Saturday, 05 October 2024 20:25

Written by  Administrator

በላዕላይ ፀለምቲ ወረዳ፣ ሰዎች  ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ምክንያት እየሞቱ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ። በዚሁ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ሳቢያ  ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ሕጻናት ለሞት መዳረጋቸው ተነግሯል።
በወረዳው “ደገርባይ” በተባለ የገጠር ቀበሌ፣ ከሁለት ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ አምስት ሕጻናት፤ “ምጫራ” እና “ዲማ” በተባሉ ቀበሌያት ደግሞ ሁለት ሕጻናት ለሞት መዳረጋቸውን ቢሮው ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። በዚሁ መግለጫ እንዳብራራው፤ ሕጻናቱ የሞቱት ከመስከረም 1 እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች ማረጋገጡን ጠቁሟል።
ታማሚዎች ከሚያሳዩዋቸው ምልክቶች መካከል ትውከት፣ መዝለፍለፍና የሆድ ማበጥ መሆናቸውን የጠቀሰው የክልሉ ጤና ቢሮ፤ ወረዳው ከጊዜያዊ ክልሉ የአስተዳደር መዋቅር ውጪ በመሆኑ በቦታው ተገኝቶ በሽታውን ለመፈተሽ፣ ብሎም አስፈላጊውን የሕክምና እገዛ ለማድረግ ሁኔታዎች አልፈቀዱም ብሏል።
“አሁን የሚስተዋለውን አደገኛ ሁኔታ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሊያውቁት ይገባል። አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉም እየሰራን ነው” ብሏል፣ የክልሉ ጤና ቢሮ።
የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ እንዲሁም ከሌሎች የሕክምና ባለሞያዎች ጋር በመሆን የሕክምና ድጋፍ ለማድረስ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክቷል።
ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ዓዲያቦ ወረዳ፣ የኮሌራ በሽታ በወረርሽኝ መልኩ ተስፋፍቶ በርካቶችን ማጥቃቱን መዘገባችን አይዘነጋም።