
ማኅበራዊ በመሣሪያ ላይ የተመሠረተ አተነፋፈስ ማቋረጥ የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ
ቀን: October 16, 2024
በመሣሪያ ላይ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት ማቋረጥን የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ፣ በጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ተካቶ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡
በመሣሪያ ላይ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ማቋረጥ የሚቻለው የታማሚዎችን የልብና የመተንፈሻ አካላት የአሠራር ሥርዓት መመለስ በማይችልበት ደረጃ ሥራቸውን ሲያቆሙ፣ ወይም የአንጎል ሞት ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 14 ተደንግጓል፡፡ የአንቀጹ ዝርዝር አፈጻጸም የጤና ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ እንደሚወሰን ተመላክቷል፡፡
ከዚህ ቀደም በመሣሪያ የታገዙ ታማሚዎች ሕይወታቸው እንደማይተርፍ እየታወቀ፣ መሣሪያውን ለመንቀል ከሥነ ምግባር አኳያ ለመወሰን ይከብድ እንደነበር የሕክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
በመሣሪያ ላይ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት የሚቋረጥበት ሁኔታ የሕግ ማዕቀፍ እንደሌለው የሚገልጹት የሕክምና ባለሙያዎቹ፣ የተወሰነ የአንጎል ክፍል እየሠራ ነገር ግን መሣሪያው እየተነፈሰላቸው እስከ ሁለትና ሦስት ዓመታት በሕክምና የሚቆዩ ታማሚዎች እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡
በጤና ሥርዓቱ ውስጥ በሕግ የተጠቀሰ አሠራር አለመኖሩን የገለጹት ባለሙያዎቹ የታማሚው ቤተሰብ፣ የሕክምና ባለሙያው፣ የጤና ተቋሙ፣ ጊዜ፣ ሀብትና ሌሎች ነገሮች ይባክኑ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በመሣሪያ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት የሚቋረጥበት ሁኔታ መፍቅድ ተገቢነት እንዳለው አስረድተው፣ ለባለሙያውና ለጤና ተቋማት ትልቅ ዕፎይታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የእንክብካቤ ክፍል (ICU) ውስን እንደሆነ፣ ነገር ግን ይህ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር በርካታ ስለሆነና ባለመመጣጠኑ ሳቢያ መሣሪያ እያጡ የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር ቀላል እንደማይባል አስረድተዋል፡፡
በመሣሪያ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት የሚቋረጥበትን ሁኔታ ውሳኔ ለመስጠት ማረጋገጫ በሚሰጡ ሆስፒታሎች የሥነ ምግባር ኮሚቴ መኖር እንዳለበት የሕክምና ባለሙያዎቹ አሳስበዋል፡፡
ጉዳዩ በባለሙያ ብቻ መወሰን የሌለበት በመሆኑ በየጤና ተቋማቱ ራሱን የቻለ የሥነ ምግባር ኮሚቴ መቋቋም እንደሚገባውም አክለዋል፡፡
በማይድን በሽታ የሚሠቃዩና የሕይወታቸውን ፍፃሜ የሚጠባበቁ ሰዎችን ሥቃይ ለመቀነስ የሚሰጥ የጤና አገልግሎት በረቂቅ አዋጁ የተካተተ ሲሆን፣ በጤና ባለሙያ ወይም ሥልጠና ባገኘ ማንኛውም ግለሰብ (አካላት) ሊሰጥ እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 13 ተደንግጓል፡፡
‹‹ሆስፒስ›› እየተባለ የሚጠራው አገልግሎቱ የሚሰጠው ተገልጋይ የቅርብ ዘመዶቹ ስለታካሚው የበሽታ ክብደት፣ ደረጃና ስለሚያስከትው ውጤት ሊያውቁ እንደሚገባ በረቂቅ አዋጁ ተዘርዝሯል፡፡ በማንኛውም ሁኔታ የተገልጋይን ሕይወት የሚያሳጥር ሕክምና ተግባር መፈጸምን ይከለክላል ይላል፡፡
በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው በክፍል ሦስት በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሥር ከተዘረዘሩት ውስጥ፣ ስለሆስፒስ ወይም በማይድን በሽታ የሕይወታቸው ፍፃሜ የሚጠባበቁ ሰዎች የሚሰጥ አገልግሎትና በመሣሪያ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት ስለሚቋረጥበት ሁኔታ በተመለከተም ይገኝበታል፡፡
ሆስፒስ ማለት በሕይወት መትረፍ የማይችሉ ሰዎች የሚሰጣቸው የሕክምና አገልግሎት መሆኑን፣ ታካሚው ስለሕመሙ እንዲያውቅ የሚደረግበትና ቤተሰብ (አስታማሚ) እንደሚቀበሉት የሥነ ልቦና ድጋፍና ምክር የሚገኙበትን አገልግሎት ያካተተ መሆኑን የሕክምና ባለሙያው አስረድተዋል፡፡
የጤና አገልግሎቶች አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ በአሥራ ሁለት ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን፣ ጠቅላላ ድንጋጌዎች ስለአጠቃላይ የጤና አገልግሎት፣ ስለመብትና ግዴታ፣ ስለጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ስለልዩ የጤና አገልግሎቶችና ሌሎች 60 አንቀጾች ተካተውበታል፡፡
የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 5/2017 ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጤና ማኅበራት ልማትና ባህል ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
