
October 16, 2024 – EthiopianReporter.com
‹‹ካዛንቺስ ጉዳይ ነበረኝ…››
በአንባቢ
October 16, 2024
አይባባ አይባባ ሆዴ
አይባባ አይባባ ሆዴ
ባምቢስን ማን ባሻገረኝ
ካዛንቺስ ጉዳይ ነበረኝ›
ልጅ ሆኜ ጋሽ አራጋው የሚባል የእነ እማዬ ጎረቤት ሞቅ ሲለው በረንዳ ላይ ተቀምጦ ይህንን ዘፈን ሲያንጎራጉር እሰማው ነበር። ድምፁ ደስ ይለኛል። ጋሽ አራጋው ሞቅ ካለው በቃ ‹አይባባ ሆዴ› ተዘፈነ ማለት ነው። ከአፉ አይጠፋም ዘፈኑ። ቆይቼ ቆይቼ ትልቅ ስሆን አንድ ቀን ዘፈኑን በራዲዮ ሰማሁት። ጋሽ ማህሙድ ጀምሮት ከዚያም መስፍን አበበ በክራሩ ውብ አድርጎና (ካዛንቺስን ጨምሮ) ተጫውተውታል። ፀጋዬ መርጊያም ዘፍኖታል። ኦሪጅናሉ ዜማ የማን እንደሆነ ግን አላውቅም። (ዩቲዩብ ላይ አለላችሁ ሁሉም)…
ብቻ አሁንም ያ ዜማ በአጋጣሚ ትዝ ሲለኝ አዜመዋለሁ። ጋሽ አራጋው፣ በረንዳውና ድምፁ ናቸው ትዝ የሚሉኝ። በኢንስትሩመንትም ይስሐቅ ባንጃው ይሁን መሰለኝ ጥሩ አድርጎ ሠርቶታል።
ካዛንቺስ የሠፈሬ ጎረቤት ናት። ከኦሎምፒያ እስከ ባምቢስ ድልድይ ግዛቴ ነበር። ባምቢስን ተሻግሬ ዮርዳኖስ ሆቴልን ስረግጥ ደግሞ ካዛንቺስ ገባሁ ማለት ነው።
“ካዛ” ከልጅነቴ ጀምሮ የማውቃት ሠፈር ናት። አክስቴ ቋሚ ሠፈር በሚባለው አካባቢ (አሁን ኢንተርኮንቲኔንታል የተሠራበት) ትኖር ነበር። ባር ኖንቼን የሚያውቅ ካለ ከዚያ ጀርባ ማለት ነው። ደግሞም በአባቴ የሚዛመደን ጋሽ ብንቆይ የተባለ ሰውም እዚያው ቋሚ ሠፈር መግቢያ ላይ ከሰጎን ቡና ቤት ዝቅ ብሎ የሚገኘውን ብንቆይ ግሮሰሪ ይዞ ለብዙ ዘመናት ኖሯል። ልጅ ሳለሁ እማዬ በሳምንት ቢያንስ ሦስት ቀናት እህቷን ለመጠየቅ ይዛኝ ስለምትሄድ ከዚያ ሠፈር አልጠፋም። ሁለተኛ ሠፈሬ ናት ካዛ!
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ትንሳዔ ብርሃን ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። ለስምንት ዓመታት ካዛንቺስን በየቀኑ ስመላለስባት ኖሬያለሁ። መርካቶ የምትኖር አክስቴ ጋ ለመሄድ 39 ቁጥር አውቶቡስን የምሳፈረው ካዛንቺስ ሄጄ ነው። ሲኒማ ኢትዮጵያ ለመግባት 9 ቁጥር አውቶቡስ የምንሳፈረው እዚያው ካዛንቺስ ሄደን ነው። እናቴ አስቤዛ የምትገዛውም ከዚያው አካባቢ ሱቆች በአንዱ ነው።
ዘመዶች ስለነበሩኝ ብቻ ሳይሆን ሠፈሩ ለኦሎምፒያ ሰዎች መሻገሪያም መናኸሪያም ስለነበር ካዛንቺስን ሳንረግጥ የምናጠፋው ቀን አልነበረም ማለት ይቻላል። ኖራ ኖራ ካዛንቺስ ቀስ በቀስ መፍረስ ጀመረች። ቀዳሚው ፈረሳ የተካሄደው ለእነኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልና አያት ሪል ስቴት፣ እንዲሁም ለእነንግሥት ታወርና ለእነኢሊሌ ሆቴል ግንባታ ተብሎ የተካሄደው ፈረሳ ነው።
ያ ፕሮጀክት ኢሕአዴግ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ተግኖ አዲስ አበባን ለማዘመን የጀመረው ግንባታ አካል እንደነበር አስታውሳለሁ። አካባቢው የጭቁን ሠፈር ስለነበር መንግሥት ሁሉንም የካዛ ነዋሪዎች ጠራርጎ ሲኤምሲና ገርጂ ጊዮርጊስ ለመውሰድ ብዙም አልተቸገረም። ካዛንቺስ የመጀመሪያ ስደቷን ስታደርግ በመንግሥት ቤት ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎቿ ገርጂ ጊዮርጊስ ተጠቃልለው ገቡና አዲስ ‹ካዛንቺስ ሠፈር› የሚባል አካባቢ መሠረቱ። የሚገርመው ነገር በ15 ሺሕ ብር ክፍያ ብቻ ነው ለሁሉም እንደ ቤታቸው ስፋት ደርግ የሠራው ባለ ግቢ ቤት የታደላቸው። ደግ ዘመን!
ካዛንቺስ የጆሊዎችና የጭስ አራዳዎች መናኸሪያ እንደነበረች ተድባበ ጥላሁን በ‹‹ማህልየ ማህልይ ዘ ካዛንቺስ› መጽሐፉ ብጥር አድርጎ አሳይቶናል። እነ ስሪ ዶርስ፣ እነኦሜድላ ሆቴል እነ አሰብ ሆቴል…፣ የቀድሞ የሸገር አራዶች ብዙ ብዙ ያዩባቸው ሥፍራዎች ነበሩ።
ካዛንቺስ ስሟን የወረሰችው ከዛሬው ራዲሰን ብሉ ሆቴል ፊት ለፊት ካለው ሰፊ ቤተ መንግሥት የመሰለ (ቀድሞ ሰርቢያ ኤምባሲ ከነበረውውብ ግቢ ላይ ተውሳ ነው። “ካዛ” ማለት ደግሞ በጣሊያንኛ ቤት ማለት ነው። ካዛ ኢንቺዝ (ካዛንቺስ) ማለት ደግሞ “የኢንቺዝ ቤት” እንደማለት ነው።
ካዛንቺስ ከአዲስ አበባ ቀደምትና ደማቅ ሠፈሮች አንዷ ነበረች። ቆይቶ ቆይቶ ካዛንቺስ በድጋሚ መፍረስ ጀመረች። ከዮርዳኖስ ሆቴል እስከ ሃናን ዳቦ ቤት ድረስ ያለው ሠፈር ለግዙፍ ፎቆች ይፈለጋል ተብሎ ፈረሰ። (እስከ ዛሬ ምንም ነገር ባይሠራበትም)። ያኔ አዲስ ጉዳይ መጽሔትን ስንሠራ ቢሯችን እዚያው ንግሥት ታወር ላይ ስለነበር ፈረሳውን ቆመን አየን። እኔ ‹‹የካዛንቺስ የመጨረሻ ቀናት›› የሚል ሰፊ አርቲክል ጽፌ ለንባብ አብቅቼ እንደነበር አስታውሳለሁ። ካዛንቺስን መዘከሬ ነበር እንደአቅሚቲ። ሆኖም ካዛንቺስ በከፊል ተርፋ ስለነበር ወዘናዋ ሳይጠፋ ዛሬ ድረስ ቆይታለች። ከመናኸሪያ እስከ ዑራኤል መቃረቢያ ድረስ የተዘረጋው አስፋልት ብዙ ነዋሪዎችን እንደያዘ ኖሯል።
የካዛንቺስ የመጨረሻ ቀናት ግን ያኔ ሳይሆን አሁን ነው። ይህ ሁሉ ሠፈር ተጠራርጎ እየፈረሰ ነው። በካዛንቺስ ለታሪክ የሚቀሩ ሠፈሮች አይኖሩም። አጎራባቾቿ አቧሬና መናኸሪያን ጨምሮ። ነገር ግን ካዛ ትዝታዋን ብቻ በልባችን ትታ ሄዳለች።
ያች የቤተ መንግሥት አዋሳኝ፣ የአራዶቹ ሠፈር፣ ባለብዙ ታሪኳ ካዛ ነገ ስሟ ብቻ እንጂ ዳናዋ አይገኝም። ‹‹ካዛ ብላንካ›› ይሏት ነበር ልጆቿ ሲያቆላምጧት። ‹‹ነጩ ቤት›› እንደማለት ነው በስፓኒሽና ጣሊያኖች ዘንዳ። የእኛዋ ካዛ ነጭ ነጠላዋን እንዳጣፋች ከዓይን ጠፍታለች!
አይባባ አይባባ ሆዴ
ባምቢስን ማን ባሻገረኝ
ካዛንቺስ ጉዳይ ነበረኝ…
– መላኩ ብርሃኑ በማኅበራዊ ገጹ እንደከተበው