
ከ 4 ሰአት በፊት
አሜሪካዊው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በስሩ ባሉ ተቋማት የሚሰሩ 17 ሺህ ሰራተኞችን በመቀነስ የድርጅቱን የሰው ኃይል በአንድ አስረኛ ሊቀንስ መሆኑን አስታወቀ።
33 ሺህ ሰራተኞቹ በስራ ማቆም አድማ ፈትረው የያዙት ቦይንግ የበላይ ኃላፊ ኬሊ ኦርትበርግ “ ቢዝነሳችን በአደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገኛል። እናም በጋራ የምንጋፈጠውን ተግዳሮት መግለጽ ከባድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ኬሊ ኦርትበርግ ለኩባንያው ሰራተኞች በላኩት የኢሜል መልዕክት ላይ በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ ስራዎች ሁሉ አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን ገልጸዋል።
ቦይንግ መሳርያዎች እና ወታደራዊ ቁሳቁሶች በሚያመርትበት ክንፍም ኪሳራ ሊገጥመው እንደሚችል አስጠንቅቆ 777X የተሰኘውን አውሮፕላንን የሚያስረክብበትን ቀን ገፍቶታል።
ይህ ዜና የተሰማው ድርጅቱ ሰራተኞች በስራ ማቆም አድማ እንዲሁም የአውሮፕላኖቹ ጥራት ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት ሰዓት ነው።
ኦርትበርግ በኢሜላቸው ላይ ኩባንያው የሰራተኞቹን ቁጥር “በሚቀጥሉት ወራት” መቀነስ እንደሚጀምር ተናግረዋል።
“የሚቀጥለው ሳምንት አለቆቻችሁ ለድርጀቶቻችሁ ይህ ምን ማለት እንደሆነ የተጠናከረ መረጃ ያደርሷችኋል” ብለዋል።
“ቢዝነሳችን ያለበት ሁኔታ እና ከእርሱ ለማገገም የምናደርገው የወደፊት ጥረት ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ይጠይቃል” ሲሉም አክለዋል።
- ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነታቸው የሻከረው ኤርትራ፣ ግብፅ እና ሶማሊያ ለመተባበር ተስማሙ11 ጥቅምት 2024
- በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በአዲስ አበባ አገረ ስብከት መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ11 ጥቅምት 2024
- በኢትዮጵያ የዘር ፍሬ ልገሳን የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ11 ጥቅምት 2024
የሰራተኛ ኃይሉን ከመቀነስ ባለፈ 777X አውሮፕላኖችን ማስረከብያ ጊዜውን ያራዘመው ኩባንያው “በእድገት ላይ እንዲሁም ከበረራ ሙከራዎች ጋር ተያይዞ የገጠመን ተግዳሮት በተጨማሪም ያለው የስራ መቆራረጥ” ሲል ለረዥም ሳምንታት የቀጠለውን የስራ ማቆም አድማ የፈጠረውን ተጽዕኖ በምክንያትነት ጠቅሷል።
“ለደንበኞቻችን በ2026 የመጀመርያውን አውሮፕላን ለማስረከብ ማቀዳችንን አስታውቀናል” ብሏል።
ለወር ያህል በቀጠለው የቦይንግ ሰራተኞች ስራ ማቆም አድማ በግምት 33ሺህ ያህል ሰራተኞች የክፍያ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ኩባንያው እና የሰራተኞቹ ተወካዮች እያደረጉት የነበረው ድርድር ያለስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ ሰራተኞቹን በመወከል ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ጆን ሆልደን ለሮይተርስ የዜና ወኪል “በዚህ ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየታችን አይቀርም አባላቶቻችን ይህንን ይረዳሉ” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ ባጋጠመ አሰቃቂ አደጋ ምክንያት ከበረራ ታግዶ በነበረው ማክስ 737 ምክንያት ኩባንያው በአሜሪካ ምክር ቤት ጥብቅ ክትትል ስር ነው ያለው።
እኤአ በ2018 እና በ2019 ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ የኢንዶኔዢያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች ከተከሰከሱ በኋላ አውሮፕላኑ በመላው ዓለም ለ20 ወራት ከበረራ ታግዶ ቆይቷል።
በ2020 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎም ከፍተኛ ኪሳራ ያስተናገደው ቦይንግ ለማምረት ተቀብሏቸው የነበሩ በርካታ ትዕዛዞች ተቋርጠውበታል።
በቅርብ ጊዜም እንዲሁ የአላስካ ኤርላየን ንብረት የሆነው 737 ማክስ አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ መስኮቱ መገንጠሉን ተከትሎ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል።