

ወ/ሮ ምሕረት ንጉሤ የፍቅር የኢትዮጵያ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት
ማኅበራዊ ፈተናነቱ በልጆች ላይ የፀናው የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት
ቀን: October 6, 2024
ወ/ሮ አዳነች መለሰ ይባላሉ፡፡ እናትና አባታቸውን በወጣትነት ዕድሜያቸው በሞት አጥተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ላለፉት 17 ዓመታት የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን እህትና ወንድማቸውን የመንከባከብ ኃላፊነት በእሳቸው ጫንቃ ላይ የወደቀ ሆኗል፡፡
‹‹የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች የመንከባከብ ከባድ ሸክም እንዳለ ሆኖ፣ ማኅበራዊ ሥሪታችንና ፖሊሲዎቻችን እነኚህን ልጆች የሚደግፉ ሆነው አልተቀረፁም፤›› የሚሉት ወ/ሮ አዳነች፣ ለዚህም የኢትዮጵያን የትምህርት ፖሊሲ እንደ ዋና ማሳያ ያነሳሉ፡፡
የትምህርት ፖሊሲው የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች ታሳቢ ያደረገ አይደለም፡፡ ‹አካቶ› የሚለውም የትምህርት ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ወደ ትምህርት ተቋማት የምንልካቸው ልጆች በየትምህርት ቤቱ በተለየ ክፍል ውስጥ የሚቀመጡና ገለልተኛ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
በወ/ሮ አዳነች አነጋገር፣ በትምህርት ዘርፍ አካታችነት የሚባለው ነገር ከቃል አልፎ በተግባር እየተተረጎመ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ትምህርት ቤቶች ልጆቹ የሚቆዩበት እንጂ የሚማሩበት ሥፍራ ነው ብለውም አያስቡም፡፡ ልጆቹ ተጫውተው፣ ሲደክማቸውም ተኝተው፣ የሚመጡ ብቻ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ፡፡
‹‹ከትምህርት ባሻገር ማኅበረሰቡ ለእነኚህ ልጆች ፍቅርና እንክብካቤ አያደርግም፤›› የሚሉት ወ/ሮ አዳነች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችና ለውጦች ይመጣሉ ተብሎ ቢታሰብም፣ ማኅበረሰቡ ዛሬም ድረስ በልጆች ዙሪያ ያለው አመለካከት አልተቀየረም፡፡
ልጆቹን የእግዚአብሔር ቁጣ አድርጎ የመመልከት፣ የሚሠሩና ነገሮችን የመከወን አቅምና ችሎታ እንዳላቸው ያለመገንዘብ፣ ስሜትና ፍላጎታቸውን ለመረዳት አለመፈለግና ማግለል በሕዝቡ ዘንድ የሚፈጸሙ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም በልጆቹ ዙሪያ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ሥር የሰደደ አመለካከት ለመቀየር ሰፊ የሆነ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ መሠራት ይገባዋል ብለዋል፡፡
ፍቅር የኢትዮጵያ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ምሕረት ንጉሤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማኅበሩ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች በወለዱ ቤተሰቦች በ1987 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡
የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት በእንግሊዝኛ አጠራር፣ ‹‹ኢንቴሌክቸዋል ዲስአቢሊቲ›› ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ይህም ማለት ለዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ግብዓቶች ባለመሟላታቸው ምክንያት በግላዊና በማኅበራዊ ክንዋኔዎች ረገድ መዘግየት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም አስፈላጊው ድጋፍ የሚሟላ ከሆነ መሻሻል የሚችል ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖች ቁጥር ከአራት ሚሊዮን በላይ ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት የሚናገሩት ወ/ሮ ምሕረት፣ የማኅበሩ መኖር በርካቶችን ከታሰሩበት ጨለማ ክፍል እንዲወጡ፣ ከሰው እንዲቀላቀሉና ጥቂትም ቢሆን ማኅበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ አድርጓል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ፣ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከተማ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች የሚያስተምረው ትምህርት ቤት ‹‹ኮከበ ጽባህ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት›› ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ከማኅበሩ ምሥረታ በኋላ በሌሎች ትምህርት ቤቶችም አካታችነት የትምህርት ፖሊሲ እንዲተገበርና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ልጆቹ እንዲማሩ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ማኅበሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በዘጠኝ ክልሎች ላይ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅት ከ15 ሺሕ በላይ አባላት ያሉት መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ምሕረት፣ እነኚህ ልጆች በአቅማቸው ሊሠሯቸው የሚችሉትን የእጅ ሥራ ሙያዎች የሚያሠለጥኑ ሁለት የቴክኒክና ሙያ ተቋማትም አሉ፡፡ በድህነት ውስጥ ለሚገኙና የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ለሚያሳድጉ ወላጆች የኢኮኖሚ ችግሮቻቸውን እንዲቀርፉ የሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ በመደረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
‹‹በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው የግንዛቤ እጥረት የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ባለባቸው ልጆች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ምሕረት፣ ይህ መሆኑም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ባሉ የተለያዩ የልማት ዘርፎች እነኚህ ልጆች ተሳታፊ እንዳይሆኑ አግዷቸዋል፡፡ በተጨማሪም ማኅበሩ እስከ ገጠር ጫፍ ሄዶ አስፈላጊውን ድጋፍና ዕገዛ እንዳይሰጥ የገንዘብ ችግር ፈተና እንደሆነባቸው ፕሬዚዳንቷ አክለው ገልጸዋል፡፡
