
October 9, 2024

የቻይናው ቾንግቺንግ ኩንኋንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ (Chongqing Kunhuang International Industry Group -CKIIG)፣ በስድስት ቢሊዮን ብር (50 ሚሊዮን ዶላር) በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በንዑስ ተቋራጭነት መሬት ለማልማት ተስማማ፡፡
ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የንዑስ ተቋራጭ አልሚነት ስምምነት የተፈራረመው የቻይና ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪ ግሩፕ፣ በገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ከሚገኘው መሬት 20 ሔክታር የሚሆነውን በማልማት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንደሚተገብር ታውቋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዳስታወቀው ስድስት ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ካፒታል ያለው የቻይናው ሲኬአይአይጂ እንዲያለማ የተፈቀደው 20 ሔክታር መሬት፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ይሁንታ ተሰጥቶታል፡፡
የንዑስ ተቋራጭነት አልሚነት ስምምነት የተፈራረመው የቻይናው ኩባንያ የኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረት ኢንቨስትመንት ላይ መዋዕለ ነዋይ ከማፍሰስ ባሻገር፣ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ድርጅቶችን በሥሩ ጋብዞ እንዲያለሙ ማድረግ እንደሚችል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እና የቾንግቺንግ ኩንኋንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ባለድርሻና ተወካይ ቺያዎ ፌንግ ቹ፣ ትናንት ማክሰኞ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም. የንዑስ ተቋራጭ አልሚነት ስምምነት በኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት መፈራረማቸው ተገልጿል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱም ወቅት ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ዘርፈ ብዙ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር፣ በተኪ ምርት (Import Substitution)፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከማሳደግ አኳያ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ምርት ትስስር ረገድ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆን ተብራርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሁለት ሳምንታት አስቀድሞ በኢትዮጵያ በግል ኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚነት ከተሰማሩ አልሚዎች ጋር የውይይት መድረክ አሰናድቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የውይይቱ መድረኩ አንኳር ነጥብ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሚቀየሩበትን ሁኔታ የተመለከተ ነበር፡፡
ሁአጂያን፣ ውዳ፣ ጆርጁ ሹ፣ ኢስት አፍሪካ፣ እንዲሁም ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርኮች በግል ባለሀብቶች ለምተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲሆኑ፣ አልሚዎቹ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ባደረጉት ውይይት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አስመልክቶ የተቀመጠውን የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠበቀውን ተፈላጊ ግብዓት እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ለማስገባት ከስምምነት ደርሰው እንደነበር አይዘነጋም፡፡