
By Admin

አንድነት ሰመረ
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) “ የፌደራል መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በዚህ ሕገ መንግሥት ተወስኗል። ለፌደራል መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት ። ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌደራል መንግሥት መከበር አለበት ። ” ተብሎ ተደንግጎ የክልል ሥልጣንና ተግባርም በአንቀጽ 52 ተወስኗል። በተለይ በአንቀጽ 52(2)(ሀ) ላይ፣ እያንዳንዱ ክልል “ ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራል፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል፣ ይህን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፣ ይከላከላል።” ይላል። ነገር ግን፣ የቤኒሻንጉልና የኦሮሞ ክልሎች ሕገ መንግሥቶች የፌደራሉን ሕገ መንግሥት አያከብሩም። ስለሆነም፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(2) በአንዳንድ ክልሎች አልተከበረም።
በተጨማሪ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በተከታታይ የሚሾመው በፌደራል መንግሥት ነው። የዛሬው አቶ አረጋ ከበደ የተሾሙት በግድ እንደሆነ ደጋግመው ተናግረዋል። ይህ አሠራር በሌሎችም ክልሎች ያለ ነው። እንዲሁም በአንቀጽ 46(1) እና በአንቀጽ 50(1) “ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌደራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ ነው።” ተብሎ ተደንግጓል።
ስለሆነም፣ በአንቀጽ 47(1) መሠረት፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ የሪፐብሊኩ አካል አይደሉም ማለት ነው። ይህም በአንቀጽ 47(1) “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት …” 9 ክልሎች ናቸው፣ ማለትም (1) ትግራይ ክልል፣ (2) አፋር ክልል፣ (3) አማራ ክልል፣ (4)ኦሮሚያ ክልል፣ (5) ሱማሌ ክልል፣ (6) በኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል፣ (7) የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ (8) የጋምቤላ ክልል፣ (9) የሐረሪ ክልል ተብለው ተዘርዝረዋል። ታዲያ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ከሌሉ የት ናቸው ? ይህ አንቀጽ 47(1) ያልጨመራቸው ሌሎችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አያሌ ወገኖቻችን አሉ።
በኢትዮጵያ 83 ጎሣዎች የራሳቸው ቋንቋና ባህል ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አሉ ስለሚባል፣ ከዘጠኙ ክልሎች ውስጥ፣ በአንቀጽ 5(3) መሠረት፣ የአምስቱ ክልሎች የሥራ ቋንቋ የራሳቸው ጎሣ ቋንቋ ሲሆን፣ የቀሩት የአራቱ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው። ስለዚህ፣ በጠቅላላ ሪፐብሊኩ ውስጥ የክልል የሥራ ቋንቋዎች 6 ስለሆኑ፣ የራሳቸው ቋንቋ የሥራ ቋንቋ ያልሆነላቸው 77 (83 – 6 = 77) ጎሣዎች የሚጠቀሙት በሌሎች ስድስት ጎሣዎች ቋን vቋዎች ነው። የራሳቸው ክልልም ስለሌላቸው ላሉበት ክልል ተገዢ ከመሆናቸው ጋር በአንቀጽ 47(1) መሠረት የሪፐብሊኩ አባላትም አይደሉም። በዚያ ላይ፣ በአንቀጽ 8(1) መሠረት “ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው። “ ያለው ድንጋጌም እነዚያን ክልል-የለሽና ለዘጠኙ ክልሎች ተገዢ የሆኑትን 77 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አይመለከትም። አብዛኞቹ ጎሣዎቻችን፣ ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ጋር፣ ከሪፐብሊኩ ውጭ ስለሆኑ ህዝባችንን ያላካተተ የአገዛዝ ሥርዓት ፌደራል ነው ማለት አይቻልም። 6 ጎሣዎች የ 77ቱ የበላይ የተደረጉት፣ አንድም ሕዝቡ ተሰባጥሮ በመኖሩ መከፋፈል ስላልተቻለ፣ ሁለተኛም ገዢዎች የፈለጉትን አገር ለራሳቸው ከልለው ግዛት ካሰፉ በኋላ ለቀረው ግድ ስላልነበራቸው፣ ሶስተኛም 83 ክልል መፍጠርም ስላልተቻለ ነው። ሌላው የፌደራል ሥርዓት እንደሌለን ለፌደራልና ለክልል መንግሥታት በጣምራ ደርበው የሚሠሩ ሹሞች ያሉበትን የፌደሬሽን ምክር ቤት ማየት ነው።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 61(1) መሠረት፣ “ የፌደሬሽን ምክር ቤት በፌደራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚልኳቸው አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው።” ስለሆነም፣ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች (See House of Federation FACEBOOK) እና የክልል ሹሞች ስላሉበት፣ በተለይም የክልልና የሕገ መንግሥት ፈጣሪዎችም ስለሚመሩት፣ በፓርላማ ሆነ በሌላ ፌደራል አካል ተደማጭ ኃይል ነው። በአንቀጽ 47(1) መሠረት፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ የፌደራል መንግሥት አባል ክልሎች ባለመሆናቸው በምክር ቤቱ ውስጥ አይወከሉም። በተጨማሪ ተወካቶች የክልል ምልምሎች እንጂ በሕዝብ ያልተመረጡ በመሆናቸው፣ በአንቀጽ 8(3) መሠረት የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችም አይደሉም።
ይህ የክልሎች ምልምል የሆነው የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ በአንቀጽ 62(9) መሠረት፣ “ ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል።” ይላል። ይህ ድንጋጌ በአንቀጽ 50(8) የተደነገገውን የፌደራል የሥልጣን ክፍፍል ጥሶ፣ የክልል ምልምል ስብስብ ማከላዊ መንግሥትን በማዘዙ፣ ከፌደራል ሥርዓት ተጻራሪ ነው። እንዲሁም በአንቀጽ 55(16) የፓርላም ሥልጣንና ተግባር ድንጋጌ መሠረት፣ “ በማንኛውም ክልል ስብአዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይችል ሲቀር፣ በራሱ አነሳሽነትና ያለ ክልሉ ፈቃድ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ለፌደሬሽን ምክር ቤትና ለተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፤ በተደረሰበት ውሳኔ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት መመሪያ ይሰጣል።” በማለት ይህ የክልል ምልምሎች ስብስብ የሆነው የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕዝብ ከመረጠው ከፍተኛው የፌደራል ባለሥልጣን በአንቀጽ 50(3) እንደተደነገገው፣ ፓርላማ እኩል ወስኖ ለክልሉ የጎንዮሽ መመሪያ መስጠቱም የፌደራል ሥርዓት አሠራር አይደለም።
ይህ የክልሎች ምልምሎች ስብስብ የሆነው አካል በአንቀጽ 48 ላይ በክልሎች የወሰን ክርክር ላይ ዳኝነት ሲቀመጥ ክልል በክልል ላይ መፍረዱም ከፌደራል ሥርዓት ውጭ በመሆኑ፣ በአንቀጽ 62(1)፣ 84(1) እና 84(2) ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን መሰጠቱ፣ በአንቀጽ 62(8) ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡትን የፍትሐብሔር ጉዳዮች የመለየት ሥልጣን መያዙ፣
በአንቀጽ 62(5) ከፓርላማ ጋር የተሰጠ ጣምራ ሥልጣን ስላለው ይህ የክልሎች ኃያል ምልምል ስብስብ የሆነው የፌደሬሽን ምክር ቤት የማዕከላዊ መንግሥቱን ሕግ አስፈጻሚ፣ ሕግ አውጪና ሕግ ተርጓሚ ይመራል፣ ያዝዛል ወይም በጣምራ ይሠራል። ስለሆነም፣ ይህ ክልሎችንና ሕገ መንግሥቱን የቀረጹትን የጨመረ የክልል ምልምሎች ስብስብ ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ተስተካካይ ወይም የሚልቅ ሥልጣን አለው። የአገሪቱ የወቅቱ ችግሮች ማዕከሉም እሱው ነው። ስለሆነም፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 በሹሞች ሳይሆን በራሱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ስለተጣሰ የፌደራል ሥርዓት የለንም።
ይህ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁትና ያጸደቁት ሕወሀትና ኦነግ ሲጀመር ጀምሮ፣ መጀመሪያ ሕወሀቶች ሲመሩት፣ አሁን ደግሞ ኦሕዴዶች፣ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያደርጉበትና ሲያስፈልግም አሻንጉሊት ሰብሳቢ ሰይመው የሚመሩት አካል በመሆኑ፣ የፈጠሯቸውን የአገዛዝና የሥልጣን መሣሪያ የሆኑትን ክልሎችና ሕገ መንግሥቱን እንዳሉ ለማቆየት ወይም የአገዛዙን ዓላማ ለማስፈጸም መንግሥትአከራካሪ ተግባራትን ለመተግበር የፌደራሉን ሕግ አስፈጻሚ ዘርፍ፣ ሕግ ተርጓውን ዘርፍና ሕግ አውጪውን ዘርፍ ትቶ በእጅ አዙር የሚፈልገውን የሚከውንበት ፀረ-ፌደራልና ፀረ-ዲሞክራሲ አካል ነው።
ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት፣ በአሜሪካ፣ ምንም ዓይነት የአሜሪካ ክፍለ ሀገራት ምልምሎች ስብስብ ለ STATE OF CALIFORNIA ወይም ለ STATE OF TEXAS ፓርላማ መመሪያ መላክ አይችልም። በወሰን ክርክር ላይም ዳኝነት አይቀመጥም፣ ለ CONGRESS ሆነ ለ WHITE HOUSE ትዕዛዝ መላክ አይችልም። የ SUPREME COURT ውሳኔንም አይቀለብስም። “ፌደራልነቱ” እንደ እኛው ሆኖ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አሜሪካ ቢሆን ኖሮ፣ ሁሉንም በድፍረት ያደርግ ነበር። ስለሆነም፣ የእኛ ሥርዓተ መንግሥት ለዘውድ-የለሽ ኋላ ቀር የፊውዳል ሥርዓት ይበልጥ ይቀርባል።
ለማጠቃለል፣ አለ የሚባለው የኢትዮጵያ ETHNIC FEDERALISM፣ ሲጀመር ጀምሮ የክልሉ ሕገ መንግሥት ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት የተለየበት፣ (See Benishangul Region Constitution, Article 2, for example) ፣ የክልል ሹም ስብስብ (See House of Federation FACEBOOK) ለክልል መመሪያ የሚሰጥበት፣ የክልል ሹም ክልልንና የፌደራል መንግሥትን በጣምራ ደርቦ የሚያገለግልበት(ለምሣሌ፣ አቶ ሽመልስ አብዲሣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳርና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ናቸው።) ፣ የክልል ባለሥልጣን ስብስብ የማዕከላዊ መንግሥትን አካላት የሚያዝበት፣ እንደ ማዕከላዊ መንግሥት አካልም የሚሠራበትና ከሕዝባችንም ብዙው፣ በአንቀጽ 47 መሠረት፣ የሪፐብሊኩ አካል ያልሆነበት አገዛዝ ነው። ስለሆነም የፌደራል ሥርዓት የሌለን በዋናነት ሕገ መንግሥቱ ሲጀመር ጀምሮ በዚያ መልክ ፌደራል ለማስመሰል ስለተቀረጸ እንጂ ሹሞች ስለጣሱት ብቻ አይደለም። እንደ ኔልሰን ማንዴላ ያለ መሪ አግኝተን፣ በአንድ ፍትሐዊ ምርጫ በሀቀኛ ፌደራልና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢተካ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለው የአገዛዝ ሥርዓት ስረገጥ፣ ስራብና ስገደል መኖር ይሻለኛል ይላል የሚሉ ካሉ፣ ሥርዓቱ የፈጠራቸው ቢሊዮኔሮችና የሥርዓቱ ፈጣሪዎች ናቸው።
__
