October 16, 2024

ርዕሰ አንቀጽ

ሰሞኑን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በፌዴራልና በክልሎች ሲከበር አፅንኦት የተሰጠው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የመስዋዕትነት፣ የነፃነት፣ የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ዓርማ መሆኑ ነበር፡፡ ቀደምቶቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ወደር የሌለው የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈል በክብር ያስተላለፏት አገር፣ በዚህ ዘመን ትውልድ ተጠብቃ ለመጪው ትውልድ የምትተላለፈው ህልውናዋ አስተማማኝ እንዲሆን ጥርጊያው ሲመቻች ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከሰንደቅ ዓላማው ጀምሮ በበርካታ ብሔራዊ ጉዳዮች ስምምነት የለም፡፡ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች በነፃነት ተጋድሎዋ አማካይነት ሰንደቅ ዓላማዋን ጭምር ዓርማቸው ያደረገች ኢትዮጵያ፣ የዚህ ዘመን ልጆቿ የጋራ የሚሉት መግባቢያ ጠፍቶ በየቦታው ቅራኔና ግጭት ነው የበረከተው፡፡ ከሩቅም ከቅርብም የኢትዮጵያን ህልውና ሊፈታተኑና ሕዝቡንም ሰላም ሊነሱ የሚችሉ ኃይሎች ሲጠራሩ፣ በውስጥ ጤና ማጣት ምክንያት የተፈጠረው ሥጋት ያሳስባል፡፡ የሕዝብ ሰላምና የአገር ህልውና አደጋ ሲጋረጥበት ደንገጥ ማለት ይገባል፡፡   

በአንድ ወቅት ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል የነበረች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሥር የዓለም ሰላም አስከባሪ በመሆን ለረጅም ጊዜ የምትታወቅ፣ አፍሪካውያን በቅኝ አገዛዝ ሲማቅቁ ድምፃቸው ከመሆን አልፋ ለነፃነታቸው ትልቅ አበርክቶ የነበራት፣ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ሥልጣኔ አሻራዋን ያሳረፈችና በበርካታ መልካም እሴቶቿ የምትታወቅ አገር በምን ምክንያት ነው በእርስ በርስ ግጭት የምትታመሰው? ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት አፈታት ሥልቶችና የሽምግልና ሥርዓቶች ሰላም ማስፈን የሚችል ብልህ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ ምን ዓይነት ችግር ቢገጥማት ነው የንፁኃንን ደም ከመፍሰስ መታደግ ያቃተው? በደስታም ሆነ በመከራ ጊዜ ለአገሩ በአንድነት መቆምን ህያው ታሪክ ያደረገ አርቆ አስተዋይ ሕዝብ ባለባት ኢትዮጵያ፣ በጭካኔ እርስ በርስ እየተፋጁ ለታሪካዊ ጠላቶች ቀዳዳ መክፈት ምን የሚሉት ሥልጣኔ ነው?

አገር ሰላም ስትሆን የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ይሆናል፡፡ አገር ሰላም ስታጣ ደግሞ የሕዝብ ሕይወት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ አንድ ሥፍራ ሰላም ሲጠፋ ሁሉም ቦታ ይታወካል፡፡ በአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዜጎችን በእጅጉ የሚያሳስባቸው የሰላም መጥፋት ነው፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ተንቀሳቅሶ መሥራትና መኖር የከበዳቸው በሚሊዮኖች ይቆጠራሉ፡፡ ከዋናዋ ከተማ አዲስ አበባ በአምስቱም በሮች ወጣ ብሎ ጉዳይን በነፃነት አከናውኖ በሰላም መመለስ አዳጋች ከሆነ ቆየ፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ በሰላም ተጉዞ መድረስ ለብዙዎች የሚታሰብ አይደለም፡፡ በየመንገዱ ያደፈጡ ታጣቂዎች ዜጎችን አግተው ሚሊዮን ብሮች የባንክ ሒሳባቸው ውስጥ ካልገቡላቸው አይለቁም፡፡ የጠየቁት የማስለቀቂያ ገንዘብ ዘገየ ብለው ብዙዎችን ገድለዋል፡፡ የታገቱባቸውን ወገኖች ለማስለቀቅ እርጥባን የሚለምኑ ወገኖች በየቦታው ሞልተዋል፡፡ በዚህ ላይ የውጭ ኃይሎች ለጥቃት ሲያሰፈስፉ አደጋው ግልጽ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ ላይ ማተኮር እየበዛ ለመግለጽ የሚያዳግቱ ጥፋቶች በዝተዋል፡፡ ጥፋቶቹ የንፁኃንን ሕይወት የሚያስገብሩ፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የሚያፈናቅሉና የደሃ አገር ሀብት የሚያወድሙ ግጭቶችን እያመረቱ ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጡ ነው፡፡ ብዙዎቹ በፖለቲካም ሆነ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ልሂቃን፣ ለአገር ዘለቄታዊ ሰላም የሚያስገኙ ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ዳተኝነት እያሳዩ መሆናቸው ችግሮቹን እያከበዳቸው ነው፡፡ ዳር ከሚይዙት በተጨማሪ ለሰላም መስፈን ጥረት ከማድረግ ይልቅ ነዳጅና ክብሪት ይዘው የሚዞሩ መብዛታቸው ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጣና ጂኦ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴው እየሾረ ከመሆኑም በላይ፣ ግብፅና ግብረ አበሮቿ ከበባ መጀመራቸውም አይረሳ፡፡

አሁን ዋነኛ ጥያቄ መሆን ያለበት ኢትዮጵያ ከገባችበት አደገኛ አረንቋ ውስጥ ወጥታ ሕዝቧ ዕፎይ እንዲል ምን መደረግ አለበት የሚለው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህልውና ሲባል ቀና ቀናውን ብቻ ማሰብ የትም አያደርስም፡፡ በየቀኑ በተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ መለስተኛ ግጭቶች፣ ጦርነቶችና ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች የንፁኃን ደም እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን አደገኛ ሒደት ማስቆም ካልተቻለ የኢትዮጵያ ትንሳዔ ሳይሆን መፍረስ ነው የሚታወጀው፡፡ ይህንን ዘግናኝና ሲሰሙት የሚያስደነግጥ እውነታ ከልብ ተቀብሎ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ብሔራዊ የጋራ አጀንዳ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በአገር በቀል የግጭት አፈታትና የሽምግልና ባህሎች የታደለች ስለሆነች፣ ለአገር እናስባለን የምትሉ በሙሉ ግጭት ከማጋጋልና የዳር ተመልካች ከመሆን ተላቃችሁ የሚፈለግባችሁን ኃላፊነት ተወጡ፡፡ አገር አንዴ ካመለጠች እንደማትገኝ ተገንዘቡ፡፡ በቅርብ ርቀት የፈረሱ አገሮች ታሪክ የሚናገረው ይህንን እውነታ ነው፡፡

በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ የፖለቲካ አሠላለፍ የተለያዩ ጎራዎች መኖራቸው ተገቢ ነው፡፡ ይህ አሠላለፍ ግን አንዱ የሌላውን ህልውና እየካደ እንዳይጓዝ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እየተዳከመ በየቦታው አመፅ የሚስፋፋው፣ ካለፉ አስከፊ ድርጊቶች ለመማር ፈቃደኝነት በመጥፋቱ ምክንያት እንደሆነ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በነፃነትና በእኩልነት የሚፎካከሩበት እንዲሆን ለሁሉም ሐሳቦች ዕድል መሰጠት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ምድር አንድ ጥይት ሳይተኮስ ሕዝብ መብቱና ነፃነቱ ተከብሮ የሚኖርበት ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ የሴራ ፖለቲካ ከሥሩ ተመንግሎ መውደቅ ይኖርበታል፡፡ ሴረኝነት ለአገር አይጠቅምም፡፡ የእርስ በርስ ጥላቻና ፍጅት የሚጠቅመው ለታሪካዊ ጠላቶች ብቻ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ የኃይል ስብስብ እየተፈጠረ ነው፡፡ ስለዚህ ከሕዝብና ከአገር በፊት ቀዳሚ ነገር እንደሌለ ይታመን!