ልናገር ሰላሳ ሦስት ዓመታት የተሻገረ የብሔር ፖለቲካ የግል ትዝታና ትዝብት በኢትዮጵያ (ግንቦት 1983…

አንባቢ

ቀን: October 9, 2024

በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

 የብሔር ፖለቲካ የትናንት፣ ዛሬና ነገ ትስስር ፋይዳን  የማያገናዝብ ግትር  ኋላቀር ፖለቲካ ነው። ዛሬ ላይ ሆኖ ስለነገው ለመተንበይ ትናንትን ጭምር  ማወቅ ያስፈልጋል። ትናንትን በጭፍን ጥላቻ ማየት ዛሬ የቆምንበትን መሠረት በመናድ ነገን በትክክል የምናይበትን ዓይናችንን ይጋርዳል። ዓይናቸውን የጋረዳቸው ትናንትን ያላወቁ የብሔር ፖለቲካ መሪዎች ስለነገ ከተናገሩት የሚታወሱኝ ሁለተኛ  ትዝታና ትዝብት አሉኝ። በእናንተም ህሊና የሚጉላላ ይመስለኛል።

  1. ጥይት ጩኾበት የማያውቀው የአገራችን ስንዝር መሬት ሁሉ ዛሬ በባሩድ ሽታ ሊታጠን፣ በደም ሊጨቀይ ደርግን ተባብረው ያስወገዱት ሻዕቢያና ኢሕአዴግ አገሪቱን ለሁለት በተካፈሉ ወቅት አስመራና አዲስ አበባ ላይ ሆነው ከእንግዲህ በኢትዮጵያና ኤርትራ መሬት አንዲትም ጥይት አትጮህም ብለው ሻምፓኝ ከፍተው ነበር፣ ግን የሆነውና እየሆነ ያለው በሁለቱም ዘንድ ይታወቃል።
  2. አርሶ አደሩ በባህላዊ ማረሻው እንኳ ማረስ ያልቻለበት ሁኔታ ዛሬ እንዲህ ሊፈጠር፣ በአገሪቱ የተለያየ አካባቢ የነበሩ የቀድሞ ወታደራዊ ኮር መምርያዎች ወደ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ሲቀየሩ (አማራ ክልል ውስጥ ከነበሩት በስተቀር)፣ መድፉን መዶሻ፣ ታንኩን ማረሻ እናደርጋለን ተብሎ በሞቅታ ተደስኩሮ ነበር፡፡ ግን ሁሉም በነበር ቀርቶ ከታንክና መድፍ በተጨማሪ ያኔ ያልነበረ የሰማይና የምድር ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ጨመርንበት። መጨመሩ ባይከፋም በወዳጅ/ጠላት የብሔር ፖለቲካ ግፊት በራሳችን ወገን ላይ አዘነብነው።

የሚስቱን ምጥ መጥናት ያየ ባል ደመነፍሱን ወደ ጓሮ ዞሮ፣ ‹‹ያለ ዛሬ አልደርስባትም፣ የዛሬን ብቻ ማርያም ድረሽላት›› እያለ ሲምልና ሲገዘት የሰማች ምጥ ላይ የነበረችውና ነገን የተረዳች ሚስቱ፣ ‹‹እባካችሁ አትማል በሉት›› አለች ይባላል። ትናንትን በቅጡ ሳያውቁ፣ ዛሬ ላይ ሆነው ስለ ነገ የሚቃዡ የብሔር ፖለቲከኞች ነገ በፈለገው መንገድ ወስዷቸው ሕልማቸው ከዕውነታው ርቆ እነሱ በቅዥት ዓለም፣ ሕዝቡ በሰቆቃ፣ ከሰውነት ተራ ወርደው በአሳፋሪ ትዝታና ትዝብት ውስጥ ይኖራሉ። 

አገሪቱ የምትከተለው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ቃልን ከተግባር ጋር ያላዛመደ፣ ተገማች ያልሆነ ፖለቲካ ነው።  ቃል በተግባር አልተዛመደም የሚባለው የፖለቲከኛው የትናንት ንግግር ከዛሬው ንግግሩ ጋር ሳይታረቅ ሲቀር ነው። ፖለቲካው ተገማች የማይሆንበት ምክንያት የፖለቲካ ጥያቄዎች በሕዝቡ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ስላልተመሠረቱ፣ ፖለቲካው የሕዝቡ ፍላጎትና ይሁንታ ስለሌለበት፣ ከቀጥታ ተዋናዮቹ በተጨማሪ በእጅ አዙር የሚሳተፉ የአገሪቱ የቅርብና የሩቅ ታሪካዊ ጠላቶች ስለሚሳተፉበት ነው።

አስመራና አዲስ አበባ መንግሥት የሆኑት የፖለቲካ  ቡድኖች በፈጠሩት አስመሳይ ዕርቅ ወቅት ለመገናኘት ከጥብጣብ ወዲያና ወዲህ የተሠለፈው የተነፋፈቀው የሁለቱም ወገን ሕዝብ የድንበሩን መክፈቻ ጥብጣብ መቆረጥ ሳይጠብቅ ሮጦ በመተቃቀፍ መላቀሱ፣ ሕዝቡ ጦርነትና የወንድማማቾች መገዳደል ይቁም በማለት ቀንበር ተሸክሞ በሰላማዊ ሠልፍ እየጠየቀ ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ አስከፊው ጦርነት መቀጠሉ፣ የብሔር ፖለቲከኞችና የሕዝብ ፍላጎት ሆድና ጀርባ ስለመሆናቸው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። 

የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች  ‹‹አህያ በወለደች ታርፋለች›› ያሉ ይመስል እኛ  እንደ አውራ ዶሮ በእርስ በርስ ንክሻ ተናንቀናል።  ከቅኝ ግዛት ታሪክና በአፍሪካ ቀንድ ላይ ፍላጎት ካላቸው የባዕዳን አገሮች ግፊትና ድጋፍ በመነሳት ለፖለቲካ ትክክለኝነትና ለመንግሥት ሥልጣን በመቋመጥ የተንቤን ሰው የኤርትራ፣ የድሬዳዋ ሰው የጂቡቲ ፕሬዚዳንቶች ሆነው ሳለ ለኢትዮጵያ ባዕድ ነን ይላሉ። ሞቃዲሾ ያለው ፖለቲካ ቢለዝብ ፖለቲከኞቹ  ያላሉትን የሕዝብ ለሕዝብ ታሪካዊ ትስስር  የኢትዮጵያና ሶማሊያ ሕዝብ ተባብሮ ይጠብቃል። 

ትግሬ/ኤርትራዊ፣ አማራ/ትግሬ፣  አማራ/ኦሮሞ ስለመሆናቸው በተጣራ አስረጂ የማይደግፉ ፖለቲከኞች በራሳቸው ጊዜ ለዜጎች የብሔረሰብ ማንነት እየሰጡ ሕዝቡን በተለያየ ጎራ አሠልፈው ዘወትር እርስ በርስ በማዋጋት በፖለቲካ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ በሕዝብ ደም እየነገዱ ተንደላቀው ይኖራሉ። ግትር የሥልጣን ጥማትና የብሔረሰብ ፖለቲካ ፉክክር በአቆራኝ ቀለበት አስተሳስሮን  ላንመለስ በሚባል ደረጃ  ገደል ጫፍ ላይ አድርሶናል። ቀይ መስመር ያለፈችም ቢሆን የግብፅ በሶማሊያና ሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ መጠጋት፣ ለአካባቢው የተልዕኮ አጀንዳ ተቀባዮች የሰጠችው የቤት ሥራ መጠናቀቁ ምልክት ነው።

ፌስቡክ ላይ ያነበብኩትን የሚከተለውን የአንድ ሰው አስተያየት ከዚህ ጋር አያይዤ ላንሳው፡፡ ‹‹…የመታገያ  ሐሳብ ብሔር ብቻ በሆነባት አገር ርዕዮተ ዓለም አጥንት በሆነባት አገር አማራ ብለን ካልተደራጀን እንጠፋለን…››፡፡

የሰውየው ሥጋት ተጨባጭነት አለው። ለአገራዊ  ብሔርተኝነት ታምኖ፣ ሁሉንም ወገኑ አድርጎ የኖረው አማራ፣ የፖለቲካ ስትራቴጂስቶቹ እንደዛቱበት ‹‹ማኅበረሰባዊ ዕረፍት›› አጣ። ሲጀመር በየብሔረሰብ በነፃነት መደራጀት መብት ነው ሲባል አማራ ግን በአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት፣ ቀጥሎ በአስመሳይ ኦሮ-አማራ ጥምረት ልጓም ሸብ ተደርጎ ወደኋላ እንዲቀር ስለተደረገ፣ እንደ ሌሎቹ ፈጥኖ በብሔረሰብ ባለመደራጀቱ የራሱን መብት ራሱ ለመወሰን የሚችልበት የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት  አልሆነም።

ወሳኝ በሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮቹ ላይ ሁሉ ስትራቴጂስቶቹ ወሰኑለት። በጣም ዘግይቶ የነቃው አማራ  መጤ ብሔርተኛ  በመሆን ከነባር ብሔርተኞች ጋር በፉክክር ግብግብ ገጠመ። በጠባብ ብሔርተኝነት ጭራሽ የማይገመተው የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ፣ ‹‹ሙያ ከጎረቤት መልክ ከእግዜር››  በማለቱ  የመታጠፊያው መንገድ ራቀ። ትግሉንም ከብሔር ፖለቲካ ትግል በላይ የህልውና ትግል አድርጓል። ‹‹በገዛ አገሩ ላይ የተኛውን በሬ፣ ቀስቅሰው ቀስቅሰው አደረጉት አውሬ›› ብላ ያቺ ሜሪ አርምዴ ያቀነቀነችው ይህ ከርቀት ታይቷት ነበር እንዴ እላለሁ?

እኔ  ግን የምለው የብሔር ፖለቲካ ለአገራችን ስለማይበጅ ከዚህ ኋላቀር የፖለቲካ አረንቋ  እንውጣ ነው፣ ግን ሰሚ የለም፡፡ ‹‹የድመት ዓይን የተገጠመለት ሰው እዚያ ጋ ምን ይታይሃል ቢሉት ዓይጥ አለ›› ይባላል። ያለ ብሔር ፖለቲካ ኑሮ የሚቃና የማይመስለው ዜጋ  በርክቷል። ሁኔታው የብሔረሰብ ፖለቲካ ምን ያህል ሥር እንደሰደደ አመላካች ነው።  የነገድ ብሔርተኝነት ፖለቲካ  ሕዝብን አራቁቶ ለጥቂት ወገኖች ምንዳ ስለሚያከፋፍል ምንደኞች በብርቱ በመሥራት የብሔር ፖለቲካን መሬት አስይዘውታል።

የሁሉም ብሔረሰብ ሕዝብ እኩል፣ በተመሳሳይ ሰዓት  የነገድ ብሔርተኝነት በቃን በማለት በብሔር ፖለቲከኞች ላይ ሊነሳባቸው ይገባል።  ማን ቀድሞ ይተው የሚል ምርጫ ከመጣ አርዓያ ለመሆን ሲባል ቀድሞ መተው ያለበት ቀድሞ  የጀመረ የብሔረሰብ ቡድን ነው። ግን ለመጀመርም ለመተውም ፉክክር ያስፈልጋል ብዬ አላምንም። ሁሉም በአንድ ጊዜ ቢተው ይሻላል። ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የመውጫ መንገድ ይሆናል ተብሎ ሲታሰብ በተያያዘው በጣም ቀርፋፋ ጉዞ የተነሳ የነበረን ተስፋ፣ ‹‹እህል የሚደርስ ለፍስለታ እኔ የምሞት ዛሬ ማታ›› የሚሉት ብሂል ዓይነት ሆነ። ታላላቅ የፖለቲካ ሰዎችን ጨምሮ በኮሚሽኑ ላይ ተስፋ ካሳደሩ ሰዎች መካከል የኮሚሽኑን የሥራ ፍሬ ሳያዩ የሞቱ በርካታ ዜጎች  ናቸው። በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ምን እየተደረገ እንደሆነ ሁሉም ያውቃል።

በሌላ በኩል የብሔር ፖለቲከኞች የብሔር ፖለቲካን እንዲተው ሚና መጫወት ይገባው የነበረ ራሱ መንግሥት  ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያ የመንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲ ተግባር የተደበላለቀባት አሳዛኝ አገር በመሆኗ፣  በየዙሩ በሚዋቀረው መንግሥታዊ ሥርዓት መንግሥት ጎሌ ለሚሆን  የብሔረሰብ ፓርቲ ቡድን የጭን ፈረስ  በመሆን ‹‹የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ›› እንዲሉ፣ በኮቴው ሌላውን ብሔረሰብ እየገረፈ መቀጠል ልማድ ሆኗል። ይህም የዙር ፖለቲካ ችግር አገራችንንና ሕዝቧን አዘቅት ውስጥ አስገብቷል።

አንድ ፌስቡክ ላይ ያነበብኩት አስተያየት፣ ‹‹ከገባንበት አዘቅት ለመውጣት የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት ያስፈልገናል›› ይላል።  ግን በፈጣሪያችን ከመዳኘታችን  በፊት  ከእኛ በኩል የእርስ በርስ መግባባት መኖር ይጠየቃል። እግዜሩ እኔ እንዳይባችሁ እናንተ በቅድሚያ ምን አደረጋችሁ ማለቱ አይቀርም፡፡

የመግባቢያ ነጥባችንም ብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ ሐሳብ  ዙሪያ ላይ ሊሆን ይገባዋል። የብሔር ፖለቲከኞች ለዕኩይ ዓላማ ሲሉ  ያደበላለቁትን/ያዛቡትን  መሠረታዊ ሐሳብ ሁሉ ለማቃናት ከባድ ፕሮጀክት ይጠይቃል። የነገድ ፖለቲከኞች ሆን ብለው ስላድበሰበሱት የመዝገበ ቃላት አገር በቀል ፍቺ  ታላቁ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የሰጡት ትርጉም ቀጥሎ በአጭሩ ቀርቧል። የሚከተለውን ሊንክ በመጫን በቀጥታ  ያንብቡ። https://ethioreference.com/archives/17710፡፡

ብሔር = አገር፣ ምድር፣ ቀየ

ብሔረሰብ = በአንድ አገር የሚኖሩ ሰዎች

ነገድ = አንድ ቋንቋና ባህል ማንነት ተጋሪ ኅብረተሰብ (የሥጋ ተጋሪ መሆን አለመሆንን አይጠይቅም)

ጎሳ = ከነገድ አነስ ያለ ኅብረተሰብ፣ አንድ ነገድ 2፣3፣4፣5፣6፣7 ጎሳ ሊኖረው ይችላል።

ኅብረተሰብ = የሰው ልጆች ኅብረት

ማኅበረሰብ = ከኅብረተሰብ ውስጥ ለየት ባለ አኗኗርና ድርጅት ቁመናው የሚለይ 

ሕዝብ = የሰው ስብስብ ማለት ሲሆን የአንድን አገር ሕዝብ “ሕዝቦች” ብሎ መጥራት የአገሪቱን ሕዝብ የዘመናት አብሮነትና ትስስር ቀስ በቀስ በማላላት ሕዝብን የመለያየት ፍላጎት መግለጫና የብሔር ፖለቲከኞችን ድብቅ ፍላጎት ማሳያ ነው።

ከዚህ በመነሳት የብሔር ፖለቲካ እንጀራ ቆራሹ ፖለቲከኛም ሆነ ሌላው ዜጋ የብሔር ማንነቱን በስትራቴጂስቶቹ ተጋተ እንጂ ብሔራዊ ማንነቱን እጣርቶ አያውቅም ማለት ይቻላል ። ስለዚህ የችግራችን ምንጭ ሁለት ነው።

  1. ብሔሩን የማያውቅ ለምንዳ የሚተጋ ብሔርተኛ ፖለቲከኛና ተከፋይ ተጓዳኝ የማኅበረሰብ አንቂ (Political activist)፣
  2. ብሔሩ ማን እንደሆነ በብሔር ፖለቲከኞች በኩል በቀጥታ የተነገረው ቅን ዜጋ፣

የሁለቱም ችግሮቻችን ምንጮች መነሻ በዕውቀትና በዕውነት ላይ ያልተመሠረተው ግልቦች የሚቆጣጠሩት የብሔር ፖለቲካና የሕዝቡ ማኅበረሰባዊ ንቃተ ህሊና ዝቅተኛ ሆኖ መገኘት ነው።  ገዥ መደቦች ሕዝቡ በማይምነት ጥላ ሥርና በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ እንዲቆይ ያደረጉት ለዚህ ፍላጎታቸው መሟላት እንዲመቻቸው ነው።

ይህ የድንቁርናና የጉልቤ ፖለቲካ ጉዞ እንዲቋረጥ ስንረባረብ ብቻ ነው ያለ ‹‹እግዜር ጣልቃ ገብነት›› ከገባንበት አዘቅት ልንወጣ የምንችልበት መንገድ የሚታየን፡፡  ወደ ዘለቄታ መፍትሔ መቃረብ የምንችለው በጠባብ ብሔርተኝነት መንገድ ሳይሆን የትናንት፣ ዛሬና ነገ ትስስር ፋይዳን ተገንዝበን በሰፊ የውይይት ሁዳድ፣ ምክክርና ግልጽና ርትዕ የፖለቲካ ድርድር  ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ ቀና መንገድ ስንከተል ብቻ ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል adalhusm@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡