Written by  Administrator

  በወላይታ ዞን የወባ በሽታ ስርጭት ከወትሮው አይሏል


       በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ወላይታ ዞን፣ የወባ በሽታ ስርጭት ከወትሮው በተለየ መጠን መጨመሩ ተገልጿል። የዞኑ ጤና መምሪያ እንደገለጸው፤ በአምስት ወረዳዎች የታካሚዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል፡፡
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ጸጋዬ ኤካ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፣ የወባ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር መጨመሩን ጠቁመው፤ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የወባ በሽታ ስርጭት መስተዋሉን  ተናግረዋል። በማያያዝም፣ ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በአምስት ወረዳዎች በተለይ የታካሚዎች ቁጥር መጨመሩን ጠቁመዋል።
ወረዳዎቹ ቦሎሶ ቦምቤ፣ ቦሎሶ ሶሬ እና ኪንዶ ዲዳዬ ሲሆኑ፣ ከተሞቹ ደግሞ አረካ እና በሌ አዋሳ መሆናቸውን አቶ ጸጋዬ ገልጸው፣ “በአምስቱም ሆነ በሌሎች ወረዳዎች ላይ ነዋሪዎች  በጊዜ ምርመራ አድርገው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው” ብለዋል። ከአጎበር አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በነዋሪው ዘንድ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ቤት ለቤት ቅኝት በማድረግ ግንዛቤ ለመስጠት እየተሞከረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አቶ ጸጋዬ አክለውም፤ “የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎች ተለይተው የማፋሰስና የማዳፈን ስራዎች እየተሰሩ ነው። እነዚህ ስራዎች የሚሰሩት የወባ በሽታ ስርጭት በጠነከረባቸውም ሆኑ ባልጠነከረባቸው አካባቢዎች ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ከአመራሮች ጋር ከፍተኛ ክትትል ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በ327 ቀበሌዎችና 23 ወረዳዎች የወባ በሽታ ስርጭት በየቀኑ ግምገማ እንደሚደረግበት  ገልጸዋል።
ሃላፊው እስከዛሬ ድረስ የወባ በሽታ እንዳይዛመት የመከላከል ስራዎች ሲሰሩ ቢቆዩም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ “ተስተውሏል” ባሉት መዘናጋት ምክንያት ስርጭቱ ሊጨምር እንደቻለ ተናግረዋል። “23ቱም ወረዳዎች ወባማ ናቸው።” ያሉት አቶ ጸጋዬ፣ የአየር ንብረታቸው ለወባ ትንኝ ርቢ አመቺ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“ሰኔ፣ ሐምሌ፣ ነሐሴና መስከረም ላይ እጅግ ዝናብ ባለበትም ወቅት የወባ በሽታ ሲሰራጭ ነበር። ነገር ግን ክረምት ላይ ያልተለመደ ዓይነት የወባ በሽታ መስፋፋቱ ለእኔና ባልደረቦቼ ግርታን ፈጥሯል” ሲሉ አቶ ጸጋዬ ገልጸዋል። በወባ ከተያዙት መካከል ተኝቶ የሚታከም ታማሚ ቁጥር አናሳ መሆኑን ግን ሃላፊው አልደበቁም።
በአጠቃላይ የታማሚዎችን ቁጥር በትክክል ለመግለጽ ባይችሉም፣ የተመላላሽ ታካሚዎች ብዛት ግን ከአምናው በበለጠ ዘንድሮ መጨመሩን አረጋግጠዋል፡፡ በሽታውን ለመቆጣጠር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ጸጋዬ፤የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ ሲናገሩ፣ “ክልሉ ከእኛ ጋር ነው። የክልሉ ከፍተኛ ባለሞያዎችና  ሃላፊዎች ከእኛ ጋር ድጋፍና ክትትል በማድረግ አብረውን እየተሳተፉ ነው።” ብለዋል።