በአፋር ክልል ዱለሳ ወረዳ የፈለቀው ፍል ውሃ አጠገብ ሰዎች ቆመው

8 ጥቅምት 2024, 16:56 EAT

በአፋር ክልል ዱለሳ ወረዳ በተከሰተ “የመሬት መንቀጥቀጥ” ምክንያት ከተፈጠረ የመሬት ስንጥቅ ውስጥ ፍል ውሃ መፍለቅ መጀመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወረዳው አስተዳደር ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከትናንት ሌሊት ጀምሮ መፍለቅ የጀመረው ፍል ውሃ “መጠኑ እየጨመረ” መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እያስተናገደ ባለው የአፋር ክልል ጋቢ ራሱ ዞን በሚገኘው ዱለሳ ወረዳ ሳንጋቶ ቀበሌ ፍል ውሃ መፍለቅ የጀመረው ትናንት ሰኞ መስከረም 27/2016 ዓ.ም. ምሽት “የመሬት መንቀጥቀጥ” ከተከሰተ በኋላ እንደሆነ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ደስታ እና ሁለት የቀበሌው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ትናንት ምሽት ሦስት ሰዓት ገደማ መከሰት የጀመረው “የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ ሶስት ጊዜ ያህል” መደጋገሙን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ይህንኑ የሚያነሱት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አሊም “ትናንት በስቲያ ከተከሰተው {የመሬት መንቀጥቀጥ አንጻር] የትናንቱ ትንሽ ያነሰ ነው” ሲሉ የክስተቱን መጠን አስረድዋል።

ከትናንት በስቲያ እሁድ ዕለት የዱለሳ አጎራባች በሆነው አዋሽ ፈንታሌ ዞን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.9 ሆኖ የተመዘገበ ነበር። ንዝረቱ አዲስ አበባ ከተማ ድረስ የተሰማው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአካባቢው ከተከሰቱት ከፍተኛው ነበር።

የወረዳው አስተዳዳሪ እና ነዋሪዎች በትናንትም የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ እንደነበር ቢገልጹም ቢቢሲ ይህንን በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶችን በሚከታተሉ ድረ ገፆች ላይ ተመዝግቦ አላገኘም።

ቢቢሲ፤ ክስተቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦፊዚክስ፣ ህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ተመዝግቦ እንደሆን ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።

“የመሬት መንቀጥቀጥ” መከሰቱን የሚናገሩት የቀበሌው ነዋሪዎች በበኩላቸው ክስተቱ ካቆመ በኋላ ሌሊት አስር ሰዓት ገደማ ላይ ድምፅ መስማታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ሡልጣን ካሚል የተባሉ የቀበሌው ነዋሪ፤ “ውሃው የወጣው የአካባቢው ማህበረሰብ [በሚኖርበት] ሰፈር ውስጥ ነው። ድምፅ ነበረው። ማታ ፈርተን ነው ያደርነው። በጠዋት ሄደን ሁሉንም ነገር ለማየት ችለናል” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

ጠዋት ላይ ነዋሪዎች ድምፅ ወደተሰማበት ቦታ ሲያመሩ ከመሬት ስንጥቅ ውስጥ ፍል ውሃ እየፈለቀ መመልከታቸውን አቶ ሡልጣን ተናግረዋል።

ሐሰን የተባሉ ሌላ የቀበሌው ነዋሪ በበኩላቸው፤ “[ፍል] ውሃው የሚወጣው በድስት እሳት ላይ እንደተጣደ ውሃ ነው። ከመሬት ጥቁር ጭቃ ይወጣል። ወደላይ ይፈናጠራል” ሲሉ በቦታው ተገኝተው የተመለከቱትን ገልጸዋል።

ቢቢሲ፤ ከወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ባገኘው ቪዲዮ ላይ ጥቁር ጭቃ ያለበት ውሃ ወደላይ እየተፈናጠረ ተመልክቷል። ውሃው የሚወጣበት አካበቢ ጭስ እንዳለበትም በቪዲዮው ላይ ይታያል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,በአፋር ክልል ዱለሳ ወረዳ የፈለቀው ፍል ውሃ

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ውሃው በሚወጣበት የመሬት ስንጥቅ ስር ድምፅ እንደሚሰማ አስረድተዋል። ወደላይ የሚፈናጠረው ፍል ውሃ መጠን እና የሚፈልቅበት ስንጥቅ መጠን እየጨመረ እንደሆነም ሁለቱም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አቶ ሀሰን፤ “[ፍል ውሃው የሚወጣበት] ቀዳዳው ሰፍቷል። እኔ [የሚውጣው] ‘ውሃ ቀንሶ ይሆን’ ብዬ ሦስት ጊዜ ሄጃለሁ። በተለያየ ሁኔታ ውሃው ጨምሮ ነው ያገኘሁት” ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል።

ፍል ውሃው በወጣበት ሳንጋቶ ቀበሌ ውስጥ ፍል ውሃ ባለመኖሩ አዲሱ ክስተት ነዋሪዎች ድንጋጤ እና ስጋት ላይ እንደጣለ ነዋሪዎች እና የዱለሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሉ ተናግረዋል።

በ1990 ዓ.ም. አካባቢ በቀበሌው ተመሳሳይ ክስተት ተፈጥሮ እንደነበር ከአካባቢው ሽማግሌዎች መስማታቸቸውን የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ በወቅቱ የፈለቀው ፍል ውሃ ከቆይታ በኋላ መጥፋቱ እንደሚነገር ገልጸዋል።

“ሰዎች በቅርበት እዚያ አካባቢ ይኖራሉ። የእኛ አካባቢ ማህበረሰብ አርብቶ አደር ከመሆኑ አኳያ ከብቶቻቸውን ፍየሎቻቸውን የሚጠብቁበት ቦታ ነው” የሚሉት አቶ አሊ፤ የወረዳው አስተዳደር ክስተቱን ለማጣራት ባለሙያዎችን ወደ ቀበሌው መላኩን ጠቅሰዋል።

ዋና አስተዳዳሪው፤ “ የሚፈጠረው ነገር ስለማይታወቅ [ነዋሪዎች’ ከዚያ አካባቢ ለቅቀው ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ የማድረግ ስራ እየሰራን ነው። እንደዚህ አይነት ነገር ታይቶም ስለማይታወቅ ከፍተኛ ስጋት ነው ያለው” ሲሉ የወረዳው አስተዳደር እየወሰደ ያለውን እርምጃ ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ጋቢ ራሱ ዞን በተደጋጋሚ እያጋጠመ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ነዋሪዎች ከሰፈሩበት አካባቢ እንዲነሱ የተደረገው በዱለሳ ወረዳ ብቻ አይደለም።

አጎራባቹ አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ከሁለት ሳምንት በፊት በአካባቢው በሚገኘው ከሰም ግድብ እና ፈንታሌ ተራራ አካባቢ የሚኖሩ ከ700 በላይ ሰዎችን ገላጣ ሜዳ ወደሆኑ አካባቢዎች ማዘዋወሩን ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።