ኩመር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መጠለያ
የምስሉ መግለጫ,ኩመር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መጠለያ

17 ጥቅምት 2024, 17:16 EAT

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ባሉ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ያሉ ሱዳናውያን ስደተኞች ከአንድ ዓመት ለበለጠ ጊዜ በታጣቂዎች ግድያዎች፣ ድብደባዎች፣ እገታዎች እና ዝርፊያዎች እንደተፈጸመባቸው እንዲሁም በግዳጅ የጉልበት ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ሂውማን ራይትስ ዋች አስታወቀ።

በአገራቸው ያለውን ጦርነት ሸሽተው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጣቢያዎች ተጠልለው ያሉ ስደተኞች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች፣ በአካባቢው ሚሊሻዎች እንዲሁም በቅርቡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንደደረሱባቸው ተቋሙ ሐሙስ፣ ጥቅምት 7/ 2017 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

ስደተኞቹ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወደ አገራቸው በግዳጅ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ስደተኞቹን ዋቢ አድርጎ ሂውማን ራይትስ ዋች አስፍሯል።

“በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ከአንድ ዓመት በላይ በታጠቁ አካላት ለጥቃት ዒላማ ተደርገው ቆይተዋል” ሲሉ የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር መግለጻቸው በሪፖርቱ ተካቷል።

አክለውም “እነዚህ ስደተኞች በአገራቸው አስከፊ ጥቃቶችን ሸሽተው የመጡ እንደመሆናቸው ህይወታቸውን ለተጨማሪ አደጋዎች ማጋረጥ ሳይሆን በአስቸኳይ ጥበቃ እና ከለላ ሊደረግላቸው ይገባል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን ስደተኞችን ከለላ እና ጥበቃ ለመስጠት በቂ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት፣ በግዳጅ መመለስን መከልከል እና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ ማረጋገጥ እንደሚገባው ተቋሙ አሳስቧል።

“በሱዳን ስደተኞች ላይ ጥቃቶች፣ ዘረፋዎች እና ግድያዎች በሚሊሻዎች እና መደበኛ ባልሆኑ ታጣቂዎች ደርሶባቸዋል የሚለውን” የሂውማን ራይትስ ዋች ግኝቶች “መሠሰረተ ቢስ እንዲሁም ስህተት ነው” ሲል የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ምላሽ ሰጥቷል።

ተቋሙ አክሎም “የኢትዮጵያ መንግሥት በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በጭራሽ አይታገስም እንዲሁም በመንግሥትም ሆነ በማንኛውም አካል በአስገዳጅ ሁኔታ ስደተኞችን ማዛወር የተፈጸመበት ሁኔታ የለም” ብሏል።

ሂውማን ራይትስ ዋች በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙት ኩመር፣ አውላላ እንዲሁም አዲስ የተቋቋመው አፍጥጥ የተሰኙት የተመድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እንዲሁም የመሸጋጋሪያ ማዕከል ያሉ ሃያ ሱዳናውያን ስደተኞችን፣ የሱዳን ተሟጋቾችን እንዲሁም የረድዔት ሰራተኞችን አነጋግሯል።

በተጨማሪም ከመጠለያ ጣቢያዎች፣ ከመሸጋገሪያ ማዕከሉ ከሳተላይት የተገኙ እንዲሁም በኦንላይን የተጋሩ ምሥሎች እና ቪዲዮዎችን መርምሮ ሪፖርቱን ማጠናቀሩን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ከሰኔ/ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች እና የአካባቢው ሚሊሻዎች በአውላላ እና ኩመር መጠለያ ጣቢያዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት በማድረስ ቢያንስ ሦስት ግድያዎችን እንዲሁም ከባድ ጥቃቶችን ተፈጽመዋል ብሏል።

ከተገደሉትም ውስጥ አንዷ የሁለት ልጆች እናት እና የሦስት ወር ነፍሰጡር የነበረችው አዲላ የተባለች የ31 ዓመቷ ስደተኛ እንደነበረች ተገልጿል።

ስደተኛዋ ለህክምና ሄዳ ስትመለስ በነበረችበት መኪና ውስጥ ባልታወቁ ታጣቂዎች በጥይት መመታቷን ሪፖርቱ አካቷል። ከግድያዎች በተጨማሪ ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች፣ ድብደባ፣ በትጥቅ የታገዘ ዝርፊያ እና በግዳጅ የጉልበት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ መደረጋቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በእርሻ ሥራ ላይ በግዳጅ እንዲሰማሩ መደረግን ጨምሮ በባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ 347 የሚሆኑ አስገዳጅ የጉልበት ሥራን የሚገልጹ ክስተቶች ከስደተኛው ማኅበረሰብ ማግኘቱን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ያናገራቸው ሱዳናውያን ስደተኞች በታጣቂዎች ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች ተደጋጋሚ መሆናቸውን ገልጸው።

በደረሱባቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት ከመጠለያ ጣቢያዎች ለቀው ጎዳና ላይ የወጡት እነዚህ ሱዳናውያን ስደተኞች እርዳታ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው በመማጸን ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች እና የመከላከያ ሠራዊት እያደረጉት ባለው ግጭት የስደተኞቹ ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

የፌደራል መንግሥት እነዚህን የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ያቋቋመበት ስፍራ አሁን ካለው ግጭት በፊትም በአካባቢው ማኅበረሰቦች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች የማያጣው እንዲሁም የወንጀል ድርጊት የሚፈጸምበት ቢሆንም የዘረጋው ፀጥታ የተወሰነ ነው ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች ገልጿል።

ከጥቂት ወራት በፊት ስደተኞቹ በታጣቂዎች የሚፈጸሙባቸውን ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች በመቃወም አንድ ሺህ የሚሆኑት መጠለያ ጣቢያዎቹን ለቀው ጎንደር ወደሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን እያቀኑ ነበር።

ሆኖም ፖሊስ ስደተኞቹን እንዳይሄዱ በመከልከሉ መንገድ ዳር ባሉ ጫካዎች ለመጠለል መገደዳቸው ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የተባበሩት መንግሥታት ከስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ጋር በመሆን ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን ከአውላላ እና እና ኩመር ጣቢያዎች አዲስ ወደተቋቋመው አፍጥጥ ተዘዋውረዋል።

ሆኖም በአውላላ ጫካ ተጠልለው የነበሩ በርካታ ስደተኞች ተጨማሪ ጥቃቶች ይደርሱብናል በሚል ስጋት ወደ አፍጥጥ ለመዛወር ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር። ነገር ግን ታጣቂዎች በየቀኑ በሚያደርሱባቸው ጥቃቶች ጫካውን ለቀው ጉዟቸውን በሱዳን ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው መተማ ማድረጋቸው በተቋሙ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል።

ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት መጀመሪያ ላይ በመንገድ ዳር ጊዜያዊ መጠለያ እንዲያዘጋጁ ፈቅደውላቸው የነበረ ቢሆንም፤ በኋላ ግን ስደተኞቹ ወደ መተማ የስደተኞች መሸጋገሪያ ማዕከል እንዲሄዱ ማዘዛቸውን ጠቁሟል ። ስደተኞቹ አንሄድም በሚሉበት ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ጊዜያዊ መጠለያዎቹን እንዳፈራረሱት እንዲሁም ስደተኞቹን መደብደባቸው ተገልጿል።

ከእነዚህ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ሱዳን ተመልሰዋል። ዩኤንኤችሲአር ስደተኞቹ በፈቃዳቸው መመለሳቸውን ቢገልጽም ስደተኞቹ በበኩላቸው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአስገዳጅ ሁኔታ እንደመለሷቸው እና በዚህም የተነጣጠሉ የቤተሰብ አባላት እንዳሉ ሂውማን ራይትስ ዋች ነግረውኛል ብሏል።

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ የተመለሱ ስደተኞች የሉም ብሏል።

“እዚያ ያለው ሁኔታ ወደ አገራቸው መመለስን ስለማይፈቅድ ስደተኞችን ወደ ሱዳን ለመመለስ ምንም ምክንያት የለም ሲል” ተቋሙ ምላሽ መስጠቱ ሪፖርቱ ያሳያል።

ሁሉም ወታደራዊ ኃይሎች እና ታጣቂ ቡድኖች በስደተኞች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ፣ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ እንዳይገቡ እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ በአስተማማኝ መልኩ እንዲደርስ ማመቻቸት እንዳለባቸው ሂውማን ራይትስ ዋች ምክረ ኃሳብ ለግሷል።

በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙት አውላላ እና ኩመር የተሰኙት የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ከሱዳን፣ ከኤርትራ እና ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ስደተኞችን ይቀበላሉ።

በሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በጦሩ መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄኔራል መሃመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ1.6 ሚሊዮን ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም መካከል ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው ገብተዋል።

ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአገሪቱ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያንን ከቤት ንበረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።

በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያን ሕይወታቸውን ከጦርነቱ ለማትረፍ ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ