውይይት ተደርጎ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ እ.ኤ.አ. በ2010 ተቋቋመ፡፡ በሚቋቋምበት ጊዜ የተሰጠው ኃላፊነት የግብርናውን ዘርፍ አንቆ የያዘውን ችግር አጥንቶ እንዲያመጣ፣ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያፈላልግና የፈጻሚዎችን አቅም እንዲገነባ የሚሉ ሁለት ሥራዎች ተሰጡት፡፡ ይህን እየሠራ እያለ ይህን ችግር ለመፍታት በጽሑፍ ሐሳቦች ከቀረቡ በኋላ፣ ሁለት ተጨማሪ ነገሮች ታክለውበት የመጀመሪያው ደንብ ማሻሻያ ተደረገበት፡፡ በማሻሻያው ተቋሙ ተሰጥቶት ከነበረው ሁለት ኃላፊነት ወደ አራት ከፍ ተደርገ፣ በተለይም በወረቀት ምክረ ሐሳብ የማቅረብ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ ምክረ ሐሳቡን አብሮ ፈጻሚ እንዲሆን የሚያደርገው ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ አሁን በሰፊው ይህ ተቋም የሚታወቅበት የኩታ ገጠም እርሻ ያን ጊዜ በተሰጠው ተጨማሪ ኃላፊነት መሠረት ነው፡፡ መጀመሪያ ሲቋቋም ሰነዱ ላይ ከ20 እስከ 25 ዓመታት ጊዜ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕውን አድርጎ የሚከስም ወይም ወደ ሌላ የሚቀየር መሥሪያ ቤት ተደርጎ ነው የተቋቋመው፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድም ይህን ነው የሚያሳየው፡፡ ብዙ አገሮች እንደ ኮሪያ፣ ቬትናምና ታይላንድ ለ20 ዓመት ግብርናን ትራንስፎርም አድርገዋልና ያንን ልምድ ተወስዶ እስከ 25 ዓመታት የሚፈጅ ጊዜ ይወስዳል የሚል ዕቅድ ተይዞ ነው የተቋቋመው፡፡ ኤጀንት ሆኖ ለውጥ ለማሸጋገር የሚያገለግል እንጂ ሁሌ መሥሪያ ቤት ሆኖ ሁሌም የሚቀጥል አይደለም፡፡ 

ሪፖርተር– ተቋሙ ከተመሠረተ 15 ዓመታት እየተቆጠሩ ነው ጉዟችሁ እንዴት ነበርበታቀደው ልክ እየተራመዳችሁ ነው?     

ማንደፍሮ (/)– አሁን 13ኛ ዓመት አካባቢ ነው ያለነው፣ በ13 ዓመታት ውስጥ ትራስፎርሜሽኑን ስንመለከት አምስት ምዕራፎች አሉት፡፡ ከአምስቱ ምዕራፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ውስጥ ነው አሁን ያለነው፡፡ የመንገዳችን አጋማሽ ላይ ነን ማለት ነው፡፡ በቀሩት 12 እና 13 ዓመታት ውስጥ ትራንስፎርሜሽኑን ዕውን ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን ደግሞ ለግብርና በተሰጠው ትኩረትና በሚደረገው ኢንቨስትመንት የታቀደውን ትራንስፎርሜሽን ዕውን ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡  

ሪፖርተር፡ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ሲባል በአርሶ አደሩና በአጠቃላይ በምግብ አቅርቦት ረገድ እንዲመጣ የሚጠበቀው ለውጥ ምንድነው?

ማንደፍሮ (/)– የግብርና ትራንስፎርሜሽን በአጭሩ ዕውን ሆነ የሚባለው አርሶና አምርቶ ከመመገብ፣ አርሶና አምርቶ ወደ መሸጥ መሸጋገርን ትልም ስለያዘ ነው፡፡ በቁጥር ስናስቀምጠው አሁን እስከ 25 በመቶ ከሆነ ወደ ገበያ የሚወስደው ትራንስፎርሜሽን አይባልም፡፡ ትራንስፎርሜሽን የሚባለው አርስ አደሩ ከሚያመርተው 75 በመቶና ከዚያ በላይ ምርት የሚሰጥ ከሆነ ነው፡፡ አንድ አራተኛውን ለራሱ አድርጎ ሦስት አራተኛውን ለገበያ ማቅረብ ከቻለ አንድ አርሶ አደር የሸማቹንና ወደ ውጭ ገበያ የሚላከውን ፍላጎት ማርካት የሚችል አቅም ላይ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ በንግድ ስታየው ከተቋቋመበት ጀምሮ በ20 ዓመታት ውስጥ ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ ነው፡፡ ይህ ማለት በሔክታር አሥር ኩንታል ሲያመርት የነበረው በአሥረኛው ዓመት ላይ 20 ኩንታል፣ በ20ኛው ዓመት ላይ 40 ኩንታል የሚያመርት ግብርና ማለት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡ በገጠሩ አካባቢ አርሶ አደሩ የሚያመርተውን ነጭ ጤፍ ሸጦ ሌላ ዝቅ ያለ ምርት የሚገዛ በጉን ወይም በሬውን ሸጦ ባቄላ ወይም ገብስ የሚገዛ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ካመረተው ጤፍ ውስጥ 75 በመቶውን ሸጦ ባቄላ ገብስ ወይም ሌላ ቢገዛ ከእናንተ የትራንስፎርሜሽን ትልም ጋር እንዴት ይሄዳልወደ ገበያ ይዞት የሚወጣው ከምርት ማደግ ጋር የተገናኘ ነገር ሳይሆን ለማቀያየር እንጂ፡፡

ማንደፍሮ (/)– ሁለቱ የተለያዩ ናቸው፡፡ አምርቶ ትርፉን ለገበያ ማቅረብና የሚባለውን ሥነ ምግብ አዋቅሮ መመገብ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ይህ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ሳይሆን በምግብ ሲስተም ትራንስፎርሜሽን ነው የሚመጣው፡፡ ጤፍ ብቻ የሚያመርት አካባቢ ከጤፍ የሚያገኘው ካርቦኃይድሬት ከሆነ፣ ከጤፍ ተጨማሪ ፕሮቲንና የቅባት እህሎች በአጠቃላይ የምግብ ስብጥሩ ምን መምሰል አለበት በሚል በምግብ ትራንስፎርሜሽን የሚሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡ ይህ ከእናንተ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ውስጥ ተካቶ ይሠራበታል

ማንደፍሮ (/)– በጥቂቱ በግብርና ውስጥ የሚሠራ በአመዛኙ ግን ከጤና ጋር ተያይዞ የሚሠራ ነው፡፡ አሁን ባለው ሥርዓት የምግብ ሽግግር ሁለቱ የጤናና የግብርና መሥሪያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሴክሬታሪያት ሆኖ እንዲሠሩት ይደረጋል፡፡ ግብርናን ትራንስፎርም ስናደርግ የምግብ ሥርዓቱን ትራንስፎርም ካላደረግን ጤናማ የሆነ አርሶ አደርና ዜጋ ለመፍጠር ስለሚያስቸግር ሁለቱን አስተሳስሮ መሄድ ያስፈልጋል የሚል ትልም ነው የምንሠራው፡፡ አሁን የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ከጀመርን ሁለት ዓመታችን ነው፡፡ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ከጀመርን ደግሞ 13 ዓመታችን ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡– የኢትዮጵያ የአመጋገብ ሥርዓት መለወጥ የለበትም ብለው ያስባሉ? አሁን ያለው የምግብ ስብጥር ተመሳሳይ መሆኑ አዳዲስ የምግብ ዓይነቶችን ወደ ማዕድ ማስገባት የሚቻለው እንዴት ነውየአንዳንድ አገሮች የአመጋገብ ሥርዓት በአጥፍ የተሻለ ነው ይባላል፡፡ ለአብነት የቻይና ይጠቀሳል፡፡

ማንደፍሮ (/)– ትልቁ ነገር የቻይና ወይም የሌላ አገርና የኢትዮጵያ አመጋገብ ባህልና ልምድ ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ከእምነት፣ ከአስተዳደግ፣ ከትምህርትና ከችግርም ጋር ይያያዛል፡፡ ቻይናዎች በአመዛኙ የሚበሉት ቅጠላ ቅጠል፣ ሥራ ሥር ወይም ጥራጥሬ ነው፡፡ የእነሱ ከእኛ በእጅጉ የተለየ የበዛ የምግብ ስብጥርን የያዘ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ለሥነ ምግብ ሥርዓት ብለው ሳይሆን የጀመሩት በችግር ነው፣ ነገር ግን መጨረሻ  ወደ ተሻለ የአመጋገብ ሥርዓት አማራጭ ቀይረውታል፡፡ የእኛ የምግብ ሥርዓት ባህልና ልምድ አብዛኛውን ጊዜ ካመረትነው ምርት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የንግድ ሥርዓታችን በጣም የተስፋፋ አይደለም፡፡ ሰው የሚበላውን ሁሉ እንዲያመርት ተደርጎ ነው በአዕምሮም በወላጆቻችንም በትምህርትም የተቀረፀውና እየወረስን የመጣነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች ራስን የመቻልና አምርቶ የመጠቀም እንጂ በልዩ ሁኔታ ስፔሻላይዝ አድርጎ እኔ የምመገበውን ተመግቤ የማልመገበበውን ሸጬ ከሌሎች ደግሞ ገዝቼ በሚል ዕሳቤ በቢዝነስና በኢንተርፕራይዝ መልክ አይደለም ግብርና የሚታየው፡፡ ያደገው ግብርና የሚታየው አርሶ ራስንና ቤተሰብን መመገብ በሚል ዕሳቤ ነው፡፡ አሁን ትራንስፎርሜሽን ስንል ግብርናን እንደ ማንኛውም ኢንዱስትሪ የራሱ ግብዓት ሒደትና ምርት ተጠቅሞ ወደ ቢስነስ የመቀየር ሒደት መፍጠርን ነው፡፡ እርሻን እንደ ቢዝነስ ስትቆጥር በአንድ ሔክታር 100 ሺሕ ኩንታል የምታገኝ ከሆነ ለ200 ሺሕ ኩንታል መሄድ አለብህ የሚል አመለካከት መፈጠር አለበት፡፡ ነገር ግን የዚህን ዓይነት አስተሳሰብ ለውጥ ስላልጨረስን በዚህ የትራንስፎርሜሽን ሒደት በዚያ መንገድ መቀጠል አለበት የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል የአመጋገብ ሥርዓታችን በዘመናዊና ሳይንሳዊ ትምህርት ሰው በልቶ ይሄዳል ወይም የተወሰነ የሚበላ ነገር ቋጥሮ ይመጣል፣ የገጠሩ ቂጣ ወይም ቆሎ ይዞ በመሄድ ዓይነት የተቃኘ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በትምህርት ቤት የምርት ንጥረ ነገር የተሟላለት አመጋገብ ሥርዓት ተማሪዎች እንዲለምዱ የማድረግ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ያ ማለት ተማሪዎች ቁርስ ምሳና ራት የሚበሉትን በመለያየት ሳይንሳዊ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓትን ማምጣት እንፈልጋለን፡፡ የምንሠራውም ለዚህ ነው፡፡ ሁለተኛ አሁን የተመጣጠነ ምግብ ወተት፣ እንቁላል፣ ሥጋ መመገብ አለብን ብለህ ብታስቀምጥ ስንቱ ይህን ማግኘት ይችላል ስትል ጉዳዩ ከዕድገትና ከአቅም ጋር የሚመጣ ነው፡፡ ስለዚህ የጀመርነውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕውን ስናደርግ ኢኮኖሚውም የዳበረና ያደገ የገጠር ማኅበረሰብ መፍጠር፣ ያ ሲያድግ ደግሞ ከሥልጣኔ ጋር የተመጣጠነ ምግብ አብሮ ይመጣልና ይህንን በሁለተኛው የግብርና ትራንስፎርሜሽን እናመጣለን፡፡

ሪፖርተር፡– የግብርና ትራንስፎርሜሽንና አርሶ አደሩ ሲወርድ ሲዋረድ ይዞት የመጣውን አገር በቀል ዕውቀት እንዴት  ታዋህዱታላችሁ?  ኤክስቴ ራተኞችና አርሶ አደሩ ይጣጣማሉ?

ማንደፍሮ (/)– ሁለቱም አይቃረኑም፡፡ የሚያቃርኑዋቸው ሰዎች ናቸው፡፡ አቅም ያለው ኤክስቴሽን ከሆነ አገር በቀልና ነባር የሆነውን ዕውቀት ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር በማድረግ የተሻለ ውጤት እንዲያገኙ ለአርሶ አደሩ ምክረ ሐሳብ መስጠት አለበት፡፡ እኔ የተማርኩበትን ብቻ ነው የማሠለጥነው የምትል ከሆነና አርሶ አደሩ በልምድና በዕውቀት ይዞት የመጣውን የምትረሳ ከሆነ መተማመንን ይሸረሽራል፣ ያለህን ዕውቀት ወደ መጠራጠር ይሄዳል፡፡ ስለዚህ መታየት ያለበት ባለሙያ ወደ ሥራ ሲገባ አርሶ አደሩ የነበረውን ዕውቀት ከዘመኑ ጋር አጣጥሞ ይሄዳል፣ አይሄድም የሚለውን በመያዝ ከነባር ዕውቀቱ ላይ የተሻለ ዕውቀት እየገነባህ መሄድ እንጂ፣ የሚጠቅመው ዘመናዊ ብቻ ነባሩና የአገር በቀሉ ዕውቀት አይጠቅምም የሚል ነገር ይዘህ የምትሄድ ከሆነ የትም አያደርስህም፡፡  

ሪፖርተር– አዲሱ የግብርና ፖሊሲ ምን ላይ ነው

ማንደፍሮ (/)– የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በ2016 ሚያዝያ ነው የፀደቀው፡፡ ፖሊሲው አሥር የሚሆኑ ምዕራፍች አሉት፣ ፖሊሲው እስካሁን የነበሩ እንቅፋቶች ማሻሻያ ተብለው በዝርዝር ቀርቧል፡፡ ለምሳሌ መሬትን በተመለከተ አጠቃቀሙ፣ አስተዳደሩ፣ መሬትን ተጠቅመህ የምታከናውነው ሥራና የምርምር ኤክስቴንሽን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አካቷል፡፡ መሬትን እንደ ማሳያ ስንወስድ የመሬት አጠቃቀም ስንል ምን ማለት እንደሆነ ያነሳል፡፡ ወደ ገጠር በምትሄድበት ጊዜ አርሶ አደሮች መሬት ከመሻማት የተነሳ መታረስ የማይገባውን ሁሉ እየሟጠጡ ያርሳሉ፡፡ ስለዚህ ፖሊሲው መታረስ ያለበት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለውን ያነሳል፡፡ ሁለተኛ ለግብርና ልማት የምታውለው ለም አፈር ያለበት ቦታ ላይ ሕንፃ ኢንዱስትሪ ይገነባል፣ ስለዚህ ይህንንም ያስተካክልና ያስቀምጣል፡፡ ለግብርና፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለደን በሚል ለይቶ በማስቀመጥ የመሬት አያያዝና አጠቃቀምን ተለይቶ ተቀምጧል፡፡ መሬት የግል አይደለም የመንግሥትና የሕዝብ ነው፡፡ እንደ ግል ንብረት አይታይም የሚጠቀመው አካል እንደ ንብረት አስይዞ ሊበደር አይችልም፡፡ ስለዚህ በፖሊሲው መሬቱን አስይዞ መበደር እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡ መስፈርቱ የሚሆነው የሚጠቅመው አካል ሰርተፊኬት ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ሰርተፊኬት ገንዘብ ተበድሮ ግብዓት መግዛትና ማልማት እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡

ሪፖርተር– በግብርናው ውስጥ ያለው የካፒታል እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ግብርናው ውስጥ ያለው ካፒታል ይኼ ነው ተብሎ ሲጠቀስ አይደመጥም፡፡ ዘርፉ የሚፈጥረው የሥራ ዕድል እንዴት ይታያል?

ማንደፍሮ (/)– የካፒታል እንቅስቃሴና የሥራ ዕድል በሁለት መንገድ እንየው፡፡ ባአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ላይ መሠረት ያደረገ ነው ስንል ግብርና ላይ ሚዛኑን የደፋ አገራዊ ምርት አለን፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? በግብርናው ውስጥ ያለው ካፒታል እንዴት አድርገን ስናንቀሳቅሰው ነው ሌላ ገንዘብ የሚፈጥረው ስትል ዋነኛ ጉዳይ የሚሆነው፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ባንክ ሥርዓትን ስትመለከትና ባንኮቹ ገጠር ላይ ምን ያህል ተደራሾች ናቸው ስትል ምንም የሉም ማለት ትችላለህ፡፡ ባለመኖራቸው ሰው የግብርና ውጤቶችን ሰብልም ይሁን እንስሳ፣ ወይም ደግሞ ዛፎችን ሸጦ የሚያገኘውን ገንዘብ ሳጥን ውስጥ ነው የሚያስቀምጠው፡፡ ያ ገንዘብ ተንቀሳቅሶ ሌላ ገንዘብ ሳይወልድ እዚያው የሚቀመጥ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ገንዘብ በባህሪው ሌላ ገንዘብ ካልፈጠረ እየሠራህ ትርፍ ካለገኘህበት በቀር ዋጋው እየቀነሰ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ ገጠር ያለውን የገንዘብ ክምችት ወደ ካፒታልና ወደ ኢንቨስትመንት ቀይረን ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያመጣ እያደረግን አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ይጠቅማል ተብሎ የሚጠበቀው የግብርና ባንክ ማቋቋምን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡ የግብርና ባንክ መመሥረት ዕሳቤ ምን ላይ ነው?

ማንደፍሮ (/)– ይህ ባንክ መሠረቱ ገጠር ይሆንና የተከማቸው ጥሬ ገንዘብ እየተሰበሰበ ወደ ኢንቨስትመንት እየተቀየረ ለብድርና ለንግድ ይውላል፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የአግሮ ኢንዱስትሪና ንግድ እንዲስፋፋ የምናደርግበት አንድ የግብርና ፖሊሲው አቅጣጫ ከአማራጭ የግብርና ፋይናንስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን እንግዲህ ፖሊሲው ከፀደቀ ስድስት ወራት ሆኖታል፣ በቀጣይ ለፖሊሲው ወደ 200 የሚደርሱ አዋጆች፣ ደንብና መመርያዎች ይወጡለታል፡፡ በዕቅዳችን ከሄድን ሥራው በስድስት ዓመት ይጠናቀቃል፡፡ አዋጅ፣ ደንብና መመርያ እስኪወጣና የግብርና ባንክ እስከምናቋቋም አሁን ያሉት የንግድ ባንኮች 80 በመቶ ሀብታቸው አርሶ አደሩ ውስጥ ነው ያለው፡፡ በዚህ ሒደት እኛ ባንኩን እስከምናቋቁም እነዚህ ባንኮች ለገጠሩ ሕዝብ በኤሌክትሪክ፣ በኢንተርኔት በሞባይልና በሌሎች አማራጮች ተደራሽነታቸውን ይጨምራሉ የሚል የማነቃቂያ ሥልታችን ነው፡፡ ይህ የእኛ እንቅስቃሴ በንግድ ባንኮች ላይ ትልቅ ግፊት ያደርጋል የሚል እምነት አለን፡፡ ስንመለከት ሥራ እፈጥራሁ ብለህ አይደለም ሥራን የምትፈጥረው፣ ሥራ የሚፈጠረው በልማት ነው፡፡ አሁን በዚህ ሁኔታ አርሶ አደሮች ትርፍ አምርተው ወደ ገበያ ሲቀርብ፣ ከአርሶ አደሮች ሰብስቦ ወደ ኢንዱስትሪው የሚያደርስ፣ ወደ ውጭ ገበያ የሚልክና፣ አብሮ ከሰንሰለቱ ጋር ተያይዞ ነው ሥራ እየተፈጠረ የሚሄደው፡፡ በተሽከርካሪ የሚጭንና የሚያወርድ፣ በሚቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያን ከኢንዱስትሪ ከወጣ በኋላ በንግድ ማዕከላትና ሸማቾች ምርቱ ሲሄድ ባለው ሒደት ሥራ እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ ይህ ማለት ከግብይት አንስቶ ሸማቹ እጅ እስኪደርስ ባለው የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠርን እንሄዳለን፡፡ አደይ ወይም ‹‹Agriculture-focused Dignified Employment for Youth in Ethiopia (“ADEY”)›› በምንለው ሥርዓት ደግሞ ሥራ ፈጠራ ሳይሆን የሰዎች ሰብዕና፣ ክብርና ልዕልና ያለው ሥራ መፍጠር የምንለው ሒደት አለ፡፡ ይህን ሥራ በምንፈጥርበት ጊዜ ካለው የእሴት ስንሰለቱ ውስጥ አርሶ አደሮች የማይሠሩት፣ ነገር ግን ወጣቶች የሚሠሩት ከባቢ የቱ ላይ ነው በሚል የተያዘ ዕቅድ ነው፡፡ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ስንል ምርጥ ዘር ማብዛት፣ ማበጠርና ማሸግ ይፈልጋል፡፡ አርሶ አደሩ ዘንድ ማድረስ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ እሴት ሰንሰለት ጋር የተያያዘ የሥራ ዕድል ውስጥ ተዋንያን ሆነው ለሚሠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ነው፡፡ አደይ ለገጠር ማኅበረሰብና ለገጠር ወጣቶች የሚውል የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው፡፡

ወደ እንስሳት ግብርና ስትሄድ ደግሞ ለምሳሌ አሁን የገጠርም ሆነ የከተማው ነዋሪ የሚመገበው የዶሮ፣ የሥጋና የእንቁላል መጠንን በማየት የዶሮ ዕርባታ ብናስፋፋና የዶሮ ሥጋ ወደ ገበያ ብናስገባ በሒደቱ በርካታ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን የሚል ነው፡፡ ወጣቶችን አደራጅተን ዶሮ እንዲያረቡ ብናደርግ በዕርባታ ሒደቱ እንቁላል ይሸጣል፣ ዶሮዎቹም ይሸጣሉ፡፡ ስለዚህ የሚያረባ አንድ ቡድን አለ፡፡ ሌላው ቡድን ደግሞ የረባውን ዶሮና የተጣለውን እንቁላል ወስዶ ለሚሸጥ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ ከእነዚህ ላይ ደግሞ ዶሮና እንቁላል ገዝቶ እየጠበሰ በየትኛውም ቦታ ላይ ለሸማቹ ለሚያቀርብ ወጣት የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ አምራቾች ደግሞ የራሳቸው የሆነ ጫጩት የላቸውም፡፡ ይህን ጫጩት የሚያቀርብ የጫጩት ማምረቻ ማሸን ያለውና ለዶሮ መኖ የሚያመርቱ ወጣቶች ይደራጃሉ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የሚፈጠረውን ሥራ ዕቅድ ውስጥ በማስገባት በአምስት ዓመት ውስጥ ወደ 680 ሺሕ የሚደርሱ የሥራ ዕድሎችን እንፈጥራለን የሚል ዕቅድ አለ፡፡ ከጀመርነው ግማሽ ዓመት ሆኖናል ወደ 50 ሺሕ ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥረናል፡፡ በዚህ ፍጥነት ከሄድን ከዚህ የላቀ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን የሚል ዕቅድ ይዘን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ በሌላ መንገድ በግብርና ሜካናይዜሽን ማዕከላት ወጣቶችን የሚያሠለጥኑ አሉ፡፡ እነዚህ ሠልጣኞች ትራክተር፣ ኮምባይነር፣ ማሽነሪ የገዛ ሰው ጋ ሄደው ተቀጥረው እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ አሁን የሾፌር ማሠልጠኛ አለ፡፡ ነገር ግን የእርሻ ማሽን ማሠልጠኛ የለም፡፡ እነዚህን ማሠልጠኛዎች በየክልሉ አቋቁመናል፣ በዚህ ሒደት በየክልሉ ሥራ እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ ሌላው ደግሞ የግብርና ግብዓት የሚባሉትን ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን ወይም ኬሚካልን የሚያሠራጩ ወደ 325 ሱቆችን በየወረዳው ፈጥረናል፡፡ በእነዚህ ሱቆች ተቀጥረው የሚሠሩ በትምህርት የተደገፈ ዕውቀት ያላቸው የሠለጠኑ ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህን በምሳሌነት አነሳሁልህ እንጂ አሁን ከጠቀስኩልህ ቁጥር በላይ በሚሊዮን የሚቆጠር የሥራ ዕድል የመፍጠር ትልም አለን፡፡ 

ሪፖርተር፡– የኢትዮጵያ ግብርና 85 በመቶውን ይሸፍናል ተብሎ ለረዥም ጊዜ ሲነገር የነበረ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ገበሬ በበሬ እያረሰ የተቆጠረ መረጃ ነው፡፡ አሁን ላይ መረጃ ተሻሽሎ አርሶ አደሩ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ሕይወት አብሮ እየተቀየረ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚህ ሒደት የገጠሩ ሕይወት ምን ያህል ተለወጠ?

ማንደፍሮ (/) እ.ኤ.አ. በ2022 ባለው መረጃ መሠረት 75 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ግብርና ላይ ነው ያለው፡፡ ይህ እየቀነሰ እንዲሄድ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን እየቀነሰ እንዲሄድ አብሮ ምን መለወጥ አለበት ሲባል የገጠር ግብርና ትራንስፎርሜሽን መኖር አለበት፡፡ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ሲባል አርሶ አደሩ ለሚያመርተው ምርት ማከማቻ፣ ማበጠሪያ፣ ወደ ገበያ የሚወስድበት ምቹ መንገድና ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ እነዚህን መሠረተ ልማቶች ካሟላህ በጥቂት ሰው በማሽነሪ እርሻ ማካሄድ ትጀምራለህ፡፡ ይህ ማለት ገጠር ላይ ያለው የሰው ኃይል እየሠለጠነ ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሄድ ታደርገዋለህ፡፡ የግብርናውን ቦታ ኢንዱስትሪው ሲወስድ መዋቅራዊ ሽግግር ይመጣል፡፡ በዚህም አጠቃላይ ኢኮኖሚያችን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እያዘነበለ ትልቁን ድርሻ እንዲይዝ ያደርጋል፡፡ እነዚህ  ከገጠር የሚወጡት አርሶ አደር ወጣቶች በሜካናይዜሽን እየተማሩና እየሠለጠኑ ይመጣሉ፡፡ ከዚያ ወደ ዘመናዊ የቴክኒክና ሙያ በመግባት ለኢንዱስትሪ የሚሆን የሰው ኃይል እየፈጠርክ ትሄዳለህ፡፡ ኢንዱስትሪ ስንል ሁሉም ክልልና ገጠር ያለ ሰው አዲስ አበባ ይመጣል ማለት አይለም፡፡ በገጠር ትራንስፎርሜሽን የጎጆና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ በገጠር በሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግርና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ገጠር ላይ የሚደረጉ ኢንዱስትሪዎችን ይይዛል፡፡ በዚህ ሒደት የአርሶ አደር ልጆች እየተማሩና እየሠለጠኑ ባለቡት ቦታ እነዚህ አምራቾችና አገልግሎት ኢንዱስትሪዎች ውስጥ እየገቡ እያደጉ ወደ ትልልቅ ኢንዱስሪዎች ሲሄዱ፣ በጠቃላይ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢኮኖሚያችንን ትልቁን ድርሻ ይይዛል ማለት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡– ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ ከሚባሉት ጉዳዮች በተለይ የገጠሩ ማኅበረሰብ ውስጥ ሲገባ ቴክኖሎጂ በሚፈለገው ደረጃ አለመራመድና የተደራሽነት ችግር፣ ቢሮክራሲ ማነቆ፣ ትራክተር የሚያንቀሳቅስ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖርና የኢንተርኔት ረት ልማት አለመሟላት ባሰባችሁት ፍጥነትና ልክ እንድትሄዱ አይገድባችሁም?

ማንደፍሮ (/)– ሥራችን ያንን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይፈልጋል፡፡ በየክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽን የምናቋቁመው እነዚህን ወጣቶች አሠልጥነው እንዲያስገቧቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ተቋማትን በገጠሩ ክፍል ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የብቅል ፋብሪካን ስትወስድ ከተማ አይደለም ያለው፣ ገጠር ውስጥ ነው የተተከለው፡፡ የቢራ ፋብሪካዎችም እንዲሁ የተለያዩ አካባቢዎች ነው ያሉት፡፡ ልክ የግብርና ዘርፉን ስታይ የወተትና የሥጋ ማቀነባበሪያዎች ወደ ገጠሩ እየወጡና እየተስፋፉ ሲሄዱ፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ያመጡና አዲስ አበባን የሚያጨናንቀው ሰው በሁሉም ቦታ ይሠራጫል፡፡ የአዲስ አበባ ዓይነት ልማቶች እያስፋፋንንና ከተሞች እየተስፋፉ፣ ሰውን እያሠለጠንን ለኢኮኖሚው የሚሆን የሰው ኃይል እየገነባን ነው የምንሄደው፡፡ ግብርናው ሰፊ በሆነበት ጊዜ ለግብርና የሚሆን የልማት ሠራተኛ እያሠለጠነክ ትሄዳለህ፡፡ ማኑፋክቸሪንግ እያደገ ሲሄድ ለማኑፋክቸሪንግ የሚሆን የሰው ኃይል እያሠለጠንክ ትሄዳለህ፡፡ ስለዚህ የሰው ኃይሉን የሚመራው ኢንዱስትሪው ነው፡፡ አሁን ሁሉም ነገር አለ? የለም፡፡ ነገር ግን ወደ እዚያ እየሠራን እንሄዳለን፡፡ የዲጂታል ሥራ ብዙ ነገሮችን ያቃልላል፡፡ ለምሳሌ የዲጂታል የምክር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ እንደ ድሮው አርሶ አደሩን ሰብስበህ አንድ ቦታ አድርገህ ሳይሆን፣ ቤቱ ቁጭ ብሎ የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኝና ጥያቄ አቅርቦ መልስ እንዲያገኝ ዲጂታል ቴክኖሎጂ አለን፡፡ በዚሁ ልክ ገበያም ሲፈልግ ሌላ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አለን፡፡ የግብርና ግብዓቶችን የሚገበያይበት ሌላ ሦስተኛ ቴክኖሎጂ አለን፡፡ አሁን እያደረግን ያለነው በእያንዳንዱ ማሠልጠኛ ማዕከል ከታብሌት ከፍ የሚል ስክሪን ተገጥሞ ዋይፋይ ገብቶላቸው፣ አርሶ አደሮች የሚፈልጉትን አገልግሎት ቤታቸው ቁጭ ብለው የሚከታተሉበት ስማርት ስልክ ባይኖራቸው እንኳ በማዕከል ሄደው እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ ሁሉም የተማሩ ላይሆኑ ይችላሉ፣ ግን የተማሩ ሰዎች በየማዕከሉ ተቀምጠው እየረዱዋቸው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚረዳ የዕርዳታ መስጫ ማዕከላት እንዲኖሩ እያደረኝ ነው እናደርጋለን፡፡ የዋይፋይ ተደራሽነትን ደግሞ በየቦታው ደንበኞች ስናመጣ የኢንተርኔት አቅራቢዎች እየሰፉ ይሄዳሉ፡፡

ሪፖርተር፡– ገበሬው ለቴክኖሎጂ ዝግጁ ነው?

ማንደፍሮ (/)– ብዙ ሰው የሚያስበው አርሶ አደር ያልተማረና መጻፍ ማንበብ የማይችል አድርጎ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አርሶ አደሮች ድሮ ቀርተዋል፡፡ አሁን ያሉት አርሶ አደሮች በትምህርት መስፋፋት ምክንያት ተምረው፣ ነገር ግን በኢኮኖሚ አቅም ምክንያት ዩኒቨርሲቲ ባይገቡ እንኳ ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ በኩታ ገጠም እርሻ በአመራር ደረጃ ያሉ ብዙዎቹ በወረዳ ደረጃ ተወክለው የሚሙጡት የተማሩ ልጆች ናቸው፡፡ ትንንሽ ሱቆች የሚከፍቱትና ሜካናይዜሽን የሚያሠለጥኑት በሙሉ የገጠር ልጆች ናቸው፡፡ ነገር ግን የተማሩ ናቸው፡፡ እና አሁን ያለው አርሶ አደር እንደ ድሮው እኛ እንደምናስበው የማያነብ ሳይሆን፣ የሚያነብና የሚጽፍ ዘመናዊ ትምህርት የተማረ ነው፡፡ የሚፈልገውን ነገር ፈልጎና አንብቦ ማግኘት የሚችል አርሶ አደር ነው፡፡  ዕውቀት ያለው አርሶ አደር ገጠር ላይ እየተፈጠረ መሆኑን ብዙ  ሰው ቶሎ አይመጣለትም፡፡ 

ሪፖርተር፡– ወጣቱ ዘንድ ወደ ከተማ የመሳብና ከተሜነትን የመውደድ አባዜ እየበዛ የመጣ ይመስላል፡፡ ይህ ከሥራ ዕድል ዕጦት እንደሆነም ይወሳል፡፡ ይህ ሁኔታ በእናንተ ሥራ ላይ ጫና አይፈጥርባችሁም? መሬትስ ፆሙን አያድርም?

ማንደፍሮ (/)– በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ለምን ወጣቶች ከገጠር ወደ ከተማ ይፈልሳሉ የሚለውን ስትመለከት፣ በአካባቢያቸው አማራጭ ቢኖራቸው ልክ በከተማ የምናደርገውን ኢንቨስትመንት ቢኖረን እኮ ማንም ከተወለደበት መራቅ አይፈልግም፡፡ ነገር ግን አማራጭ ሲያጣ፣ ገቢው ሲያንስና ሁሉም ነገር ጨለማ መስሎ ሲታየው ይወጣና ዕለታዊ የሆነ የቀን ሥራ አግኝቶ ሕይወቱን የሚመራበት መንገድ ነው የሚፈልገው፡፡ የገጠር ትራስፎርሜሽን፣ ገጠር ላይ የሚደረገው የመሠረተ ልማት ሥራ፣ ገጠር ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ሥራ ወጣቶችን እዚያው የሚይዝ ይሆናል፣ ከሠራንበት ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ከገጠር የተማረው ሰው እየመጣ በአመዛኙ ያልተማረ ሰው እዚያ እየቀረ ሲሄድ መሬት ፆሙን ሊያድር ይችላል፡፡ አዎ ሊያድር ይችላል፣ ያንን የምንፈታው በሜካናይዜሽን ነው፡፡ ሰዎች በበሬ እያረሱ በእጅ እየዘሩና በእጅ እያረሙ ሳይሆን ለሜካናይዜሽን የሚመች አካባቢን በማዘመን ነው፡፡ ሰው ስለሜካናይዜሽን የሚያውቀው ባለ500፣ ባለ300 ባለ100 የፈረስ ጉልበት ያላቸውን ትራክተሮች ነው፡፡ አሁን ትንንሽ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮች በተለያዩ መልከዓ ምድሮች የሚሠሩ፣ በእጅና በትንንሽ ሞተሮች የሚሠሩ አሉ፡፡ ድሮ የነበረውን አድካሚ ሥራ የሚያሳልጡና ሥራን በቀላሉ የሚያከናውኑ ማሽነሪዎች ስላሉ ማሽነሪዎች እንዲገዙ በማድረግ በገጠር የኢንዱስትሪ፣ የማኑፋክቸሪንግና ሌሎችም እያሳደግክ ስትሄድ ሰው ባለበት ይቀራል፡፡     

ሪፖርተር፡– በቅርቡ ስንዴን በገፍ የማምረት ሒደት ሲካሄድ አርሶ አደሮች በግድ ወደ ስንዴ እርሻ እንድንቀይር ተገደድን፣ ቲማቲምና ሽንኩርት ማምረት አልቻልንም እያሉ ቅሬታ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ይህ እውነት ነውገበሬው ሳይገደድ በሰፋፊ እርሻዎች እያመረተ ያለው እንዴት ነው?

ማንደፍሮ (/)– ስንዴ የቲማቲምና የሽንኩርት እርሻን እየወሰደ ነው የሚለው ጉዳይ ምናልባት እውነትም ሊሆን ይችላል፣ እውነትም ላይሆን ይችላል፡፡ በሁሉም ቦታዎች ፍፁም አይደለም ብዬ በመረጃ አስደግፌ የምናገረው ነገር ስለሌለኝ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መንገድ የሚመጡ ቅሬታዎች በስብሰባ ላይም ይነሱ ስለነበረ፣ በፍላጎታቸው ለማምረት የሚገባቸውንና ከዚያ መሬት ላይ ምን ብዘራ ምን አተርፋለሁ የሚለው ውሳኔ ለአርሶ አደሮች ነው የሚሰጠው፡፡ ሁለተኛ ስንዴ የሚመረተው ለሦስት ወራት ነው፡፡ በቀሪ ወራት ቲማቲም፣ ሽንኩርት ወይም ሌሎች ነገሮችን ማምረት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ከሦስቱ የምርት ወራት በአንዱ ስንዴ ማድረግ የሌሎችን አይጎዳም፡፡ እንዲያውም ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ሌላው ነገር ቲማቲም እኮ ያስፈልገናል፣ ይህንን አስፈላጊ ምርት ለማግኘት ልክ እንደ ስንዴው አቅደን እየሠራንበት ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች እንዲያ ዓይነት ግድፈቶች ይኖራሉ፣  ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ቀጣይ የሚሆኑ አስገዳጅ የማምረት ሒደቶች ከሆኑ ሊደገም አይገቡም፡፡ ምክንያቱም ሰው በፍላጎቱና ከፍተኛ ገቢ ሊያገኝበት የሚችለውን አጥንቶ እንዲያመርት ነው የሚፈለገው፡፡ 

ሪፖርተር፡– ሰፋፊ እርሻዎች (Comerical Farming) ቀድሞ ከነበሩት ለምሳሌ በደርግ ከነበረው በምን ይለያ?

ማንደፍሮ (/)– መንግሥት እንደ መንግሥት በዘመናዊ የንግድ እርሻዎች ሰብል አያመርትም፡፡ እነዚህ  እርሻዎች በኮርፖሬሽን ደረጃ ማለትም የስኳር ኮርፖሬሽን፣ ዘር አምራች የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንና መሰል ድርጅቶች አማካይነት እንጂ፣ መንግሥት መሬት ይዞ ትራክተር አሰማርቶ አስመርቶ የሚሸጠው ወይም የሚመራው እርሻ የለም፡፡ አሁን እነዚህ እርሻዎች አምስት በመቶ ይሆናሉ የሚል መረጃ አለኝ፡፡ ነገር ግን ከአዲስ አበባ እየራቅህ ስትሄድ ብዙ የግል እርሻዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ መረጃው መሠረት 95 በመቶ አነስተኛ ግብርና ነው፡፡ እኔ ግን አነስተኛ ባለይዞታ መሆናቸውን ሳይሆን የማየው፣ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም በቆሎ ወይም ስንዴ ሊያመርቱ መቻላቸውን ነው፡፡ የንግድ እርሻ የሚያሰኘው እኮ በተመሳሳይ መሬት ላይ ተመሳሳይ ምርት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ማምረቱ ነው፡፡ ግለሰብ ይዞትም መቶ ሰዎች ይዘውትም ይሠሩ የሚለያየው ክፍፍሉ ነው እንጂ፣ በኩታ ገጠምና በንግድ እርሻ መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ሥርዓታቸው ዘመናዊ እስከሆነ ድረስ ማለት ነው፡፡ ወደፊት እነዚህ በኩታ ገጠም የሚያርሱ አርሶ አደሮች ወደ ኩባንያና ኢንተርፕራይዝ እንዲቀየሩ ነው የምናደርገው፡፡

ሪፖርተር፡– ብርቱካን አፕል ወይም ሌሎች የግብርና ምርቶችን እዚህ ማምረት እየተቻለ ከውጭ ይገባሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከኢትዮጵያ ተወስደው ተቀነባብረው የሚመለሱ እንዳሉም ይነገራል፡፡ ብርቱካን ግብፅ ጭምር እንደሚመጣ ይታወቃል፣ ይህ ለምን ይሆናል?

ማንደፍሮ (/)– ብርቱካን እናመርታለን፡፡ የሚፈለገው ነገር ምንድነው የሚለውና ለምን ራሳችን አልቻልንም የሚለው ሁለት ዓይነት ነገር ነው፡፡ ብርቱካን አምርተህ አገር ውስጥ ብትሸጥ ነው? ወይስ ብርቱካን ከወጭ አስገብተህ አገር ውስጥ ብትሸጥ ነው የሚሻለው የሚለውን እኛ እንደ ንግድና ቢዝነስ ነው የምናየው፡፡ ከዚህ ቀደም ስንዴ ስናስገባ ነበር፡፡ አሁን ራሳችን ወደ መቻል ሄደናል፡፡ በየዓመቱ በ700 እና በ800 ሚሊዮን ዶላር እየገዛህ ብታስመጣ ነገሩ የሚቆም አይደለም፡፡ ሰው እየበዛ ሲሄድ የምናስመጣውም እየጨመረ ነው የሚሄደው፣ ብዙ ዋጋ ያስወጣል፡፡ ስለዚህ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሰን፡፡ ነገር ግን ብርቱካንን ማስመጣት ብዙ ገንዘብ የማያስወጣህ ከሆነ አገር ውስጥ ለማምረት ከምትፈጀው ጊዜና ገንዘብ የተሻለ ከሆነ፣ ብርቱካን የሚመገበው ማኅበረሰብ ያን ያህል ካልሆነ አማራጩን ትወስዳለህ፡፡ ነገር ግን በየቀኑ በምግብ ሥርዓታችን የሚያስፈልገን እንደ ዳቦ ዓይነት ምርት ሁሉም የሚፈልገው በመሆኑ፣ ዳቦ ማቅረብ የመንግሥት ግዴታ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ብዙዎች ከማኅበረሰቡ ፍላጎት ጋር የሚሄዱ፣ መንግሥት ማቅረብ የሚገባውንና የቅንጦት የሆኑትን ማምረት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ውስኪ ከውጭ እናስመጣለን፣ ነገር ግን አገር ውስጥ ማምረት አለብኝ የሚል ካለ ያመርታል እንጂ መንግሥት ፋብሪካ አይገነባም፡፡ የሚጠጣና መግዛት የሚችል ግን ከውጭ ያስመጣል፡፡ 

ሪፖርተር፡– የጥራቱ ጉዳይስ? ግብ የሚመጣው ብርቱካን የተሻለ እንደሆነ ይታወቃል እኮ?

ማንደፍሮ (/)– የግብፅ ብርቱካን ጥራት ምንጩ ወይ የእስራኤል ወይ አሜሪካ ነው፡፡ እኛ ዘንድ ጋር ያለውም ሆነ ሌላ አገር ያለው ዝርያዎቹ ከእነ ስሞቻቸው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህን ዝርያዎች መተሃራ አካባቢ እምጥተህ ማምረትና ግብፅ ወይም ሱዳን ውስጥ የሆነ በረሃ ውስጥ ማምረት ከፍተኛ የጥራት ልዩነት አያመጣም፡፡ የሚያመጣው ልዩነት አንተ በምታመርበት ጊዜ የምትጠቀማቸው ፀረ ተባይ፣ ፀረ አረም ኬሚሎች ናቸው ጥራቱን የሚለውጡት፡፡ ምክንያቱም አዋሽን ተጠቅመህ የምታመርተውና ግብፆች ወይም ሱዳኖች ብሉ ናይልን ተጠቅመው በቆላ አካባቢ የሚያመርቱትን ስታይ የምርምር፣ የቁጥጥርና የክትትል፣ እንዲሁም የአዋጭነት ጥናት ይፈልጋል፡፡ ከበሽታና ከተባይ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ከሆነ ችግር የሚሆነው መንግሥት ያንን እንደ ጉዳይ ላይቆጥረው ይችላል፡፡

ሪፖርተር– የልውጥ ዘረመል (Gentically Modified Organism-GMO) የሚባለው ኢትዮጵያ ውስጥ ..2015 ሕጉ በፓርላማው ከፀደቀ ወዲህ ሁለት ኃይሎች ተፈጥረዋል፡፡ በአንድ በኩል ቴክኖሎጂ ሊያመጣው የሚችለውን የጤና አደጋ፣ የዋጋ ውድነትና የአቅርቦት ችግር በማንሳት ጠንካራ ሕግ ከሌለ ሊተገበር አይገባም የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ አይ ይቻላል ድርቅን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት ማምረት ይቻላል በማለት ክርክር ያነሳሉ፡፡ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት በዚህ ረገድ ምን መልስ አለው? እንደ አንድ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም ማለቴ ነው?

ማንደፍሮ (/)– እኛ የምንመርጠውና የማንመርጠው የራሳችን ቴክኖሎጂ የለንም፡፡ መንግሥት የሚደግፈውን እንደግፋለን፣ መንግሥት የሚቃወመውን እንቃወማለን፡፡ ልውጥ ዘረመል (GMO) ማለት ሳይንስ በልህቀት ተመራምሮ የደረሰበት የምርምር ውጤት ነው፡፡ ይህ የምርምር ውጤት አዲስ ነው፣ ሙሉ በሙሉ ይህን ይዘህ ወደ አዲስ ቦታ ስትገባ ጠንካራ የሕግ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ይህንን ሳታጠናክር ያልተጠበቁ ክስተቶች ቢፈጠሩ መከላከል አትችልም፡፡ ከዚያ አኳያ እንጂ የሚነሳው ሐሳብ ልውጥ ዘረመል (GMO) በጭፍን መጥላትም ወይም በደፈናው ለችግሩ ሁሉ መፍትሔ አለው ማለት የለብንም፡፡ ስለዚህ ይህ ዘዴ ለእኛ የሚጠቅመንና አሁን ካለን ቴክኖሎጂ የተሻለ ከሆነ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ እየተቆጣጠርን መጠቀም በጣም ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግሥት ይህንን የተመለከተ ሕግ አውጥቷል፡፡ ይህ ማለት በዚህ ዘዴ ሁለት የጥጥ ዝርያዎች አገር ውስጥ እንዲመረቱ ተደርገዋል፡፡ ይህ ማለት በመንግሥት ደረጃ ጂኤምኦ ለመጠቀም ዝግጁ ነን ማለት ነው፡፡ እንደ ተቋም የምንይዘው አቋም የለንም፡፡     

ሪፖርተር፡– ወደ ተግባር ቢገባ በበቂ ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚያግዙ ሕጎች አሉ?

ማንደፍሮ (/) አዎ ሕጎች አሉ፡፡ ሕጉን የሚያስተዳድሩ  አሉ፡፡  አቅም ገንብተናል አልገነባንም የሚለውን ትተን፣ በጤና ላይ ችግር አለው ወይም የለውም የሚሉ  አካላት ሁለት የተለያዩ ጽንፎች ናቸው፡፡ ለእኔ ችግር አለ የሚለውን በመረጃ ማስደገፍ አይቻልም፡፡ አዲስ ምርት ነው ይህንን ችግር አስከትሏል የሚል በሳይንስ የተረጋገጠና የተመዘገበ መረጃ የለም፡፡ ምንም ችግር አያስከትልም እንዳትል ይህንንም በሳይንስ ያረጋገጥነው ነገር የለም፡፡ ቴክኖሎጂን እንደ ቴክኖሎጂ እንዲያው የምትሰርዘው፣ የምታገለው፣ ወይም የምትደልዘው ነገር ሳይሆን በዚያው ልክ ደግሞ እያጨበጨብክ አሁን ያሉንን በዚህ እንተካለን የሚለውን ስታይ ከሁለቱ ጽንፍ አያወጣህም፡፡ መሆን ያለበት እየሞከርን የሚጠቅመን እንወስዳለን፣ የማይጠቅመንን አንወስድም፡፡ ጂኤምኦ ጉዳት ያደርሳል ስትል ማንኛውም ባዕድ ነገር እኮ በሰው ልጆች ላይ ጉዳት አለው፡፡ ለምሳሌ የአረም መድኃኒት፣ የተባይ መድኃኒትና የበሽታ መድኃኒት ስንረጭ ሁሉም ጉዳት አለው፡፡ ግን ጥቅሙን ነው የምናመዛዝነው፡፡ ያንን ስናመዛዝን ሰው ሳይመገብ ከሚሞትና እየተመገበ ይህን ችግር እያከሙ መኖር ይቻላል የሚለውን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ብዙ የምርምር ውጤት አማራጮች አሉን፡፡ ወደ ጂኤምኦ የምንሄደው አማራጭ ስናጣ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን አማራጮች አሉን፡፡ እነዚህን አማራጮች ከማን እንገባለን? እኛ ሳንሆን የምንወስነው አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር ልንገባ እንችላለን፡፡ ነገር ግን አማራጭ አጥተን በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ የሚያስገባን ቁመና ላይ አይደለንም፡፡ መንግሥት በጂኤምኦ አምርቱ አታምርቱ አይልም፡፡ እኛም ምሁራን አሉን፡፡ አርሶ አደሮቻችን የውጭ ኩባንያ ጥገኛ ሆነው እንዳይበዘበዙ የመከላከል የሞራል ግዴታ አለብን፡፡ አሁን በሰፊው ምርት የምናመርትባቸው አካባቢዎች ድርቅ መቋቋም ካቃታቸውና ማምረት ካልቻልን ጂኤምኦ እንጠቀማለን፡፡ አሁን የምንለው ምናልባት ከምናርሰው እርሻ ውስጥ 0.5 በመቶ ስለሆነው እንጂ፣ 99 በመቶ ለሆነው እርሻችን የምንጠቀምባቸው ብዙ አማራጮች አሉን፡፡ ሌላው እኛ ብቻ አይደለንም ይህንን ቴክኖሎጂ የምንጠቀመው፣ በስፋት የሚጠቀሙት አገሮች አሉ፡፡ እነሱ ዘንድ ሰው ያልገደለ እኛ ዘንድ ሊገድል አይችልም፡፡ በሌላ አገር አደጋ ያደረሰ እኛ ጋ አደጋ ሊያደርስ የሚችል ቴክኖሎጂ አንጠቀምም፣ ምክንያቱም የሥነ ምግባር ጉድለት ስለሆነ፡፡