10ኛው የጣና ፎረም
የምስሉ መግለጫ,ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደው 10ኛው የጣና ፎረም መክፈቻ

8 ጥቅምት 2024, 12:15 EAT

የአፍሪካ ሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው እና በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር የሚካሄደው ዓመታዊው የጣና ፎረም ጉባኤ ለሦስተኛ ጊዜ ተራዘመ።

ይህ 11ኛው ጉባኤ መጀመሪያ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው ባለፈው ዓመት ከጥቅምት 2 – 4 2016 ዓ.ም. ነበር። ሆኖም ጉባኤው “ባልተጠበቁ ሁኔታዎች ምክንያት” እንደተራዘመ የፎረሙ ጽህፈት ቤት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናቶች ተቋም አስታውቆ ነበር።

ጉባኤው ሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ጽህፈት ቤቱ በጊዜው አስታውቆ የነበረ ቢሆንም በተባለው ጊዜ ሳይካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ተራዝሟል።

“አፍሪካ እየተሻሻለ በመጣው የዓለም ሥርዓት ውስጥ” የሚል መሪ ቃል የያዘው 11ኛው የጣና ፎረም ጉባኤ ከጥቅምት 15 – 17/2017 ይካሄዳል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ነገር ግን ፎረሙ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ “11ኛው የጣና ከፍተኛ የፀጥታ ጉዳዮች ፎረም (እ.አ.አ) ወደ 2025 መተላለፉን የጣና ፎረም ሴክሬታሪያት ለማሳወቅ ይወዳል” ብሏል።

ፎረሙ አክሎም የጣና ፎረም ሴክሬታሪያት ከጣና ፎረም ቦርድ ጋር በመሆን ፎረሙ የሚካሄድበትን ቀጣይ ቀን ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።

የጣና ፎረም ሲራዘም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከሦስት ዓመት በፊት 10ኛው የጣና ፎረምም በተመሳሳይ ሁኔታ መራዘሙ ይታወሳል። ኅዳር አጋማሽ 2014 ዓ.ም. ላይ ሊካሄድ ነበረው ይህ ፎረም የተካሄደው ከአንድ ዓመት በኋላ ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ነው።

ከዚያ በፊትም በ2013 ዓ.ም. የነበረው የጣና ፎረም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ በአዲስ አበባ ውስን ተሳታፊዎች ባሉበት እንዲካሄድ ሆኖ ነበር።

የጣና ፎረም የሚካሄድበት የአማራ ክልል ላለፈው አንድ ዓመት በፌደራል መንግሥቱ እና በፋኖ ኃይሎች መካከል ውጊያ እየተካሄደበት ይገኛል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሰኞ መስከረም 27/ 2017 ዓ.ም. አመሻሽ ባወጣው መግለጫ የጣና ፎረምን በምታስተናግደው ባሕር ዳር ከተማ “ተጠምዶ የነበረ ፈንጂ ጉዳት ሳያደርስ” መምከኑን አስታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በዚሁ መግለጫው ፈንጂው የመከነው በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 13 በተለምዶ ኪቤአድ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ መሆኑን ጠቁሟል። ፖሊስ ኮሚሸኑ ፈንጂውን “ጽንፈኛው ኃይል ያጠመደው” ነው ሲል በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ባወጣው ሪፖርት በአማራ ክልል ካለፈው ሰኔ ወር ወዲህ ከግጭቱ ጋር ግንኙነት የለሌላቸው ከ130 በላይ ሲቪል ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች “በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት” መገደላቸውን አመልክቷል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በአማራ ክልል በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዘፈቀደ በጅምላ መታሰራቸውን አስታውቋል።

መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ኢሰመኮም ባለፈው እሁድ ባወጣው መግለጫ በክልሉ እየተፈጸመ ነው ያለው “የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን እና መርሖችን ያልተከተሉ እስሮች በአፋጣኝ ሊቆሙ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

የጣና ፎረም ጉባኤ “አፍሪካ መር መፍትሄዎችን” ማዕከል በማድረግ በአህጉሪቱ የሚገጥሙ የሰላም፣ የደኅንነት እና የፀጥታ ዙሪያዎች ላይ ይመክራል።

ግጭቶችን ለመፍታት እና ማኅበረሰቦችን ለመለወጥ ግልጽ፣ ተገቢ ውይይት መሠረታዊ ነው በሚል መርህም የአሁን እና የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎችን፣ ከአህጉሪቱ የተውጣጡ የሰላም እና የደኅንነት ባለሙያዎችን በማሰባሰብ አፍሪካን ማዕከል የሚያደርግ የፀጥታ መፍትሄ ላይ ይወያያል።

የጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናቶች ተቋም እና በታወቁ አፍሪካውያን ጠንሳሽነት ከ11 ዓመታት በፊት የተጀመረ ነው።

የጣና ፎረም ሊቀ መንበር የቀድሞው የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ማህማ ናቸው። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆም የጣና ፎረም ሊቀመንበር ነበሩ።