ልናገር የዘመመችው የመምህራን ጎጆ
ቀን: October 9, 2024
በአንዋር አወል ሞ.
ባሳለፍነው ሳምንት አነጋጋሪ ከነበሩ ማኅበራዊ ጉዳዮች አንደኛው ቢቢሲ የአማርኛው ክፍል ዕጩ ዶክተሮች የሚገፉት አሰቃቂ ኑሮን አስመልክቶ የሠራው ዘለግ ያለ ሐተታ ነበር፡፡ ጽሑፉን ተከትሎም አዳሜ ለአንድ ለሦስት ቀን ሌላ አጀንዳ አልነበረውም፡፡ አብሶ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ‘ኤጭ! አሁንስ በዛ!’ እስክንል ድረስ አየሩን የተቆጣጠረው ርዕሰ ጉዳይ እሱ ነበር፡፡
እርግጥ ነው፣ ዘገባውን የሠራው ጋዜጠኛ (ቡድን) መረጃ የሰበሰበበት መንገድ፣ ለናሙናነት የመረጣቸው ባለጉዳዮች፣ እንዲሁም ትዕግሥቱን አለማድነቅ አይቻልም፡፡ በአናቱ፣ ስሜትን ሰቅዞ የሚይዝና መከተብ ካልቀረስ እንደዚህ ነው የሚያስብል የሥነ ጽሑፍ ክህሎትን አሳይቶናል፡፡ ስለጫማቸው መንሻፈፍ፣ ሥጋና ትሪያቸው ከተነካኩ ዘመናት ስለመቆጠራቸው፣ አንሶላ እንኳን ከአቅሟ ወደ ቤት አጀንዳነት ስለመጎኗ፣ ተማሪ ሆኖ መጎበዝ የ‘ቁጭት’ ምንጭ ስለሆነበት አጋጣሚ፣ የሙዝ በዳቦ ዘውታሪ ደንበኝነት፣ ፒኤችዲ ከመማር ባጃጅ መንዳትን አስበልጦ ዲዜርቴሽኑን ጥሎ ስለጠፋው ሰው፣ ማትሪክን ፈትነው ለሚያገኟት አበል ሲሉ ያለው መራኮትና ወደፊት መምህርነት ሙያው ላይ አደጋ የማንዣበቡን ነገር በህሊናችን እንዲታተም አድርጎ አስነብቦናል፡፡
እኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር እንደመሆኔ፣ መጀመርያ ላይ ጽሑፉን ሳነበው ‘If the lion feels the heat, the ant will burn.’ (የእሳቱ ግለት አንበሳውን ከተሰማው፣ ቁጫጩ’ማ መንደዱ ነው) የሚል አባባልን ተገን በማድረግ ችላ ብዬው ነበር፡፡ በኋላ ግን ማኅበራዊ ሚዲያው የያዘው ቤት የማይመታ አቋም ሳይ እኔም የራሴን ባንፀባርቅ ከአቋሞቹ እንደ አንዱ ቢያዝ እንጂ፣ ለክፉ እንደማይሰጥ ተገነዘብኩና በዚህ ዙሪያ ልጽፍ ተነሳሁ፡፡
መጀመሪያ ግን በዕጩ ዶክተሮቹ ላይ ጠብ እርግፍ ተብለው ከተጻፉት መካከል አንድ ሁለቱን መርጬ አንድ ሁለት ነገር ልበልባቸው፡፡
- ‘ቀድሞ ነገር፣ በገበያው የማይፈለግ ትምህርትን ለምን ተማሩ?’
- ‘ለራሱ ያልሆነን ሰው ለትውልድ ምን ይፈይዳል? የማጀት ችግሩን ያልተወጣስ እንዴት የአደባባዩን እንዲፈታ እንጠብቅ?’
ለአንደኛው ጉዳይ የሚኖረኝ መልስ ሦስት ነው፡፡
ሀ. እኔ በዕድሜዬ እስከማውቀው ድረስ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ገበያ ተኮር የትምህርት ዘርፍ የመምረጡን ዕድል ያገኙት ሰሞነኞቹ ‘ጄንዚዎች’ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነሱ ቀደም ብለን ማትሪክ የወሰድነው ሁሉ (ከ’ሜጋ’ዎቹ በስተቀር) የመደቡንን ካምፓስ ድረስ ተጉዘን፣ የሰጡንን ‘ፊልድ’ አሜን ብለን በመቀበል እናቶቻችንን ስለመጦር ከማሰብ ውጪ የገበያው ምኅዋር ወደ ቀኝ ይሽከርከር ወደ ግራ ዕውቀቱ አልነበረንም፡፡ ራሴን እንደ ምሳሌ ብወስድ የመጀመሪያ ዲግሪዬን አግኝቼ ወደ ሥራ ዓለም እስክደባለቅ ድረስ፣ ዲግሪ የተባለ ሁሉ አንድ ዓይነት ደመወዝ የሚበላና እኩል የመመንደግ ዕድል ያለው ይመስለኝ ነበር፡፡ ማንም አብራርቶ የነገረኝ አልነበረምና በእኔ አይፈረድም፡፡
ለ. ወዳጄ ሆይ! ያረጀ ካርታ ታውቃለህ? የድሮ ስለሆነ ዛሬ ላይ ሕንፃ በሕንፃ የሆነ መልክዓ ምድርን እየጠቆመ በዚህ አቋርጠህ እለፍ ይልኻል፡፡ ‘ስፓይደር ማን‘ ካልሆንክ በስተቀር ግን በእሱ ማለፍ አትችልም፡፡ አንዳንድ ዲግሪዎች ይኼው ናቸው፡፡ የሆነ ወቅት ላይ በባትሪ ይፈለጉ ነበር፡፡ ያ ወቅት አልፎ በከተማው ድንገተኛ አፈሳ አድርገህ የአሥር ሰውን ኪስ ብትበረብር ስምንቱ ያንን ዲግሪ ይዘው ልታገኛቸው ትችላለህ፡፡ የእነዚህ ችግር ከሀሌታው ሀዎቹ ችግር ይለያል፡፡ እነዚህ ሲማሩ የገበያውን ግራ ቀኝ አጥንተው ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ዲግሪያቸውን አጠናቀው ልክ መነሳንሳቸውን እንዳዞሩ የተማራችሁት ዲግሪ በገበያው ፈላጊ የለውም የሚል መርዶ ተነገራቸው፡፡ በጣም በአጭሩ የዲግሪ ‘ፕራንክ!’ ተሠሩ እንደማለት ነው፡፡
በዕውቀቱ ሥዩም በአንዱ ግጥሙ ላይ፡-
አዳም ተማረረ፣ ተማረረና ተመራመረ
ተመራምሮም አልቀረ፣ ጋቢ መሥራት ጀመረ
ጅማሬውን ወደደ
ተጀምሮ እስኪፈጸም የዕድሜው ግማሽ ወሰደ
ያሳዝናል! ጋቢውን ጨርሶ ሲቋጭ ገላው ብርዱን ለመደ
ይላል፡፡ ግጥሟ ለእኔው ወሬ ልክክ ያለች ትመስለኛለች፡፡ ምክንያቱም አዳም ከሽመናው ‘ጋቢ’ የተባለ ሸክም እንደተረፈው ሁሉ የምስክር ወረቀቱም ለዚህኛው ባለዲግሪ የሚጠቅመው ነገር አይኖርም፡፡ ግጥሙ ቀርቶ በስድ ንባብ ይጠናከር ከተባለም ይህንን ጉዳይ የሚገልጽ ዓይነተኛ ምሳሌ አናጣም፡፡ ከዓመታት በፊት መንግሥት በትምህርቱ መንደር ‘ሰባ ሰላሳ’ የሚባል ቋንቋ አመጣ፡፡ በሰባው ተፈጥሮ ሳይንስ ላይ በአጠቃላይ፣ ምህንድስናንና ቴክኖሎጂ ላይ ደግሞ በተለይ ትኩረት አድርጌ እሠራለሁ አለ፡፡ የማኅበራዊ ሳይንሱ ዘርፍ ለአገር ግንባታ ጠብታ ጥቅም እንደሌለው ተደርጎ ወደ ጎን ተገፋ፡፡ በወቅቱ በሚስቱ አልፈልግህም የተባለ አንድ ሰውዬ እንኳን ‘ሶሻል‘ የሚል የሹክሹክታ ቅፅል እንደተሰጠው አስታውሳለሁ፡፡ አሥር ዓመት ቆይቶ መንግሥት ሆዬ (የአስፈጻሚዎቹ ለውጥ እንዳለ ሆኖ) አንድ መቶ ሰማንያ ዲግሪ ቀኝ ‘ኋላ ዞሮ’ ሰባ ሰላሳው የአገሪቱን አቅም ሳያገናዝብ በምርቃና (‘ምርቃናው’ እኔ ያከልኩት) የተወሰነ ነበር’ አለ፡፡ ታዲያ በመንግሥት ‘ምርቃና’ ብዙ ሰው ‘ፕራንክ’ አልተሠራም ወይ?
ሐ. በዕድል ደረሳቸው እንዳይባል መርጠውታል፣ ‘መንግሥት ተጫወተባቸው’ እንዳይባልም መንግሥት ለዚያ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ሳይጨምር ሳይቀንስ ከቋሚ ትኩረቱ ጋር ቆርቦ ዘልቋል፡፡ ይኼኛው ብዙ ጊዜ አንድን ሙያ ከማፍቀርና እዚያው ዘርፍ ላይ የረዥም ጊዜ ሕልምን ሰንቆ ከማዝገም ጋር የተቆራኘ ምርጫ ነው፡፡ ምድባችን እዚህኛው ላይ ነው የሚሉ ሰዎች ለቢቢሲ አማርኛ ቀርቶ ለፈጣሪም በዚህ ሙያ ሆድ ባሰኝ ብለው በለሆሳስ የማያማርሩ ዓይነት ፅኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ‘ወደሽ ከተደፋሽ፣ ቢረግጡሽ አይክፋሽ’ እንደሚባለው ‘ደስ የሚል ስቃያቸውን’ ያጣጥማሉ (አኃዙ ከሚሊዮን አንድ ሊሆን ይችላል እንጂ ሳይንሱ እንዲህ ዓይነት ሰው አለ ይላል)፡፡
ወደ ሁለተኛው ጠብ እርግፍ ጥያቁ ልለፍ፡፡ ግን አንደኛውን ሳብራራ ትንሽ በመቆየቴ ሁለተኛውን ጥያቄ ረስታችሁት ሊሆን ስለሚችል ከላይ ኮፒ አድርጌው ልምጣ እዚሁ ጠብቁኝ፡፡
‘ለራሱ ያልሆነን ሰው ለትውልድ ምን ይረባል? የማጀት ችግሩን ያልተወጣስ እንዴት የአደባባዩን እንዲፈታ እንጠብቅ?’
እውነት ለመናገር ይህኛው አስተያየት ትንሽ አበሳጭቶኛል፡፡ መጀመሪያ ላይ በግል እንደተሰነዘረብኝ ስድብ ነበር የወሰድኩት፡፡ ለምን ብትሉ የመምህር ኑሮ ሁሌም ቢሆን ከቅድስና ተፈጥሮው በታች ስለሆነ ነው፡፡ ብዙዎቹ ነቢያት፣ ታዋቂ ፈላስፎች፣ ዝነኛ የርዕዮተ ዓለም ቀማሪዎችና ደራሲዎች በልቶ ማደርን እንደ ብርቅዬ ነገር ‘ሰለብሬት’ የሚያደርጉ ድሆች ነበሩ፡፡ ጉልበታችንን ሸጠን እንደር ቢሉ የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ ለማግኘት ከሰው አንሰው ሳይሆን ከሙያቸው ጋር ድብን ያለ ፍቅር ስለያዛቸው ነው፡፡ ፍቅር ደግሞ ዕውር ነው ይባላል፡፡ ኒቼና ካንት፣ ኦርዌልና ዶስቶዬቭስኪ የፈጠሩትን ተፅዕኖ ያህል ተቆራምደው ስለማለፋቸውም ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የመምህራኑም ነገር በተመሳሳይ ሌንስ ቢታይ እላለሁ፡፡ ኪሳቸው ብር የለውም ማለት ግን ለትውልድ የሚያበረክቱት ነገር የላቸውም ከሚለው ጋር ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ ማጀታቸው በችጋር የተጠበሰ ነው ማለትም ብሔራዊ ባቡሩን የሚጓዝበት ሐዲድ ማመላከት አይችሉም የሚለውን አያስይዝም፡፡
ብዙዎቹ የዶክትሬት ተማሪዎች ‘ቲኔጀር‘ ሆነው ካምፓስ እንደገቡ በዚያውም ሳይወጡ የቀጠሉ ናቸው፡፡ አንዴ እዚያው ‘ሰቅለው’ ተመረቁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ‘አገልግሉኝ’ ብሎ አስቀራቸው፡፡ ትንሽ እንደሠሩ ሁለተኛ ዲግሪ ተምረው እንዲመጡ የሆነ ቦታ ተላኩ፡፡ እንደገና ‘ሰቅለው’ ተመረቁ፡፡ እነሆ አሁን ቢቢሲ ያገኛቸው ለሦስተኛ ዙር ተልከው አሳራቸውን ሲበሉ ነው፡፡
በመሠረቱ፣ በሌላው ዓለም ላይም ቢሆን የዲግሪው አውራጃና የሳንቲሙ አውራጃ ለየቀል ነው፡፡ የሳንቲሙ አውራጃ የራሱ ጥናት፣ የራሱ ጉብዝናና የራሱ ‘ሰቃይ’ አለው፡፡ ካምፓስ ሁሉም ሰቅሎ እንደማይወጣው ሁሉ እዚህ ላይም ሁሉም አይሰቅልም፡፡ ፋይናንሳዊ ሰኬት የሚመራው ራሱን በቻለ ልዩ ‘ስትራቴጂ’ ነው፡፡ ጂም ሮን የተባለው ታዋቂ ሥራ ፈጣሪ ሰውዬ ‘Formal education will make you a living; self-education will make you a fortune’ ይላል፡፡ በግርድፉ ወደ አማርኛ ስመልሰው ‘መደበኛው አስኳላ እስትንፋስህን ያቆይልኻል፣ ራስህን ማሠልጠን ግን ዕጣ ፈንታህን ያስወስንኻል’ እንደማለት ነው፡፡ ይኼኔ ጨዋው አንባቢ፣ አንተ ምን ብታካብት ነው ምክርህን እንዲህ የምታዥጎደጉድብኝ? ሊለኝ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ መልሴ ‘ምንም’ ነው፡፡ ነገር ግን መርሁ እኛ አልተመራንበትም ማለት አይሠራም ማለት አይደለም፡፡ ‘ዘ ሲክሬት’ ውስጥ ‘ከአንድ ከፍ ያለ ሕንፃ ላይ ሳት ብሎህ ብታመልጥ፣ አንተ ክፉም ሁን ደግ ሰው ከመሬት ጋር መላተምህ አይቀሬ ነው’ የምትል ዋዛ አለች፡፡ እዚህም እንደዚያው ነው፡፡
በመጨረሻም
መንግሥት ሆይ! ‘መምህርነት የሙያዎች ሁሉ ቁንጮ ነው’ ብለህ አማርኛውን በወርቅ ቅብ ከምታሳብደው ትንሽዬ ወደ ኪስ የምትገባ ብር ልቀቅ፡፡ በውጭም በአገር ውስጥም ያሉ ‘የቤት ሠራተኞች’ን መብት ለማስከበር ጥብቅና እቆምላቸዋለሁ የሚል አካል እንዴት የገዛ ሠራተኞቹን መብት ማክበር ተሳነው? ካዝናው ብዙ ወጪ ኖሮበት እንደ ልብ ላይደግፍ ይችል ይሆናል፡፡ በትግርኛ ‘ከሌላት እናትም ከአለት ትጠናለች’ ይባላል፡፡ እውነተኛ ምክንያቱ ያ ዕጦት እንኳን ከሆነ ምሁራኑን ጠጋ አድርጎ ማነጋገሩ ማንን ገደለ? ነው ወይስ ሰቆቃው መንግሥትም ከእኛ እኩል ዘገባውን አንብቦ ነው ያወቀው? እንዲያ ከሆነ መቼስ ‘ገርሞኝም አያባራ!’ (እንዲል ስብሐት)፡፡
መምህራን ሆይ! ዘገባውን ሳነብ አንዱ መምህር እንዲህ ብሏል፡፡ ‘ኢኮኖሚያቸውን ፈርጠም ካሉ የቀድሞ ወዳጆቼ ጋር ድንገት መንገድ ቢያገናኘን፣ እግሬ አውጪኝ ብዬ እፈረጥጣለሁ’ (ቃል በቃል አይደለም)፡፡ ምን የሚያስሮጥ ነገር አለ? የብር ክምር ኖሮን በሱስና በቁማር አልናድነው፡፡ ታዲያ ለምን እንሸሻለን? የመምህር ገቢ እንደሆነ ይታወቃል፣ ኑሮው መገመትም ቀላል ነው፡፡ ከአቅማችን በላይ ከተጠየቅን እዚያው ፊት ለፊት ‘አቅሜ አይፈቅድም’ ማለቱ ይከብዳል? ጉልበት ያለው ግልጽነት’ማ ይኑረን እንጂ፡፡ ጭራሽ ለሰው ብለን ኑሯችንን ከድጡ ወደ ማጡ እንስደደው እንዴ ደሞ? ይልቅስ ድብብቆሹ ቀርቶብን ‘ያለፈለት’ የቀድሞ ጓዳችን ዘንድ ጠጋ እንበል፡፡ አጠያየቃችን አሳምረንም ጊዜያዊ የችግር መፍቻ ሥልትና እስከወዲያኛው የሚሆን ዘዴም ክብራችንን ሳናስነካ እንቅሰም፡፡ የፎርድ ሞተር ኩባንያ መሥራቹ ሄንሪ ፎርድ በቶማስ ኤዲሰን ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ መሥራቱ አንድ ነገር ነው፡፡ ፎርድ የራሱን ኩባንያ ሲያቋቁም ኤዲሰን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዳደረገለትም በስፋት ይነገራል፡፡ የሁለቱ ነገር፣ ቀሪው ታሪክ ነው፡፡
ተማሪዎች ሆይ! ትምህርት ‘ያዋጣል አያዋጣም’ የሚለው ራሱን ችሎ ገምግሙት፡፡ እዚህ አገር ‘ትምህርት’ የሚል ዋና ርዕስ ካያችሁ ከጎን ‘ሀብት’ የሚል ማነፃፀሪያ ንዑስ ርዕስ በሴኮንዶች ውስጥ እንደሚያጎነቁል ጠብቁ፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ሳይቸግረው ዕውቀትና ገንዘብን እያነፃፀረ የመጣ ማኅበረሰብ ስለሆነ ዛሬም ዞር አለ እንጂ አልሸሸም፡፡ ‘ትምህርት ከማቋረጥና ከመጨረስ?’ ሲል ወጥሮ ይጠይቃችኋል፡፡ ማቋረጥ የተሸናፊዎች አመል ነው ብላችሁ በቀናነት ‘መጨረስ’ ስትሉት የስኬታማ ‘ድሮፕ አውት’ መዓት ይደረድርላችኋል፡፡ መገላገል አምሯችሁ እንደምንም ተሟሙታችሁ ይህን ርዕሰ ስታስጥሉት ጉዳዩ ጃኬቱን ገልበጦ ‘ከመቀጠርና የራስ ሥራ ከመሥራት?’ ሆኖ ይከሰታል፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚሆን ፍቱኑ መድኃኒት የትምህርትን አስፈላጊነት ከምንም ጋራ ሳያስተሳስሩ ነጥሎ መመርመር ብቻ ነው፡፡
ሰላም!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የትምህርት ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡