ኤልያስ ተገኝ

October 9, 2024

ሦስት የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች በተያዘው ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተገለጸ፡፡

በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የተገነባውን የመድኃኒት ፋብሪካ ጨምሮ፣ ሌሎች ሁለት የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች በተያዘው ዓመት ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የመድኃኒት አምራቾች ኢንስፔክሽንና ሕግ ማስፈጸም ክፍል መሪ አስፈጻሚ አቶ ጌታቸው ገነቴ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ሦስት አዳዲስ የመድኃኒት ፋብሪካዎች ማምረት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የመድኃኒት ፋብሪካዎቹ በአዲስ አበባ፣ በደብረ ብርሃንና በባህር ዳር መገንባታቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ከእነዚህም ውስጥ የመጀመርያው ፋብሪካ ጂኤምፒ (Good Manufacturing Practice-GMP) የሚባለው የምርት አመራረት ደረጃ ግምገማ ሰርተፊኬት ጭምር የተሰጠውና በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛውና በደብረ ብርሃን ከተማ የተገነባው ፋብሪካ በተያዘው ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ፋብሪካው በአፍ የሚሰጡ መድኃኒቶችን እንደሚያመርት ታውቋል፡፡

ሦስተኛው የመድኃኒት ፋብሪካ በባህር ዳር መገንባቱን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ምናልባት ፋብሪካው በአካባቢው ካለው የፀጥታ ሁኔታ አኳያ ወደ ሥራ የሚገባበት ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያለውን ጨምሮ፣ በደብረ ብርሃንና በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ የመድኃኒት ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ ባለሀብቶች መገንባታቸው ታውቋል፡፡

የመድኃኒት ፋብሪካዎቹን ስምና ተያያዥ መረጃዎችን ከመጥቀስ የተቆጠቡት የኢንስፔክሽንና ሕግ ማስፈጸም ክፍል መሪው፣ ሁለቱ የመድኃኒት ፋብሪካዎች ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ መሆኑን ግን ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2019 ሥራ የጀመረውና በ279 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፋርማሲቲካል ኩባያዎችን ለመሳብ ተብሎ የተገነባ ሲሆን፣ በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በተገነባው ፓርክ የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችን ጨምሮ የህንድና የሌሎች አገሮች ፋብሪካዎች የተለያዩ ዓይነት መድኃኒቶችን እያመረቱበት ይገኛሉ፡፡