Belay Manaye 

የኮሪደር ልማት፤ ማህበራዊ ኢፍትሃዊነትን የሚያጸና ድሃ ጠል ፖሊሲ ነው፣

ሚሊዮኖችን አግልሎ ጥቂት ባለሃብቶችን የአገርና የከተማ ባለቤት የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ እንደሆነ ደጋግሜ ጽፌያለሁ፡፡ ዛሬ የተፈናቃዮችን ለቅሶ ደጋግሜ ስሰማ መንግስት በኮሪደር ልማት ስም ሚሊዮኖችን እያፈናቀለና ከልማት እያገለለና ግፍን እያጸ በሄደ ቁጥር በተከለው የመንገድ መብራት ልክ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ የሰው ቦንብ እያጠመደ መሆኑን ለማሳሰብ ወደድኩ፡፡

+++++

በኮሪደር ልማት ስም እየተካሄደ ያለው አዲስ አበቤን የማፈናቀልና የማተራመስ ሥራ ሦስት መሰረታዊ አደጋዎች አሉበት፡፡

1ኛ/ ማህበራዊ ኢፍትሃዊነት (social injustice) እያሰረጽ ስለሚሄድ ከተማዋን ከሚሊዮኖች ነጥቆ ለጥቂት ከበርቴዎች የሚሰጥ እጅግ አግላይ ባለሃብት ተኮር የልማት ፖሊሲ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የከተማዋን ልማት እንደራሱ ሃብትና ንብረት የማይቆጥር ትውልድና ህዝብን ይፈጥራል፡፡ ከተማዋን ያቀኑ፣ ያለሙ፣ እና ዛሬ ያላትን ተፈላጊነት እንዲኖራት ለብዙ አመታት ሃብታቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ካፈሰሱባት ነዋሪዎቿ ነጥቆ ወፍ ዘራሽ (የውጪ ባለሃብትን ጨምሮ) ለሆኑ ባለሃብቶች የሚሰጥ አግላይና ኢፍትሃዊ የሆነ የልማት ፖሊሲ ሁሌም ለከተማዋ አደጋ ነው፡፡ ከተማዋን ማልማት አንድ ነገር ሆኖ የካሳንቺስ፣ የፒያሳ፣ የአራት ኪሎ፣ የለገሃር፣ የጨርቆስ፣ ወዘተ … ነዋሪዎችን አስፈንጥሮ ከከተማዋ ጠርዝ ላይ መጣል እና መንደራቸውን ብር ላላቸው ጥቂት ከበርቴዎች መስጠት አይን ያወጣ ንጥቂያ ብቻ ሳይሆን የለየለት ኢፍትሃዊነትም ነው፡፡ ጠንካራ የሲቪክ ማህበራት ቢኖሩ ኖሮ እና ገለልተኛ የፍትህ ተቋማት ቢኖሩ መንግስትን ከሶ ይህን ህገ ወጥነት እልባት ማስያዝ ይቻል ነበር፡፡

2ኛ/ ሁለተኛው የዚህ ልማት ችግር ደግሞ እጅግ ድሃ ጠል የሆነ እና የኢትዮጵያን ጉስቁልና፣ መከራና ስቃይ የአዲስ አበባን አውራ መንገዶች በማልማትና በሚንቆጠቆጡ የምሽት መብራቶች ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች መኖራቸው ነው፡፡ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ለተንሰራፋው የከፋ ድህነት፣ ለዜጎች ጉስቁልና፣ በግጭት ምክንያት ትምህርት ቤቶቻቸው ወድመውባቸው መማር ስላቆሙት ሚሊዮን ህጻናት እና በየመጠለያው ላሉ ተፈናቃይ ድሆች ግድ የማይሰጠው መሆኑን ማሳያም ነው፡፡ ሚሊዮኖችን አስርቦ፣ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ፣ ሚሊዮኖችን ከትምህርት ገበታ አርቆ፣ ሚሊዮኖችን የኑሮ ዋስትና አሳጥቶ፣ ሚሊዮኖችን የሥራ እድል ነፍጎ፣ ሚሊዮኖችን ሰላም በሌለበት አስቸጋር ሁኔታ ውስጥ ከቶ በብዙ ቢሊዮኖች በሚገመት ገንዘብ ቤተመንግስትና መንገድ የሚያለማ፣ ያገጠጠና ያፈጠጠውን የአገሪቱን ድህነት በገጽታ ግንባታ በጀት ለመሸፈን የሚደረግ ርብርብ ድሃ ጠል ከሆነ ፖሊሲ የሚመነጭ ነው፡፡ ድህነትን መጥላትና ድሃን መጥላት ይለያያል፡፡

3ኛ/ ሌላው የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ትልቁ ችግር ዘመናት ያስቆጠረውን የከተማዋን ነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ማህበራዊ መዋቅር የሚያፋልስ መሆኑ ነው፡፡ እንደማንኛውም የአንድ አካባቢ ሕዝብ የአዲስ አበባም ነዋሪ የራሱ የሆነ social-psychological ወይም የጋራ የሆነ ማህበራዊ ሥን ልቦናዊ ውቅር አለው፡፡ ይህን የጋራ የሆነ የጋራ ሥነ ልቦና ደግሞ አዋቅረው ያቆዩለት እድር፣ እቁብ፣ ሰንበቴ፣ ጽዋ፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የጎደኞች፣ የአብሮ አደጎች ማህበራት አሉት፡፡ የአዲስ አበባ የጉርብትና ትስስር ብሄር፣ ሃይማኖት ወይም ሌላ መለያ የለውም፡፡ ልክ እንደ አኑዋር መስጊድና ራጉኤል ቤተክርስቲያን የጸሎት ትስስር የአዲስ አበቤም ሥነ ልቦናው እንዲሁ በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ህይወቱ እጅግ የተሳሰረ ነው፡፡ ይህን ህዝብ ሆን ብሎ ወደ ከተማዋ የተለያዩ ጥጎች መበታተን እነዚህን ተቋማትም አብሮ መበታተን (Dismantling social fabric) ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ለአዲስ አበቤ ሁሉ ነገሩ ናቸው፡፡ እድር ገበና ነው፡፡ እድር የህይወት ኢንሹራንስ ነው፣ እድር መከራ መወጫ ነው፡፡ እቁብ እንደ ባንክ ነው፡፡ ሌሎቹም ማህበራዊ ተቋማት እንዲሁ ለአዲስ አበቤ ለዘመናት የተጫነውን መከራና ድህነት የሚቋቋምበትና የሚመክትበት ነው፡፡ የካሳንቺስ ሰው ሲበተን አካባቢው ላይ ያሉ ተቋማት ሁሉ አብረው ይበተናሉ፡፡

Yared Hailemariam