የዓይን ጤና ስትራቴጂ ይፋ ሲሆን

ማኅበራዊ በ27 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበረው የዓይን ጤና ስትራቴጂክ ዕቅድ

ታደሰ ገብረማርያም

ቀን: October 16, 2024

የዕይታ ችግርና ዓይነ ሥውርነት በተንሰራፋባቸው አገሮች የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደየአገሮቹ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ይወሰናል፡፡ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮችና ትኩረት በተነፈጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያሳድረው ጫና ከሁሉም የከፋና አስቸጋሪ ነው፡፡

በ27 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበረው የዓይን ጤና ስትራቴጂክ ዕቅድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ሕይወት ሰለሞን (ዶ/ር)

ካተራክት፣ ትራኮማ፣ ኮርኒያል ብላይንድነስ፣ ግላኮማ እና ዲያቤቲክ ለዕይታ ችግር ዋንኛ መንስዔዎች ናቸው፡፡ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የአኗኗር ዘይቤ አለመሻሻል ለችግሩ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች እጅግ ከፍተኛ የዕይታ ችግርና ዓይነ ሥውርነት ጫና ካለባቸው አገሮች ከቀዳሚዎቹ የምትመደብ ስትሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጫናው ከተንሰራፋባቸው 56 አገሮች ውሰጥ አንዷ ናት፡፡ ሆኖም ከልማት አጋሮችና ከአገር ውስጥ ተዋናዮች ጋር በመሆን የችግሮቹ መንስዔዎች ላይ በመሥራትና በመከላከል ረገድ ስኬት ከተቀዳጁ አገሮችም ትመደባለች፡፡

ስኬቱን ለማስቀጠልም ለሦስት ዓመታት ሥራ ላይ የሚቆይ የዓይን በሽታ መንስዔን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ አድርጋለች፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተከናወነ ዓውደ ጥናት ላይ ይፋ የሆነው ስትራቴጂክ ዕቅድ አምስተኛው ሲሆን፣ ለተግባራዊነቱም 27.3 ሚሊዮን ዶላር ተበጅቷል፡፡

ስትራቴጂክ ዕቅዱ የተለያዩ የማስፈጸሚያ ሥልቶች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የመጀመሪያ ደረጃ የዓይን ጤና አገልግሎትን ሥራ ላይ ከዋለው የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ጋር እንዲቀናጅ ማድረግ፣ ከብት አርቢ ኅብረተሰብ ባሉበትና ለመድረስም አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የዓይን ጤና ቡድን ማቋቋም ይገኙበታል፡፡

የካተራክት ቀዶ ሕክምናን አሁን ካለበት 819 የበጀት ዓመት ወደ 1‚500 ከፍ ማድረግ፣ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ መፍጠር፣ የጤና ባለሙያዎች የመጀመሪያ ደረጃ የዓይን ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለዓይን ጤና ልማት የሰው ሀብት ልማትን ማጠናከርም የእቅዱ አካል ናቸው፡፡

እንደ ጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሕይወት ሰለሞን (ዶ/ር)፣ ዕቅዱ እንዲዘጋጅ የተደረገው ከዓለም ጤና ድርጅት በመካከለኛ ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉት አገሮች የተቀናጀ የዓይን ጤና ፕሮግራም ሥልት ወይም ስትራቴጂ ነድፈው እንዲተገብሩ የሚያስችል አቅጣጫ በመሰጠቱ ነው፡፡

በተያያዘም፣ የዓለም የዕይታ ቀን ‹‹ትኩረት ለልጆች ዓይን ጤና›› በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ፕሮግራሞች መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ታስቦ ውሏል፡፡ ከፕሮግራሞቹ መካከል በቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተሰጠው የሕፃናት የዓይን ቀዶ ሕክምና ይገኝበታል፡፡ በመድኃኔዓለምና በጄኔራል ታደሰ ብሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተከናወነው የተማሪዎች የዓይን ምርመራም የፕሮግራሙ አካል ነበር፡፡

የዓይን ጤና እክል አካላዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሚያስከትል የጠቆሙት  ሕይወት (ዶ/ር)፣ በርካታ ሕፃናት መከላከል በሚቻሉ የዓይን ጤና ችግሮች ምክንያት ዕይታቸውን እንደሚያጡ በመግለጽ፣ ወላጆችና አሳዳጊዎች በተለይም እየተለመደ የመጣውን የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች አጠቃቀም በተመለከተ ሊያስቡበት እንደሚገባ አሳስበዋል።