October 8, 2024 – Konjit Sitotaw 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ቶጫ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ 5 ቀበሌዎች ላይ የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ የመሬት መንሸራተት አደጋ መከሰቱ ተገልጿል።

በወረዳው ቲማ፣ ደሊ፣ ሻንዳ፣ ኦክሊና ቦቶሪ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመዝነቡ እና ከአካባቢው መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ ያጋጠመው የመሬት መንሸራተት አደጋ በአርሶ አደሮች ማሳ፣ በእንስሳት፣ በመኖሪያ ቤቶች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተጠቅሷል።

በደረሰው አደጋ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ተጠቁሟል።

የተከሰተውን ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ወረዳው ግብረ- ኃይል አቋቁሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ከዳውሮ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የወረዳው አስታዳደር በቀጣይም ከመደበኛ በላይ መጠን ያለው ዝናብ የሚጠበቅ በመሆኑ ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።