ከ120 ሚሊዮን ቁጥር በላይ ሕዝብ ያላት አገር ለዚህ ግዙፍ ለሆነ የቁጥጥር ሥርዓት በተለይም ደረጃ-3 የተባለውን መሥፈርት ላይ ከመድረስ አኳያ በጣም መሥራት ይጠበቅባታል::

ቢዝነስ

ኤልያስ ተገኝ

October 9, 2024

ከዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው በመድኃኒት ዋጋ ከፍተኛ መሆን የተነሳ ችግር ላይ እንደሚወድቅ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየናረ ከመጣው የመድኃኒት ዋጋ አንጻር በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ማኅበረሰቡ ቢጠቀም ተመራጭ ነው የሚል ምክረ ሐሳብ በተደጋጋሚ ሲሰነዘር ይደመጣል፡፡

ምንም እንኳን መንግሥት በአገር ውስጥ የሚመረቱ የመድኃኒቶች ውጤቶች በኅብረተሰቡ እንዲለመዱና የገበያ ድርሻቸውም ከፍ እንዲል ቢፈልግም፣ ነገር ግን ሒደቱ በአገሪቱ ላይ በቂ የጥራት ቁጥጥርና ፍተሻ የሚደረግባቸው ማዕከላት ባለመኖራቸው የቁጥጥር ከባቢውን ጎዶሎ እንዳደረገው፣ ይህም የጥራት ደረጃቸው የተረጋገጡ በአገር ውስጥ የተመረቱ የመድኃኒት ውጤቶች በበቂ ሁኔታ ለገበያ እንዳይቀርቡ እንቅፋት ስለመሆኑ የሚናገሩም አሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር 21ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ በኢሊሌ ሆቴል ባካሄደበት ወቅት የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ዘርፉን ለማሳደግ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር ማኅበሩ አሁናዊ ያላቸውን ችግሮች መነሻ በማድረግ በቀጣይ አምስት ዓመታት በስትራቴጂካዊ ዕቅድ መመለስ የሚገባቸውን ጉዳዮች የተመለከተ የዳሳሰ ጥናት ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ማኅበር የቦርድ አባልና የአፍሪ ኪዩር መድኃኒት መሥራችና ባለቤት ታደሰ መኮንን  (ዶ/ር)፣ ማኅበሩ እ.ኤ.አ. ከ2025-30 ባለው ጊዜ ሊተገበር ስለታቀደው ረቂቅ የስትራቴጂክ ዕቅድ ገለጻ አቅርበዋል። በውቅቱ ባደረጉት ገለጻም፣ መንግሥት ለፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኛ በሆነበት በዚህ ሰዓት አምራች ኢንዱስትሪው በስትራቴጂ የማይመራ ከሆነ ህልውናው አደጋ ላይ ይወድቃል ብለዋል፡፡

መድኃኒት የመልካም አመራረት ተግባርን ተከትሎ ካልተመረተ፣ የጥራትና ደረጃ ሒደቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ወደ ውጭ ምርት የመላክ ዕቅዱ ቀርቶ በኢትዮጵያ ውስጥ ያመረተውን የመሸጥ እንኳን ችግር እንደሚገጥመው ታደሰ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

‹‹እንደ ኢንዱስትሪ አምራች ባለቤትነታችን አንድ ልናውቀው የሚገባ ነገር ሰፊ ጉድለቶች እንዳሉብን ነው፤›› ሲሉ ያስረዱት የቦርድ አባሉ ‹‹14 ከሚደርሱት የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ፋብሪካዎች በአገር አቀፍ ደረጃ የጥራትና ደረጃ ሒደትን በትክክል የሚያሟሉት አምስት የሚደርሱ ናቸው›› በማለት ገልጸዋል፡፡

– Advertisement –

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውንና ፈዋሽነታቸውን በማረጋገጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡

በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመድኃኒት አምራቾች ኢንስፔክሽንና ሕግ ማስፈጻም ክፍል መሪ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ጌታቸው ገነቴ እንደሚሉት፣ ከውጭ የመጣም ይሁን በአገር ውስጥ የተመረተ አንድ መድኃኒት ማሟላት ያለበት ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም ጥራቱን የጠበቀ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሁም ውጤታማ (Effective) መሆን ናቸው ሲሉ አስረድተዋል።

ታደሰ መኮንን (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ ለአንድ የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና አምራች ኢንዱስትሪ ጂኤምፒ (Good Manufacturing Practice-GMP) ኮምፕሊያንስ የሚያስፈልገው ከምንም በላይ ለመንግሥት ሳይሆን ለአምራቹ ለራሱ ነው፡፡ አምራቹ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርት ካላመረተ ያመረተውን ምርት የሚሸጥበት ገበያ እንደማያገኝ፣ ስለሆነም ይኼን ማሟላት የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

በእንግሊዘኛው ምሕፃረ ቃል ጂኤምፒ ተብሎ የሚጠራው መመሪያ ወይም መሥፈርት ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራትና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ መመረታቸውን የሚመለከት ነው፡፡ ጂኤምፒ መድኃኒቶች በቋሚነት የሚመረቱ፣ ለታለመላቸው ጥቅም በሚስማማ የጥራት ደረጃ በግብይት ፍቃድ ወይም የምርት ስፔሲፊኬሽን መሠረት መሆኑን የሚያረጋግጥ የጥራት ማረጋገጫ ነው፡፡

አንድ የተመረተ የመድኃኒት ውጤት ሲመዘገብ ማሟላት ያለበት ጉዳይ እንዳለ ያስረዱት አቶ ጌታቸው፣ ለምሳሌ አገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ተፈላጊ መረጃዎች ሳይኖራቸውና ሳይታወቁ ለተጠቃሚዎች የሚደርሱበት ሁኔታ እንደሚስተዋል ባቀረቡት ገለጻ አስታውቀዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንደተገለጸውም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ የጂኤምፒ መሥፈርትን አያሟላም።

የዓለም አቀፍ ፋርማሱቲካል አቅርቦት ሰንሰለት በየጊዜው መቀያየር የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራችና ኢንዱስትሪውና ቁጥጥሩ ላይ የራሱ የሆነ ጉልህ ተፅዕኖ እንዳለው አቶ ጌታቸው ሌላው ያከሉት ጉዳይ ነው፡፡

የመድኃኒት ዋጋ በየጊዜው መናርና ተጠቃሚዎች ሌሎች አማራጮችን መፈለጋቸው የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪው ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንዳለው የኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ማኅበር ባካሄደው የ21ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፋብሪካዎች የጥራት ደረጃቸውን አሻሽለው የሚቀርቡ ከሆነ 120 ሚሊዮን የሚደርሰው ሕዝብን ጨምሮ ያልተነካው የምሥራቅና የአፍሪካ ገበያ ትልቅ ዕድል እንደሆነ ታደሰ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡

በአፍሪካ የፋርማሱቲካል አምራች ኢንዱስትሪ እንደ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ ለመሆን የኢንዱስትሪው ባለቤቶች ዘላቂነት ያለው ምርት ማምረት፣ አዳዲስ ግኝቶች እንዲሁም ምርት ወደ ውጪ የመላክ ጉዳይ ላይ አበክረው ሊሠሩ ይገባል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በ268 ንዑስ አመላካች ነጥቦች ተቆጣጣሪ አካላትን እየፈተሸና እየገመገመ በተለያየ ደረጃ እየከፋፈለ የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ በአግባቡ የተዋቀረ፣ የቁጥጥር ሥርዓት ያለው ተቋም ከሆነ ቢያንስ ደረጃ-3 የሚባለው መሥፈርት ላይ ያስቀምጠዋል፡፡

አቶ ጌታቸው እንደገለጹት፣ በአፍሪካ አራት አገሮች ‹‹የማቹሪቲ ደረጃ-3›› በመድኃኒት ቁጥጥር ዙሪያ አግኝተዋል፡፡ እነዚህም ታንዛኒያ፣ ጋና፣ ናይጄሪያና ዚምባቡዌ ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካና ግብፅ በክትባት ቁጥጥር ደረጃ-3 ያገኙ አገሮች ናቸው፡፡

ከ120 ሚሊዮን ቁጥር በላይ ሕዝብ ያላት አገር ለዚህ ግዙፍ ለሆነ የቁጥጥር ሥርዓት በተለይም ደረጃ-3 የተባለውን መሥፈርት ላይ ከመድረስ አኳያ በጣም መሥራት ይጠበቅባታል፡፡

‹‹ማቹሪቲ ሌቭል-3›› ማሟላት ስላለው ጥቅም በቂ ግንዛቤ አልተፈጠረም›› የሚሉት የኢንስፔክሽንና ሕግ ማስፈፀም ክፍል መሪው፣ ጂኤምፒ የሚባለውን ቅድመ ሁኔታ በመጥቀስ ነው፡፡ ይህ መሥፈርት ጥራቱን የጠበቀ፣ ደኅንነቱን የተጠበቀና ውጤታማ መድኃኒት ለኅብረተሰቡ መቅረብ አለበት የሚለውን አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃ በማጣቀስ ነው፡፡

አንድ የመድኃኒት ምርት ከደረጃ በታች የተመረተ መሆኑን ተከትሎ በረከሰ ዋጋ ለገበያ በሚቀርብበት ወቅት፣ ኅብረተሰቡ በዋጋ ወደድ ያለውን ምርት ወደ ጎን የመተው ሒደቶች እንደሚፈጠሩ የሚገልጹት አቶ ጌታቸው፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ጥራት፣ ደኅንነትና ሌሎች ደረጃዎችን ሳያሟሉ ለገበያ የሚቀርቡ መድኃኒቶች ዋጋቸው ብዙውን ጊዜ እንደሚረክስ ይህንንም አማራጭ የሚያደርግ ኅብረተሰብ ሊኖር እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች ተሞክሮም የሚያሳይ ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮችን ለመቅረፍና የአገር ውስጥ የመድኃኒት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ቅንጅት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ኢንዱስትሪው ከመንግሥት፣ መንግሥት ከኢንዱስትሪው እንዲሁም ኢንዱስትሪው ከሌሎች ተቋማት መቀናጀት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

የጉባዔው ተሳታፊዎች እንዳስታወቁት፣ የአገር ውስጥ መድኃኒት ኢንዱስትሪው የጥራት ቁጥጥር ሥርዓት፣ የጥሩ ምርት አመራረት ሒደት፣ የአቅም ግንባታ ለተመለከቱ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት አለበት፡፡

አቶ ጌታቸው ለሪፖርተር እንዳስታወቁት የመልካም ምርት ተግባር የአገር ውስጥ የመድኃኒት ኢንዱስትሪው የአንድ ጊዜ ተግባር ሳይሆን በአጠቃላይ ቀጣይነት ያለው ሊሠራበት የሚገባ ነው፡፡ ተቆጣጣሪውም ሆነ ድጋፍ የሚያደርገው አካል የጤና ሚኒስቴር ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉበት የሚገባ ነው፡፡

ኢንዱስትሪው የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን ተግባራዊ እያደረጉ መሥፈርቶችን የማሟላት ሥራዎች መሠራት ይገባዋል፣ በዚህ ረገድ የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪው ጥሩ ደረጃ ላይ ነው የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ መሥፈርቱን ለማሟላት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ፣ በቀጣይ በአጭር ጊዜ የጂኤምፒ መሥፈርቱን አሟልተው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ ሒደት ውስጥ ይገባሉ የሚል ተስፋ አለ ብለዋል፡፡

የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪ እንደ ሌሎች አገሮች ሒደታዊ በሆነ መለኩ ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀለት ሲሆን ያንን ታሳቢ በማድረግ አምራቾች ችግሮቻቸውን እየቀረፉ ቅድመ ሁኔታ (መሥፈርት) እንዲሟላ በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይገልጻል፡፡

የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ (Africa Medicine Agency) እየተቋቋመ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ ጌታቸው፣ ይኼ ደግሞ ቁጥጥሩ በአኅጉር ደረጃ ስለሚሆን ለዚያ ዝግጁና ተወዳዳሪ መሆን ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾች እንደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ ካሉ አገሮች የመድኃኒት አምራቾች ጋር መወዳደር ግድ እንደሚሆንባቸው የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ መሥፈርት ያስገድዳል፡፡ ይህም ቁጥጥሩ በአኅጉር ደረጀ እንዲሁም የሌሎች አገሮች ተቆጣጣሪዎች ግምገማውን ስለሚያካሂዱት ነው፡፡

በጉባዔው ላይ ተሳታፊ የሆኑ አስተያየት ሰጪ የኢትዮጵያ የመድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪ ተዋንያን ያሉበትን የአመራረት ሒደት በግልጽ ስለሚያውቁት የጂኤምፒ ኮምፕሊያንትን ተግባራዊ ካላደረጉ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችሉ ሊረዱ ይገባል ብለዋል።