

ዜና ኢትዮ ቴሌኮም 30 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን ለሽያጭ አቀረበ
ቀን: October 16, 2024
ኢትዮ ቴሌኮም አስር በመቶ ድርሻውን ለሕዝብ ለመሸጥ በያዘው ዕቅድ መሠረት 3ዐ ቢሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን በዛሬ ዕለት ለሽያጭ አቀረበ።
ኩባንያው 10 በመቶ ድርሻውን ዛሬ ከቀትር በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በተገኙበት ይፋ ያደረገ ሲሆን ፣ በዚህም 30 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ መቶ ሚሊዮን አክሲዮኖችን ለሽያጭ እንዳቀረበ አስታውቋል።
ለሽያጭ ያቀረቡት አክሲዮኖች እያንዳንዳቸው 300 ብር የሚያወጡ ሲሆን አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛው መጠን 33 ወይም 9,990 ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን ነው። አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ከፍተኛ መጠን ደግሞ 3,333 ወይም 999,900 ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን እንደሆነ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በእያንዳንዱ አክሲዮን ላይ ታክስና አስፈላጊ የአገልግሎት ክፍያ ጨምሮ እንደሚያስከፍልም ታውቋል።
የአክሲዮኖን ሽያጩ በቴሌ ብር አማካኝነት የሚከናወን ሲሆን ፣ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚቆይ ይሆናል።