
October 13, 2024

ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በዱቤ ወስደው ከሦስት ወራት በላይ የሚያቆዩ የጤና ተቋማት፣ ከባንክ ሒሳባቸው ተቀናሽ የሚደረግበት አሠራር በአዋጅ ሊፈቀድ ነው፡፡
ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የመድኃኒት ፈንድና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ለማቋቋም በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ለአገልግሎት ከተሰጡ ሥልጣኖች ውስጥ በዱቤ መድኃኒት ወስደው የማይከፍሉ የጤና ተቋማት፣ ከባንክ ሒሳባቸው የመቀነስ ሥልጣን እንዲኖር የሚለው ተካቶበታል፡፡
አገልግሎቱ ከመንግሥት በሙሉም ሆነ በከፊል የሚመደብለት በጀት ስለሌለና ለጤና ተቋማት በዱቤ ለተሰጣቸው መድኃኒት መከፈል ያለበት ክፍያ በወቅቱ መሰብሰብ ካልተቻለ፣ መሠረታዊ መድኃኒቶች ለጤና ተቋማት ባልተቆራረጠ ሁኔታ የማቅረብ ዋና ተልዕኮውን ለመፈጸም እንደሚቸገር ተገልጿል፡፡
የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በዘመቻ መልክ ውዝፍ ዕዳ ካለባቸው የጤና ተቋማት መሰብሰብ ያለበትን ሒሳብ ባደረገው ጥረት የተሰበሰበ ሒሳብ መጠኑ ቢቀንስም፣ አሁንም ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ሒሳብ እንዳለው ተገልጿል፡፡
የተሰብሳቢ ሒሳብ መጠንን ለመቀነስ መውሰድ ያለበት ተጨማሪ ዕርምጃ እንዳለ ሆኖ፣ ከሦስት ወራት ያላነሰ የመክፈያ ጊዜ ተሰጥቷቸው ዕዳቸውን መክፈል ያልቻሉ የጤና ተቋማት የባንክ ሒሳብ ሒሳብ ተቀናሽ የማድረግ አማራጭ፣ ተቋማቱ በቂ በጀት ሳይኖራቸው የግዥ ጥያቄ እንዳያቀርቡ ለመከላከልና ለመድኃኒት የተፈቀደላቸውን በጀት ለሌላ ዓላማ እንዳያውሉ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡
ከአገልግሎቱ መድኃኒት በዱቤ ከቀረበ በኋላ በወቅቱ ዕዳቸውን ካልከፈሉ ተቋማት ጋር ከአላስፈላጊ ምልልስና በመካሰስ ጊዜ በማባከን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረግ ይልቅ፣ ለባንኮችና ለውስን ተቋማት የተሰጠው ሥልጣን ለአገልግሎቱም የተጠቀሰው ሥልጣን ቢሰጠው ችግሩን መቅረፍ ያስችላል ተብሏል፡፡
ረቂቅ አዋጁ አራት ክፍሎች ማለትም ጠቅላላ ድንጋጌዎችን፣ የመድኃኒት ፈንድ ስለማቋቋም፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ስለማቋቋምና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የሚያመለከቱ 28 አንቀጾች አካቶ ይዟል፡፡
የመድኃኒት ፈንድና የኢትዮጵያ አቅራቢ አገልግሎት ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 4/2017 ዓ.ም. ለጤና ማኅበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
ከዚህ ቀደም ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ በሠራው ዘገባ የጤና ተቋማቱ ዕዳቸውን ባለመክፈላቸው፣ በ2016 ለፓርላማው በጀት ዓመት ብቻ 1.9 ቢሊዮን ብርና ያልተከፈለ ዕዳ እንዳለባቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡
ዕዳቸውን ካልከፈሉ የጤና ተቋማት መካከል ጥቁር አንበሳ፣ ዘውዲቱ፣ ጳውሎስ፣ ፈለገ ሕይወትን ጨምሮ 20 ሆስፒታሎችና ሌሎችም የጤና ተቋማት እንዳሉበት መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ዕዳቸውን ያልከፈሉ የጤና ተቋማትን በሕግ መጠየቅ ሌላው መፍትሔ መሆኑን፣ በዘላቂነት የመድኃኒት ክፍያ ዕዳ እንዳይኖር ለማድረግ ውል የተገባለት የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን፣ የጤና ተቋማትም የመድኃኒት በጀታቸውን በቀጥታ ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
