ማኅበራዊ
በአማራ ክልል የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የሚቀበሉበትን ጊዜ ማራዘማቸው ተሰማ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: October 9, 2024

በፀጥታ ችግር ምክንያት የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ነባር የቅድመና የድኅረ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎችን የሚቀበሉበትን ጊዜ ማራዘማቸው ታወቀ፡፡

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የአካዴሚ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሰዋለም ሙሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በየመንገዱ የሚታየው የፀጥታ ችግር ምክንያት ተማሪዎችን በተፈለገው ጊዜ መቀበል አልተቻለም፡፡

በደባርቅ አካባቢ ከመስረከም 1 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ የፀጥታ ችግር እንደነበረና በዚህም ምክንያት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን የሚበቀልበት ጊዜ መራዘሙን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የግብዓት አቅርቦት እጥረትና ተያያዥ ችግሮች እንዳሉበት የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በተቻለ መጠን ሰላም እንዲሰፍን ተማሪዎችም ሆኑ ዩኒቨርሲቲው እንደሚፈልጉ አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት በገርበ ጉራቻ አካባቢ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማንነታቸው በማይታወቁ ታጣቂዎች ታግተው እንደነበር አስታውሰው፣ በወቅቱም በማኅረበሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ድንጋጤ መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የጎንደርና የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎችን የተማሪዎች ቅበላ ጊዜ ታሳቢ አድርጎ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን እንደሚቀበል፣ እስካሁንም ከሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው 5,000 የሚሆኑ መደበኛ ተማሪዎች እንዳሉት፣ በ2017 የትምህርት ዘመን ደግሞ 2,500 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል፡፡

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የነባርና የድኅረ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎች የ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የምዝገባ ጊዜ ከመስከረም 28 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ለማከናወን ጥሪ ያደረገ ቢሆንም፣ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ባለማከናወኑ የቅበላ ጊዜውን ማራዘሙን አስታወቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የቅድመ ዝግጀት ሥራዎችን ካጠናቀቀ በኋላ እንደገና ጥሪ እንደሚደርግ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያስታወቀ ሲሆን፣ ስለጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ሪፖርተር ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጥያቄ ቢያቀርብም፣ በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ከተቀመጠው ጽሑፍ ውጪ የተለየ ምላሽ እንደማይሰጡ ገልጸዋል፡፡

የተማሪዎችን ቅበላ በተመለከተ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችን በስልክ ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የወልዲያና የወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊዎች በአካባቢው ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር ባለመኖሩ፣ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተማር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  

በ2017 ዓ.ም. በጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ የቅድመ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎችን ለመቀበል፣ ሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ዝግጅት ማድረጋቸውን ኃላፊዎቹ አክለዋል፡፡