ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ሺ

ከ 8 ሰአት በፊት

ቻይና እና ሩሲያ የፍልስጤማውያን የአገር ባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ደጋፊ ሆነው ቆይተዋል።

በቅርቡ ግን ቤይጂንግ እና ሞስኮ አዲስ እና ያልተለመዱ ሚናዎችን እየወሰዱ ነው። በተለይም ለአንድ ዓመት የዘለቀውን በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት በሽምግልና ለመፍታት ላይ ታች እያሉ ነው።

በሐምሌ ወር ሐማስ፣ ፋታህ እና ሌሎች በደርዘን የሚቆጠሩ የፍልስጤም ቡድኖች ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ጋዛን የሚያስተዳድር “የብሔራዊ ጊዜያዊ መንግሥት” ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ስምምነት በቻይና መዲና ቤይጂንግ ተፈራርመዋል።

በየካቲት ወር ደግሞ ቡድኖቹ ሞስኮ ላይ ተገናኝተው ተመሳሳይ ስምምነትን ፈጽመዋል።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ (መሐል) ከፋታሁ አል-አሉል (ግራ) እና ከሐማሱ ሙሳ አቡ ማርዙክ ጋር
የምስሉ መግለጫ,የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ (መሐል) ከፋታሁ አል-አሉል (ግራ) እና ከሐማሱ ሙሳ አቡ ማርዙክ ጋር

ቻይና እና ሩሲያ ከፍልስጤም ጋር ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ቁልፍ ከሆኑት ከኢራን፣ ከሶሪያ እና ከቱርክ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስቀጥለዋል። ከልዕለ ኃያሏ ዩናይትድ ስቴትስ በተቃራኒም ቤይጂንግም ሆነች ሞስኮ ሐማስን እንደ አሸባሪ ድርጅት አይመለከቱትም። ቡድኑን እንወያይ ብለው ለመጋበዝ ችግርም የለባቸውም።

ለመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ሽምግልና ተጨባጭ ውጤት ይኖረዋልን? ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ግን “የማይመስል ነው” አድርገው ይመለከቱታል። በርካቶች የሚያነሱት ሌላኛው አንገብጋቢ ጥያቄ ግን ቻይና እና ሩሲያ ከዚህ ምን ለማግኘት ይፈልጋሉ የሚለው ነው።

ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት፡ ዓለም አቀፍ ተጽእኖን ለማግኘት እና በዓለም ላይ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ያላቸውን ኃያልነት መገዳደር ናቸው።

ከማኦ እስከ ዢ ጂንፒንግ

የቀድሞው የቻይና መሪ ማኦ ዜ ዱንግ ምሥል በማዕከላዊ ቤይጂንግ
የምስሉ መግለጫ,የቀድሞው የቻይና መሪ ማኦ ዜ ዱንግ ምሥል በማዕከላዊ ቤይጂንግ

ዘመናዊቷ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና በአውሮፓውያኑ 1949 ከተመሠረተች ወዲህ ለፍልስጤም ጥያቄዎች በጎ ዕይታ ነበራት።

ለምዕራቡ ኢምፔሪያሊዝም መሠረት እና ዋሽንግተን የዘረጋችውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት የሚተቹትን ለመቆጣጠር የተቋቋሙ ናቸው በማለት የአገሪቱ መሥራች የሆኑት ማኦ ዜዱንግ እስራኤልን እና ታይዋንን በተመሳሳይ መልኩ ይመለከቷቸዋል።

የአዲሲቷ ቻይና ፀረ-ምዕራባዊ እና ፀረ-ቅኝ ግዛት ትርክት “በፍልስጤም ስቃይ ላይ የራሷን ልምድ ያየችበት ነው” ሲሉ የቻታም ሐውስ ተመራማሪ ሆኑት አህመድ አቡዱ ለቢቢሲ ሙንዶ ተናግረዋል።

ድጋፉ ግን በትርክቶች ብቻ አላበቃም። በዓለም ዙሪያ የሚደረጉ የነጻነት እንቅስቃሴዎችን የደገፉት ማኦ፤ ለፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት (ፒኤልኦ) የጦር መሳሪያ ከመላክ ባለፈ በድርጅቱ አስተሳሰብ ላይም ሰፊ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር
የምስሉ መግለጫ,የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር

በኋላ ላይ የቻይና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተቀየረ። የዴንግ ዣኦፒንግ እአአ በ1978 ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ “ባለጸጋነት ክብር ነው” የሚል ሃሳብ ተያዘ።

ቻይና የሶሻሊስት ገበያ ኢኮኖሚን ራዕይዋን ተግባራዊ ለማድረግ እና ለዓለም ክፍት መሆን ነበረባት። ይህንንም ለማሳካት ደግሞ ከርዕዮተ ዓለም ወደ ተግባራዊነት መሸጋገር ነበረባት። መንግሥታዊ ያልሆኑትን ከመደገፍ ይልቅ ቻይና ከዓለም ታላላቅ እና መካከለኛ ኃይሎች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት ነበራት።

እአአ በ2012 የዢ ጂንፒንግ ፕሬዝዳንት መሆን ግን ነገሮችን ለውጦታል ይላሉ አቡዱ። ዢ የአገራቸውን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ርዕዮተ ዓለሙን እንደገና አሻሽለው አቀረቡ። የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት ይህንን አካሄድ ለማስቀጠል ትክክለኛው አጋጣሚ ነው።

ከስታሊን እስከ ፑቲን

የእስራኤልን ነጻነት በቅድሚያ ዕውቅና ከሰጡት መካከል የጆሴፍ ስታሊኗ ሩሲያ አንዷ ናት
የምስሉ መግለጫ,የእስራኤልን ነጻነት በቅድሚያ ዕውቅና ከሰጡት መካከል የጆሴፍ ስታሊኗ ሩሲያ አንዷ ናት

ሩሲያ ከፍልስጤማውያን ጋር ያላት ግንኙነት ግን ትንሽ ለየት ባለመንገድ ይጀምራል። እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1948 እንደ አገርነት ስትመሠረት በቀዳሚነት ዕውቅና ከሰጧት አገራት አንዷ የጆሴፍ ስታሊኗ ሶቪየት ኅብረት ናት።

“በወቅቱ እስራኤል የሶሻሊዝምን ዝንባሌ የያዘች ይመስል የነበረ ሲሆን፤ ሁሉም ጎረቤቶቿ ደግሞ በአውሮፓ ቅኝ ግዛት ስር ነበሩ” ሲሉ በጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርሲቲ የመንግሥት እና የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክ ካትስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስራኤል የሶሻሊስት መንገድን አልተከተለችም። እአአ በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ ደግሞ የቀድሞው የሶቪየት መሪ ኒኪታ ክሩስቼቭ ራሳቸውን ከአረብ ብሔርተኝነት ጋር አዛመዱ።

“የፍልስጤም ጉዳይ ለሞስኮ በጣም ጠቃሚ ነበር። አሜሪካ እስራኤልን በመደገፏ ሶቪየት ደግሞ ፍልስጤማውያንን ስለደገፈች በአረብ አገራት ዘንድ ተወዳጅ እንድትሆን አድርጓታል” ብለዋል ፕሮፌሰር ካትስ።

ለብዙ አረብ አገራት የፍልስጤም ጉዳይ የመርኅ ጉዳይ ቢሆንም ለሞስኮ ግን የማመቻቸት ጉዳይ ነበር።

ሞስኮ በሚገኘው እስራኤል ኤምባሲ ፊት ለፊት የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓለማ የያዘ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ,ሞስኮ በሚገኘው እስራኤል ኤምባሲ ፊት ለፊት የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓለማ የያዘ ሰዎች

“በተለይ ከአሜሪካ ጋር ግጭት ውስጥ እስከሚከታቸው ድረስ ሊደግፉ አልፈለጉም። ሙሉ ለሙሉም ፀረ እስራኤልም አልነበሩም” ሲሉ ካትዝ አክለዋል።

የሶቪየት ኅብረትን መፈረረስን ተከትሎ ሩሲያ በእስራኤል ላይ ያላት የጠላትነት እየተቀዛቀዘ ሄደ። የሩሲያ አይሁዶች ወደ እስራኤል እንዳይሰደዱ የሚከለክለው ቁጥጥርም ተነሳ።

ቭላድሚር ፑቲን በአውሮፓውያኑ 2002 የሩሲያ ፕሬዝዳንት በሆኑበት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ እስራኤላውያን የቀድሞዋ የሶቪየት ኅብረት ዝርያ ነበራቸው። አብዛኞቹም የሩሲያ ቋንቋን ይናገሩ ነበር።

ከዚያ ወዲህ ክሬምሊን ከእስራኤል ጋር ባለው ግንኙነት እና ለፍልስጤማውያን በሚሰጠው ድጋፍ መካከል ሚዛን ለመጠበቅ ሞክሯል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከእስራኤል መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ተቀዝቅዟል። በተለይም መስከረም 26 ሐማስ ድንበር ተሻግሮ ከፈጸመው ጥቃት እና እስራኤል በምላሹ በጋዛ ከከፈተችው ጦርነት በኋላ ግንኙነቱ ይበልጥ ተቀዛቅዟል።

አማራጭ የዓለም ሥርዓት

ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ዢ ቤይጂንግ ውስጥ
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ዢ ቤይጂንግ ውስጥ

ቻይና በዓለም ቀዳሚዋ የነዳጅ ገዢ ሆናለች። ግማሽ ያህሉን የምትገዛው በመካከለኛው ምሥራቅ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ከሚገኙ አገራት ነው።

ታዲያ የእሥራኤል እና የፍልስጤም ግጭትን ለማደራደር የምታደርገው ጥረት ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሟ ጋር የተያያዘ ነው ማለት ነው? በቻተም ሐውስ ተባባሪ ባልደረባ እንደሆኑት አህመድ አቡዱ እንደሚሉት መልሱ “አይደለም” የሚል ነው።

“በርካታ የአረብ አገራት ከእስራኤል ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አሻሽለዋል። እንደ ሳዑዲ አረቢያ ያሉ እና እስካሁን ያላሻሻሉት ደግሞ የጋዛ ጦርነት እልባት ሲያገኝ ለማስተካከል ተዘጋጅተዋል። ቻይና ይህንን በመረዳቷ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች አላገናኘችም” ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ አነጋገር በግጭቱ ላይ ባላት አቋም ምክንያት የትኛውም አገር ለቻይና ነዳጅ መሸጡን አያቆምም ማለት ነው።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ወደ አሜሪካ ባቀኑበት ወቅት የሁለቱን አገራት ባንዲራ የያዙ እናት እና ልጅ
የምስሉ መግለጫ,የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ወደ አሜሪካ ባቀኑበት ወቅት የሁለቱን አገራት ባንዲራ የያዙ እናት እና ልጅ

የቻይና ፍላጎት ከአሜሪካ ጋር ካላት ፉክክር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዕለ ኃያል ሆና የመታየት ምሥልን ለመፍጠር ካላት ፍላጎት ጋር የተዛመደ ሊሆን ይችላል።

“ቻይና ለሽምግልና እና ለሠላም ግንባታ ፍላጎት ያላት ምክንያታዊ እና ኃላፊነት የሚሰማት ታላቅ አጋር ሆኖ መታየት ትፈልጋለች” ብለዋል አቡዱ።

ቤይጂንግ “ከዩናይትድ ስቴትስ የተለየ የዓለም ሥርዓት አማራጭ ለማስተዋወቅ ትፈልጋለች” በማለትም ይከራከራሉ። ይህን ደግሞ አብዛኞቹ አገራት ፍልስጤማውያንን በሚደግፉበት የደቡቡ ዓለም ማሳካት ትሻለች ብለዋል።

“ቻይና ፍልስጤማውያንን እንዴት አንድ ማድረግ እንዳለባት ወይም በፍልስጤም እና በእስራኤላውያን መካከል ያለውን የተወሳሰበ ግጭት እንዴት መፍታት እንደሚቻል ምንም ፍንጭ የላትም። ከዚህ ግጭት አፈታት ጋር የተገናኘ ምንም ዓይነት ትልቅ ፍላጎትም የላትም” ብለዋል አቡዱ።

ትኩረትን ከዩክሬን ላይ ማንሳት

ዩክሬን ውስጥ መስዕዋትነት ለከፈሉ ወታደሮች በተዘጋጀ ስፍራ የቆመ ወታደር
የምስሉ መግለጫ,ዩክሬን ውስጥ መስዕዋትነት ለከፈሉ ወታደሮች በተዘጋጀ ስፍራ የቆመ ወታደር

በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ያለው ግጭት የዓለምን ትኩረት ከዩክሬን ጦርነት ላይ ለማንሳት በጣም ጠቃሚ ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ካትስ ተናግረዋል።

ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጀምሮም በአውሮፓ ውስጥ ያለው ግጭት ተረስቶ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ዞሯል።

የዩክሬን አጋሮች በተለይም አሜሪካ ወደ ኪዬቭ የሚልኩት አንዳንድ የጦር መሳሪያዎች ወደ እስራኤል እንዲዞር ተደርጓል።

“እስራኤል በፍልስጤም ላይ የምታደርገውን ዘመቻ በዝምታ በማለፍ ሩሲያ ዩክሬንን ወርራለች በማለት ምዕራባውያን እየከሰሱ መልከ ብዙ መሆናቸውን እያሳዩ ነው በማለት ሞስኮ ትከሳለች ብለው ያምናል” ፕሮፌሰር ካትስ።

የቻተም ሐውሱ አህመድ አቡዱ በበኩላቸው የሩሲያ የሽምግልና ሚና ዩክሬንን ከወረረች በኋላ “ከዓለም አቀፍ መድረኮች ከመገለል እንድትወጣ” እንዲረዳት ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።

“ከሩሲያ ጋር የንግድ ግንኙነታቸውን ለመቀጠል ፈቃደኛ የሆኑ የባሕረ ሰላጤው አገራት ያሉ ይመስላል” ብለዋል አቡዱ።

ቭላድሚር ፑቲን እና የኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃሚድ አል-ታኒ
የምስሉ መግለጫ,ቭላድሚር ፑቲን እና የኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃሚድ አል-ታኒ

ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ ጋዛን እያስተዳደረ የሚገኘው ሐማስ በሚከተለው እስላማዊ ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ሩሲያ የምትመርጠው የፍልስጤም አጋር ሆኖ አያውቅም።

ይህ ግን ሩሲያ ከቡድኑ ጋር ከመሥራት እንድትቆጠብ አላደረገም። ግንኙነቷን እንድትጠቀምበትም አላደረገውም።

ፑቲን ከሐማስ ጋር ግንኙነት እንዲመሠርቱ ከገፋፋቸው ምክንያቶች አንዱ “በሩሲያ ውስጥ በተለይም በቼቺኒያ የሚገኙ የጂሃዲስት ቡድኖችን እንደማይደግፉ ለማረጋገጥ ነው” ብለዋል ፕሮፌሰር ካትስ።

ስትራቴጂው ውጤት አስገኝቷል። ሩሲያ እአአ በ2008 ጆርጂያን በወረረችበት ወቅት “ሐማስ እና ሄዝቦላህ በጆርጂያ ዙሪያ የሩሲያን አቋም ይደግፉ ነበር” አክለዋል።

ሞስኮ ከሐማስ ጋር ያላት ግንኙነት ቢቀጥልም ለቡድኑ መሳሪያ ስለመላኳ አልተረጋገጠም። ለዚህ አንደኛው ምክንያት እስራኤልም በተመሳሳይ መንገድ ዩክሬንን እንዳታስታጥቅ ስልምትፈልግ ነው ብለዋል ተመራማሪዎች።

የተለያዩ ስልቶች

ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ዢ
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ዢ

አንዳንድ ግቦቻቸው በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ እና በደቡብ የዓለም ክፍል ያለውን የአሜሪካ ተጽዕኖን ከማዳከም አንጻር ተመሳሳይ ሊሆኑ ቢችሉም ቻይና እና ሩሲያ ግን በጣም የተለያየ ዘዴ ይከተላሉ።

የመጀመሪያው ሩሲያ በሶሪያ ጦርነት እንዳደረገችው በአካባቢው ወታደራዊ ተሳትፎ አድርጋለች። ቻይና ግን ተመሳሳይ ፍላጎት የላትም።

ቻይና ከፍላጎቷ ጋር በሚስማማ መልኩ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ቀጣናዊ ሥርዓት ለማስጠበቅ ትፈልጋለች። ሩሲያ በበኩሏ ግን “ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እና የሩሲያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንደገና ለማዋቀር ትፈልጋለች” ሲሉ አቡዱ ተናግረዋል።

ቻይና ከፍተኛ ተጽዕኖ የምታሳድርበት የፍልስጤም መንግሥት ተመሥርቶ ግጭቱ እንዲፈታ ቤይጂንግ ትፈልጋለች ብለዋል።

ክሬምሊን ደግሞ ሌሎች ፍላጎቶች አሏት። ሞስኮ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ያለው ግጭት እንዲፈታ አትፈልግም። ከዚያ ይልቅ መፍትሄ ፈላጊ ለመምሰል ነው የምትጥረው ሲሉ አቡዱ ያብራራሉ።

“ችግሩ መፍትሄ ካገኘ ሁለቱም ወገኖች [እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን] ሩሲያን ለምንም ነገር አይፈልጓትም። ሁለቱም ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ይሠራሉ። ለዚህም ወደ ምዕራቡ ዓለም ወይም ወደ ቻይና ወይም ደግሞ ወደ ሁለቱም መዞር ይጠበቅባቸዋል።”

“ሩሲያ ባለው አለመረጋጋት ትጠቀማለች። ይህ ግን የከፋ ከሆነ አትጠቀምም። ማሰሮው እንዲፈላ እንጂ እንዳይንተከተክ ይፈልጋሉ” ብለዋል ፕሮፌሰር ካትስ።