October 15, 2024 

በአማራ ክልል እየተፈፀሙ ባሉ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶች በርካታ ዜጎች እንደተገደሉ እንደሆነ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ በአማራ ክልል የተለያዩ ስፍራዎች እየተፈፀሙ ያሉ የድሮን ጥቃቶች በርካታ ዜጎችን ለሞት እየዳረጉ እንደሆነ የክልሉ ነዋሪዎች ለመሠረት ሚድያ እየተናገሩ ይገኛሉ።

የአይን እማኝ የሆኑ እነዚህ ዜጎች ባደረሱን መረጃ መሰረት በዛሬው እለት ባህር ዳር አቅራቢያ በሚገኘው ሜጫ ወረዳ፣ አማሪት ቀበሌ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶች ተፈፅመው ንፁሀን ዜጎች ጭምር ተገድለዋል።

በሌላ በኩል በዳጋሞት ወረዳ፣ ፈረስ ቤት ከተማ እንዲሁ በደረሰ ጥቃት በርካታ ሰዎች ለሞት እና መቁሰል እንደተዳረጉ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።

ከዚህ በተጨማሪ በዛሬው እለት ከሞጣ ከተማ በ34 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አስተሪዮ ከተማ መንግስት በተመሳሳይ የድሮን ጥቃት መፈፀሙ ታውቋል።

መንግስት በሚፈፅማቸው የድሮን ጥቃቶች ዙርያ ማብራርያ የማይሰጥ ሲሆን ከዚህ በፊት ግን ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የኢትዮጵያ ጦር ድሮን የታጠቀው አለኝ ለማለት ሳይሆን ሊጠቀምበት እንደሆነ መግለፃቸው ይታወሳል።

ይሁንና በአማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት ሰለባ እየሆኑ ያሉ ንፁሀን ዜጎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ እየወጡ ያሉ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

መረጃን ከመሠረት!