ማኅበራዊ የእንስሳት ጤና ቦርድ እንዲቋቋም የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

ሔለን ተስፋዬ

ቀን: October 16, 2024

የእንስሳት ጤና ቦርድ እንዲቋቋም የሚወስን የእንስሳት ጤናና ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ተካቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችን ለመመዝገብ፣ ሙያዊ ፈቃድ ለመስጠት፣ አገልግሎቱን ለማሻሻል የሚያስችላቸው ወቅቱ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲይዙና የተደራጀ ቁጥጥር የሚያደርግ፣ የሥነ ምግባር ጥሰቶች ሲፈጸሙ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን የሚወስድ ገለልተኛ አካል በአገር ደረጃ መደራጀት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው እንደሚታመንበት በረቂቅ አዋጁ ተዘርዝሯል፡፡

ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሕክምናና ጤና ጋር ተያይዞ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነትን መሠረት በማድረግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡና አጠቃላይ መዋቅሩ የዕድገት ፖሊሲ ተከትሎ ተገቢውን ቁጥጥር ተደርጎበት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚረዳ ቦርድ መቋቋም እንደሚኖርበት ለፓርላማው የቀረበው የእንስሳት ጤናና ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት መሥራች አባል መሆኗን የገለጸው ረቂቁ፣ ከላይ የተጠቀሰውን ግዴታ የሚወጣ ገለልተኛ የእንስሳት ጤና ቦርድ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ያስረዳል፡፡

የዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት በ2003 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ላይ ባካሄደው ግምገማ፣ ዝቅተኛ የጤና አገልግሎት የምትሰጥ መሆኗን በረቂቁ አዋጁ ተመላክቷል፡፡

ለዚህ ዝቅተኛ ውጤት ገለልተኛ የሆነ የእንስሳት ጤና ቦርድ አለመኖር አንዱ ክፍተት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በቀጣይ ይህንን ተቆጣጣሪ አካል በአፋጣኝ አደራጅቶ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ማድረግ አንገብጋቢ መሆኑን፣ ቦርዱ ሳይቋቋም በመቅረቱ የእንስሳት ልማት ዘርፍ በተለያዩ ችግሮች ተተብትቦ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ለመወጣትና ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር የእንስሳት ጤና ቦርድ ማቋቋም እጅግ ወሳኝ የሆነበት ወቅት እንደሆነ በረቂቁ ተዘርዝሯል፡፡

በእንስሳት ሕክምና የሠለጠኑ ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ተላብሰው የእንስሳት፣ የኅብረተሰቡንና የአካባቢን ጤና በማረጋገጥ ረገድ የተጣለባቸውን ግዴታ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡

ለዚህም ባለሙያዎች እንዲመዘገቡ፣ ሙያዊ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱና ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚችሉ ሥልጠና ወስደው ጥራቱን የጠበቀ የእንስሳት ጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል፣ በፌዴራል ደረጃ ተደራጅቶ ሒደቶቹን በገለልተኝነት የሚቆጣጠር አካል ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ የቦርዱ መቋቋም ወሳኝ እንደሆነ በረቂቁ ተጠቁሟል፡፡

በዘርፉ በሚሰጠው ትምህርትና ሥልጠና የሚታዩ የጥራት ችግሮችን በማስተካከል፣ የአገሪቱን የእንስሳት ሀብት በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም እንዲቻል ቦርዱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት፣ ቦርዱ በእንስሳት ሀብት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ረቂቅ አዋጁ አሥር ክፍሎችና 46 አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ ስለእንስሳት ጤና ባለሙያ ምዝገባና አገልግሎት አሰጣጥ፣ አገር አቀፍ የእንስሳት በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር፣ የእንስሳትና የእንስሳት ውጤቶች ደኅንነትና ጥራትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ተካተውበታል፡፡

የእንስሳት ጤናና ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 3/2017 ሆኖ ለፓርላማው የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡