ሲንዋር

17 ጥቅምት 2024, 17:48 EAT

እስራኤል ለረጅም ጊዜ ስታድነው የቆየችው የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር በጋዛ መገደሉን ማረጋገጧን አስታወቀች።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ሐሙስ፣ ጥቅምት 7/ 2017 ዓ.ም በጋዛ መገደሉን ያስታወቁ ሲሆን ሐማስ ስለ መሪው ግድያ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በበኩሉ ከዓመት ክትትል በኋላ ሲንዋር ወታደሮቹ በጋዛ ደቡባዊ ክፍል ባደረጉት ዘመቻ ትናንት ጥቅምት 6/ 2017 ዓ.ም ተገድሏል ብሏል።

በመከላከያው እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መካከል ያለው የመረጃ መጣረስ ምክንያቱ አልተገለጸም።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በመግለጫው ሲንዋር የመስከረሙን ጥቃት ያቀነባበረ እና በበላይነት ያስፈጸመ እንደሆነ ገልጾ “ለበርካታ እስራኤላውያን ግድያ እና አፈና ተጠያቂ ነው” ብሏል።

“ያህያ ሲንዋር በጋዛ ሲቪል ህዝብ ጀርባ ከመሬት በላይ እና ከመሬት በታች ባሉ የሃማስ ዋሻዎች ውስጥ ላለፈው አንድ አመት ተደብቆ ከቆየ በኋላ ተወግዷል” ብሏል በመግለጫው

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ውስጥ “የሃማስ ከፍተኛ አባላት ተጠርጥረው የሚገኙበትን ቦታ የሚጠቁሙ” መረጃዎችን ተከትሎ በደቡባዊ ጋዛ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል” ሲልም አክሏል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የ 828ኛ ብርጌድ የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች “ሶስት አሸባሪዎችን ለይተው አስወግደዋል” ያለው መግለጫው ከተገደሉት አንዱ ሲንዋር መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል።

ሚኒስትሩ በበኩላቸው የሐማሱ መሪ ያህያ ሲንዋር ግድያን “ይህ ለእስራኤል ታላቅ የወታደራዊ እና የሞራል ስኬት እንዲሁም ነጻው ዓለም በኢራን በሚመራው ክፋት የተሞላው ጽንፈኝነት ድልን የተቀዳጀበት ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አክለውም “የሲንዋር መወገድ ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እድል ይከፍታል እንዲሁም በጋዛ ውስጥ ያለ ሃማስ እና ያለ ኢራን ቁጥጥር አዲስ እውነታን የሚያመጣ ለውጥ መንገድ ይከፍታል “ ብለዋል።

የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ በሦስት ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ “የሞቱት ሦስት አሸባሪዎች” ማንነት ገና አልተረጋገጠም ብሎ ነበር።

የእስራኤል ደኅንነት ባለሥልጣን የተገደለው ታጣቂ የሐማስ መሪ መሆኑን ለማረጋገጥ የዲኤንኤ (ዘረመል) ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቦ ነበር።

ሦስቱ ታጣቂዎች በተገደሉበት ሕንፃ ውስጥ የእስራኤል ታጋቾች መገኘታቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች እንዳልታዩም ነው የተገለጸው።

የእስራኤል ሠራዊት ሬድዮ በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ በራፋህ ከተማ በተካሄደው የምድር ላይ ጥቃት የእስራኤል ወታደሮች ሦስት ታጣቂዎችን ገድለው አስከሬናቸውን መውሰዳቸውን ሪፖርት አድርጓል።

ምሥላዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከታጣቂዎቹ መካከል አንዱ ያህያ ሲንዋር ሊሆን እንደሚችል እና ማንነቱን ለማረጋገጥ የዘረመል (ዲኤንኤ) ምርመራዎች እየተደረጉ ነው ሲል ዘግቦ ነበር።

እስራኤል ያህያ ሲንዋርን ከአውሮፓውያኑ 1988 እስከ 2011 አስራው በነበረበት ወቅት የወሰደቻቸው የዲኤንኤ ናሙናዎች አሏት።

የ62 ዓመቱ ሲንዋር በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው ኻን ዩኒስ የስደተኞች ካምፕ ነው የተወለደው።

አብዛኛው ህይወቱን በእስራኤል እስር ቤት ያሳለፈው ሲንዋር በአውሮፓውያኑ 1988 ለሶስተኛ ጊዜ ሲታሰር አራት የዕድሜ ልክ አስራት ተፈርዶበት ነበር።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2011 በጋዛ በሐማስ ተይዞ በነበረው እስራኤላዊ ወታደር ልውውጥ ከ1 ሺህ26 ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን አረብ እስረኞች መካከል አንዱ የነበረው ሲንዋር ከእስር ተፈትቷል።

ያህያ ሲንዋር ከጥቂት ወራት በፊት ቴህራን በሚገኘው መኖሪያ ቤት የተገደሉትን የሐማሱን መሪ ኢስማኤል ሃኒያን ተክቶ ነበር የመሪነት ቦታውን የያዘው።

አቡ ኢብራሂም በሚል በስፋት የሚታወቀው ያህያ ሲንዋር፣ ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ካቀነባበሩ አንዱ ነው።

ሲንዋር ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ የቡድኑ መሪ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፣ ከሃኒያ ግድያ በኋላ የቡድኑ ፖለቲካዊ ክንፍ ኃላፊም ሆኖ እየሠራ ነበር።