የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታን የጫኑ ተሽከርካሪዎች [ከፋይል]
የምስሉ መግለጫ,የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታን የጫኑ ተሽከርካሪዎች

8 ጥቅምት 2024, 16:11 EAT

የተባበሩት መንግሥታት በአማራ ክልል የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የምግብ እርዳታን ጨምሮ ለማቋረጥ እያሰበ ሲሆን፣ ይህ ዕቅዱ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የተመለከተው ረቂቅ ምክረ ሃሳብ በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት በክልሉ የሚያካሄደውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማቋረጥ ሃሳብ እንዳለው አመልክቷል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ነሐሴ ወር ላይ ያዘጋጀው ይህ ረቂቅ ምክረ ሃሳብ ባለፈው ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ብቻ 10 የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሠራተኞች አካላዊ ጥቃት ሲደርስባቸው 11 ደግሞ ባልታወቁ ወንጀለኛ ቡድኖች መታገታቸው በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ያዘጋጀው ባለሦስት ገጽ ሰነድ “በክልሉ የሚያካሄደውን የሰብዓዊ እርዳታ ለጊዜው ማቆም” ማሰቡን አስፍሯል።

በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ለጋሽ አካላት በምክረ ሃሳቡ ላይ የቀረበውን በክልሉ የሚካሄደውን የረድኤት ሥራ የማቋረጥ ሃሳብን መቃወማቸው ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአምስት ወራት ውስጥ 50 የረድዔት ሠራተኞች በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ተግባራት ላይ ተሰማርተው እያሉ ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውቆ ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኢትዮጵያን አስመልክቶ ሰኔ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርቱ የፀጥታ ችግር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚያደርገው ሰብዓዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጿል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም አጋር የሆነው ሜዲካል ቲምስ ኢንተርናሸናል የተሰኘው የረድዔት ድርጅት አሽከርካሪ በአማራ ክልል እንደተገደለ በዚህ ሪፖርት ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም ሕይወታቸው የጠፋ የእርዳታ ሠራተኞች ቁጥር ሃምሳ ማድረሱንም አክሏል።

የረድዔት ሠራተኞችን ይዞ የነበረው መኪና በጥይት መመታቱን ተከትሎ አሽከርካሪው መገደሉን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ግንቦት 20/2016 ዓ.ም. መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

ሪፖርቱ አክሎም በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ለሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ጭምር ፈታኝ መሆኑንም ኮሚሽኑ በወቅቱ ገልጾ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የሆኑት ራሚዝ አላክባሮቭ ለሮይተርስ እንደተነገሩት ከሆነ በሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ግድያዎች እና እገታዎች “የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ሥራቸውን እንዳያከናውኑ ያደርጋል፣ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ድጋፍ ወደሚያስፈልገው ማኅበረሰብ የምንደርስበት መንገድ በአግባቡ እስኪመቻች ድረስ ድጋፉ ይቋረጣል” ብለዋል።

በአማራ ክልል 2.3 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት የሚሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያቋርጥ ከሆነ በቀጥታ ተጎጂ እንደሚሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰቦች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ለበርካታ ሰዎች ሞት እንዲሁም ለመፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ረቂቅ ምክረ ሃሳቡ በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ቢሮ፣ ለጋሾች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ለመንግሥታቱ ድርጅት ቢሮዎች ተጋርቷል።

በጉዳዮ ላይ ኦቻ ምላሽ እንዲሰጥ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ከአማራ ክልል አንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባዮችንም ምላሽ ለማግኘት አለመቻሉን ሮይተርስ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ከ2019 ጀምሮ እስከ 2023 ባሉት ዓመታት 36 የረድዔት ሠራተኞች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ( ዩኤን ኦቻ) ባለፈው ዓመት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች ምክንያት ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ፈታኝ መሆኑንም ማስተባበሪያ ቢሮው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ጠቅሷል።

ዩኤን ኦቻ በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት ምክንያት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ እና በርካታ ጉዳቶች ማጋጠማቸውን ገልጿል።

የረድዔት ሠራተኞች በታጠቁ አካላት ቀጥታ ዒላማ ባይሆኑም “ባለው የፀጥታ ሁኔታ ተለዋዋጭነት፣ የአካባቢ ሚሊሻዎችን ጨምሮ መሳሪያ ያነገቱ ዜጎች በአጠቃላይ የታጠቁ አካላት መበራከት ለረድዔት ሠራተኞች እና ለሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች ከፍተኛ ስጋትን ደቅነዋል” ብሏል።

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በረድዔት ሠራተኞች ላይ ዕገታ፣ ዝርፊያ እና ጥቃትን ጨምሮ 93 ክስተቶችን በአውሮፓውያኑ 2023 መዝግቤያለሁ ብሏል።

ሮይተርስ የተባበሩት መንግሥታትን ምክረ ሃሳብ በሚመለከት ለፕላን ኢንተርናሽናል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ መረጃው አንዳላቸው እና በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

“የሰብዓዊ ድጋፍ እጅጉን በሚያስፈልግበት ወቅት ለማቆም የቀረበውን ሃሳብ እንዲሁ በቀላሉ አንመለከተውም። ያም የሚሆነው በጣም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው” ብለዋል የፕላን ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቢሮ ዳይሬክተር ፒተር ስዌትናም።

ይህም የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጡ ሠራተኞቸ በአማራ ክልል ደኅንነታቸው ተጠብቆ መንቀሳቀስ መቻላቸውን እንዲሁም በክልሉ በሠራተኞች ላይ የተፈጸሙ እገታዎች እና ግድያዎች በገለልተኛ አካላት የሚመረመሩ ከሆነ ነው ብለዋል።