ዋሽንግተን የሚገኘው የኤፍቢአይ ዋና መስሪያ ቤት

ከ 7 ሰአት በፊት

በዩናይትድ ስቴትስ የምርጫ ዕለት በኢስላሚክ ስቴት ቡድን ስም ጥቃት ለማድረስ አቅዶ ነበር ያለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአገሪቱ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

ተጠርጣሪው ናስር አህመድ ታውሄዲ የሚባል የ27 ዓመት የአፍጋኒስታን ዜጋ ሲሆን በኦክላሆማ ነዋሪ መሆኑን ዓቃቤ ህግ ተናግሯል።

“ተከሳሹ በአይኤስ አነሳሽነት፣ በምርጫ ቀን፣ በአገራችን ላይ የኃይል ጥቃት ለመፈጸም አሲሯል” ሲሉ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ሬይ ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ግለሰቡ የጦር መሳሪያዎችን ለማጠራቀም እየሞከረ መሆኑን ኤፍቢአይ ገልጾ፤ የቤተሰቡን ንብረት በመሸጥ እነሱን ወደ ሌላ አገር ለማዛወር እርምጃ ወስዷል ብሏል።

ታውሄዲ ለውጭ አገር አሸባሪ ድርጅት ድጋፍ ወይም ግብአት በመስጠት፣ ለማቅረብ በመሞከር፣ የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን ለመግዛት በመሞከር ወንጀል ወይም የሽብር ድርጊት ለመፈጸም በማሴር ነው የተከሰሰው።

ኤፍቢአይ እንዳለው ከሆነ ታውሄዲ ስሙ ከማይታወቅ ተባባሪ ዘመዱ ጋር ይሠራ ነበር። ተባባሪው ወጣት እና የአፍጋኒስታን ዜጋ መሆኑም ተገልጿል።

በሕግ አስከባሪ አካላት በተገኙ የጉግል መዛግብት ላይ ተመስርተው ባገኙት ማስረጃም የኢስላሚክ ስቴት ፕሮፓጋንዳዎችን በኢንተርኔት እየተከታተለና እና ለአይኤስ ደጋፊ ሆኖ ለሚሠራው የበጎ አድራጎት ድርጅት ገንዘብ በመለገስ ተከሷል።

“አይኤስአይኤስ እና ደጋፊዎቹ በአሜሪካ ብሕራዊ ደህንነት ላይ የሚያደርሱትን ቀጣይነት ያለው ስጋት መዋጋት እንቀጥላለን። የአሜሪካን ህዝብ ለማሸበር የሚሞክሩ ግለሰቦችን ለይተን እንመረምራለን እንዲሁም ለህግ እናቀርባለን” ሲሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ ተናግረዋል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው ከሆነ ታውሄዲ ዋይት ሃውስን እና የዋሽንግተን ሃውልትን የሚያሳዩ በዋሽንግተን የሚገኙ የስለላ ካሜራዎችን በተመለከተ ጥናት ማድረጉን የፌደራል መርማሪዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም የላላ የመሣሪያ ህግ ያላቸውን ግዛቶች በተመለከተም ጥናት አድርጓል።

ታውሄዲ ጥቃቱን ለመፈጸም ኤኬ-47 ጠመንጃዎችን ለመጠቀም ፈልጎ ነበር ሲሉ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

መስከረም 26 እሱ እና ተባባሪው የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶቹን ለመግዛት ለኤፍቢአይ በድብቅ ከሚሰሩና የመሣሪያ ነጋዴዎች መስለው ከቀረቡት ግለሰቦች ጋር ተገናኝተዋል።

መሣሪያውን ከገዙ በሏላም ታውሄዲ እና ተባባሪው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሰኞ ዕለት ከታሰረ በኋላ በተደረገ ምርመራ ታውሄዲ በምርጫ ቀን “በርካታ ሰዎች በተሰበሰቡበት” ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ለመፈጸም ማቀዱን እና ይህንንም በመፈጸም ለመሞት መዘጋጀቱን ለኤፍቢአይ አረጋግጧል ተብሏል።

ታውሄዲ እአአ መስከረም 2021 በልዩ የስደተኛ ቪዛ ከባለቤቱ እና ከልጃቸው ጋር አሜሪካ ገብቷል። በተያዘበት ጊዜም በኦክላሆማ ሲቲ ይኖር ነበር።

የሕጋዊ ውኪሎች ይኑሩት አይኑሩት የሚታወቅ ነገር የለም።