ያህያ ሲንዋር
የምስሉ መግለጫ,ያህያ ሲንዋር

23 ህዳር 2023

ተሻሽሏል 17 ጥቅምት 2024

ያህያ ሲንዋር አጠቃላይ የሐማስ መሪ ተደርጎ የተሾመው የቡድኑ የፖለቲካ ክንፍ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ቴህራን ውስጥ በእስራኤል ነው በተባለ ጥቃት ከተገደለ በኋለ በኋላ ነበር።

ሲንዋር ከዚህ ሹመት በፊት የሐማስ ወታደራዊ መሪ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ይሁን እንጂ የሐማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒያ ግድያን ተከትሎ የቡድኑ አጠቃላይ መሪ ሆኖ ተሹሟል።

ይህ ግለሰብ የሐማስ መሪ ተደርጎ ይሾም እንጂ የት እንዳለ ሳይታወቅ ወራት አልፈዋል። ለነገሩ በሺዎች የሚቆጠሩት የእስራኤል ወታደሮች በሰላዮች እና ድሮኖች ታግዘው ያለበትን ለማወቅ በሚያነፈንፉበት ወቅት አድራሻውን ማጥፋቱ የግድ ነበር።

በነጭ ፀጉሩ እና ችምችም ባለው ጥቁር እና ነጭ ቅንድቡ የሚለየው ሲነዋር፣ በእስራኤል ቁጥር አንድ ተፈላጊ ሰው ነበር።

እስራኤል ለመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃት ቁጥር አንድ ተጠያቂው ሲንዋር ነው ትላለች።

ሐማስ በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ከ1200 በላይ እስራኤላውያንን ገድሎ ከ200 በላይ ሰዎችን አግቶ ወስዷል።

ከዚህ ጥቃት ማግስት የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች ቃል አቀባይ “ያህያ ሲንዋር የዘመቻው ጠንሳሽ እና መሪ ነው . . . ሞት የማይቀርለት ሰው ነው” ሲሉ አውጀው ነበር።

የዚያን ዕለቱ ጥቃት የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካን ከመቀየሩም በላይ እስራኤል ከአረቡ ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት አቅጣጫ ያስቀየረ ነው ማለት ይቻላል።

“ይህ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጠው ያህያ ሲንዋር ነው። ስለዚህ እርሱ እና በስሩ ያሉ አባላቱ ሞታቸው እርግጥ የሆኑ ቆመው የሚሄዱ ሰዎች ናቸው” ያሉት ደግሞ የእስራኤል የመከላከያ ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሔርዚ ሃሌቭ ነበሩ።

እስራኤል የሐማስ መሪ ተደርጎ የተሾመው ሲንዋር፣ በጋዛ እንዳለም የእስራኤል ጽኑ እምነት ነው።

የእስራኤል ደኅንነት መረጃዎችን እንደሚያመለክቱት ሲንዋር በጋዛ ልክ እንደ የሸረሪት ድር በተዘረጉት ከመሬት በታቸ ባሉ ዋሻዎች በአንዱ ከግል ጠባቂዎቹ ጋር ተደብቆ፤ የስልክ መስመሩ ሊጠለፍ ይችላል በሚል ስጋት ከተቀረው ዓለም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳያደርግ ተደብቆ እንደቆየ ይታመናል።

ያህያ ሲንዋር

የሲንዋር እድገት

አሁን ላይ የ61 ዓመት አዛውንት የሆነው ሲንዋር ብዙዎች የሚያውቁት አቡ ኢብራሂም በሚለው መጠሪያው ነው።

ሲንዋር የተወለደው በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጠ ነው። በደቡባዊ የጋዛ ሰርጥ በሚገኘው የኻን ዩኒሲ መጠለያ ጣቢያ።

ምንም እንኳ የቤተሰቦቹ ቀዳሚ የመኖሪያ ሰፍራ አሁን የእስራኤል ከተማ በሆነችው አሸኬሎን የነበረ ቢሆንም፣ ፍልስጤማውያን አል-ናቅባ ብለው በሚጠሩት የመፈናቀል አና የስደት ዘመን ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ ከተገደዱ በኋላ ነው ሲንዋር በመጠለያ ጣቢያ የተወለደው።

ትምህርቱን በጋዛ የተከታተለው ሲንዋር፤ ኢስላሚክ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ጋዛ ከተባለው ተቋም በአረብኛ ቋንቋ በዲግሪ ተመርቋል።

ሲንዋርን እስር ላይ ባለ ወቅት ከአንድም አራት ጊዜ ቃለ መጠይቅ ያደረጉለት የዋሽንግተን ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ኢሁድ ያሪ፤ ሲንዋር ገና ለጋ የ19 ዓመት ወጣት ሳለ በእስራኤል በቁጥጥር ስር መዋሉን ይገልጻሉ።

በሲንዋር የወጣትነት ዘመን ኻን ዩኒስ የሙስሊም ወንድማማቾች ንቅናቄ ትልቁ የድጋፍ ማዕከል ነበረ።

ሲንዋር “እስላማዊ እንቅስቃሴ” ማድረግ በሚል በ19 ዓመቱ እአአ በ1982 ላይ በቁጥጥር ስር ዋለ። ከሦስት ዓመታት በኋላ ዳግም ታሰረ።

ታዲያ ሲንዋር በተደጋጋሚ በእስራኤል መታሰሩ የሐማስ መሥራች የሆኑት የሼክ አሕመድ ያሲን አመኔታን ለማግኘት አስችሎታል።

“ሁለቱ ሰዎች በጣም በጣም ተቀራረቡ” የሚሉት በቴል አቪቭ የሚገኘው የብሔራዊ ደኅንነት ጥናቶች ኢንስቲቱት ከፍተኛ አጥኚ የሆኑት ኮሚ ማይክል ናቸው።

ሲንዋር ለሼክ አሕመድ ያሲን መቅረቡ እና ታማኝነት ማግኘቱ ልቡ ለሐማስ እንዲሸፍት አደረገው።

እአአ 1987 ላይ ሐማስ ከተቋቋመ ከሁለት ዓመታት በኋላ በቡድኑ ውስጥ በእጅጉ የሚፈራውን አል-ማጂድ የተባለውን የደኅንነት ሕዋስ አቋቋመ። ሲንዋር ይህን ሲያደርግ ታዲያ ገና ዕድሜው 25 ነበር።

አል-ማጂድ በጋዛ የሥነ-ምግባር ጥሰት ፈጽመዋል የሚላቸውን መቅጣት እና ልቅ የወሲብ ፊልም የሚይዙ ሱቆችን ዒላማ ማድረግን ተያያዘ። ከእስራኤል ጋር ተባባሪ ናቸው ያላቸውን አድኖ መግደል ጀመረ።

ያሪ ከእስራኤል ጋር ተባብረዋል የተባሉ ሰዎች በአስቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ ተጠያቂው ሲንዋር ነው ይላሉ። “አንዳንዶቹን በገዛ እጁ ነው የገደላቸው በዚህም ኩራት እንደሚሰማው ነግሮኛል” ይላሉ።

እንደ የእስራኤል ባለሥልጣናት ከሆነ ሲንዋር በአንድ ወቅት ለእስራኤል መረጃ ሲያቀብል ነበረ የተባለን ሰው በገዛ ወንድሙ በሕይወት እንዳለ እንዲቀበር ማድረጉን አምኗል።

“በጣም አድርገው የሚፈሩትን ተከታዮች እና ደጋፊዎችን ማፍራት የሚችል ሰው ነው” ሲሉ ያሪ ሲንዋርን ይገልጹታል።

እአአ 1988 ላይ ሲንዋር ሁለት እስራኤላውያን ወታደሮችን አግቶ አሰቃይቶ በመግደል ተከሶ በተመሳሳይ ዓመት በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ከዚያም 12 ፍልስጤማውያንን በመግደል በእስራኤል ጥፋተኛ ተብሎ 4 የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

ሲንዋር

የእስር ዓመታት

ሲንዋር አብዛኛውን የጉልምስና ዕድሜውን ያሳለፈው በእስር ቤት ነው። ከ1988 እስከ 2011 ድረስ 22 ዓመታትን በእስራኤል እስር ቤት ማቅቋል።

ከእነዚህ ረዥም ዓመታት የተወሰኑትን ያሳለፈው ለብቻው በጠባብ ክፍል ውስጥ ታስሮ ነው። ታዲያ ሲንዋር ለብቻ በጠባብ ክፍል ውስጥ ታስሮ መቆየቱ በእስራኤል ላይ የበለጠ ጥላቻ እንዲያዳብር እንዳደረገው ይታመናል።

እስራኤል ሲንዋርን በእስር ቤት ሳለ በሚከተሉት ቃላት ባህሪውን ገልጻው ነበር፡

“ጨካኝ፣ አቅም ያለው ተጽእኖ ፈጣሪ፣ ልዩ የሆነ አካላዊ ጥንካሬ ያለው፣ ተንኮለኛ እና በሕይወቱ የሚረካ… በእስር ቤት ውስጥም ሆኖ ከሌሎች እስረኞች ጋር ምሥጢር በመጠበቅ… ብዙ ሰዎችን የመምራት ችሎታ ያለው።”

ሲንዋር በእስር ቤት ሳለ የእስራኤል ጋዜጦችን በማንበብ የሂብሩ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ጀመረ። ያሪ አረብኛ ቋንቋ መናገር ብችልም ሲንዋር እንድንነጋገር የሚፈልገው በሂብሩ ቋንቋ ነው ይላሉ።

“የሂብሩ ቋንቋ ችሎታውን ለማሳደግ ከማረሚያ ቤት ጠባቂዎች የተሻለ የሂብሩ ቋንቋ መናገር ከሚችል ሰው ጋር መነጋገር ስለፈልግ ይመስለኛል ከእኔ ጋር በሂብሩ ማውራትን የሚመርጠው።”

እአአ 2011 ላይ እስራኤል ጊላድ ሻሊት የተባለ ወታደሯን ለማስለቀቅ ስትል 1027 ፍልስጤማውያንን ከእስር ለመልቀቅ ከስምምነት ስትደርስ ሲንዋር ነጻ ሆነ።

ሻሊት በሲንዋር ወንድም እና በሌሎች ታግቶ ለአምስት ዓመታት ያህል በእገታ ከቆየ በኋላ ነበር በእስረኛ ለውውጥ የተለቀቀው።

ሲንዋር ከእስራኤል እስር ቤት ሲወጣ እስራኤል የጋዛ ሰርጥን ለቅቃ ወጥታ ሐማስ ተቀናቃኙ የነበረውን የያሲር አረፋት ፋታሃ ፓርቲን አስወግዶ ጋዛን የሚያስተዳደርበት ወቅት ነበር።

ተግባቢው እና የሚፈራው ሲንዋር

ሲንዋር ወደ ጋዛ እንደተመለሰ መሪ ሆነ። ሲንዋር የሐማስ መሥራች መሆኑ እና ረዥም ዓመታትን በእስር ቤት ማሳለፉ መሪ እንዲሆን መንገድ ጠርጎለታል።

ማይክል “ሰዎች ይፈሩት ነበር። ይህ ግለሰብ ሰዎችን በገዛ እጁ የገደለ ሰው ነው። በጣም ጨካኝ እንዲሁም ደግሞ በጣም ተግባቢ የሆነው ሰው” በማለት ለሲንዋር ሥልጣን ላይ መውጣት ሌላ ምክንያት ያስቀምጣሉ።

ሲንዋር እአአ 2013 ላይ በጋዛ የሐማስ ፖለቲካ ቢሮ አባል ሆኖ ተመረጠ። እአአ 2017 ላይ ደግሞ በጋዛ የሐማስ ኃላፊ ሆነ።

የሲንዋር ታናሽ ወንድም ሞሐመድ ልክ እንደ ታላቅ ወንድሙ በሐማስ ቁልፍ ሚና መጫወት ጀመረ። መሐመድ ከበርካታ የእስራኤል የግድያ ሙከራ መትረፉን ይገልጻል። እአአ 2014 ላይ ግን ሐማስ የመሐመድን ሞት ይፋ አደረገ።

የሲንዋር ታናሽ ወንድም መሐመድ ሲንዋር
የምስሉ መግለጫ,የሲንዋር ታናሽ ወንድም መሐመድ ሲንዋር

አንዳንዶች ግን የመሐመድን ሞትን ይጠራጠራሉ። አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ሪፖርቶች ሞሐመድ በጋዛ ባሉ ዋሻዎች ተደብቆ እንደሚገኝ እና በመስከረም 26ቱ ጥቃት ተሳታፊ ስለመሆኑ ጨምር አመልክተዋል።

የሲንዋር የጭካኔ ዝና ‘የኻን ዩኒስ ቡቸር’ [የኻን ዩኑሱ አራጀ] የሚል ቅጽል ስም አሰጥቶታል።

“የሐማስ አባላት የሲንዋርን ትዕዛዝ የማይቀበሉ ከሆነ ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደሆነ ያውቃሉ” ይላሉ ያሪ።

እአአ 2015 ላይ መሐሙድ አሸቲዊ የተባለ ከፍተኛ የሐማስ አዛዥ በማጭበርበር እና በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ከተወነጀለ በኋላ ስቃይ ደርሶበት እንዲገደል ትዕዛዝ የሰጠው ሲንዋር ስለመሆኑ ይገልጻል።

ሲንዋር እና ኢራን

በእስራኤል የመከላከያ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ በርካቶች በእስረኛ ልውውጥ ወቅት ሲንዋርን መልቀቅ ትልቅ ስህተት ነው ብለው ያምናሉ።

እአአ 2015 ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ሲንዋርን “ዓለም አቀፍ አሸባሪ” ሲል ፈርጆታል።

ግንቦት ወር 2021 ላይ የእስራኤል አየር ኃይል መኖሪያ ቤቱን እና መሥሪያ ቤቱን ደብድቦ ነበር። ሲንዋር ግን በቦታው አልነበረም።

ሲንዋር 2022 ላይ አደባባይ ወጥቶ ለፍልስጤማውያን በተቻላችሁ መንገድ ሁሉ እስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሙ ሲል መልዕክት አስተላለፈ።

ተንታኞች በሐማስ ፖለቲካዊ እና በወታደራዊው ክንፍ አልቃስም ብርጌድ መካከል ቁልፉ ሁነኛው ሰው ሲንዋር ነው ይላሉ።

ይህም ብቻ አይደለም የሱኒ አረብ ድርጅት የሆነው ሐማስ፤ የሺዓ አገር ከሆነችው ኢራን ጋር ግንኙነት እንዲያደረጅ ያደረገ ቁልፉ ሰው ሲንዋር ነው ይባላል።

ሲንዋር እአአ 2017 ላይ ግብፅ ድንበር አቅራቢያ
የምስሉ መግለጫ,ሲንዋር እአአ 2017 ላይ ግብፅ ድንበር አቅራቢያ

ሐማስ እና ኢራን አንድ ግብ አላቸው። ይህም እስራኤል የተባለች አገርን ማጥፋት እና ኢየሩሳሌምን ከእስራኤል የኃይል ይዞታ ስር ነጻ ማውጣት።

ሁለቱ አካላት ተመሳሳይ ዓላማቸውን ለማሳካት እጅ እና ጓንት ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል።

ኢራን በገንዘብ፣ በሥልጠና እና በቁስ ሐማስን ትደግፋለች። ሐማስ ደግሞ በየዕለቱ ሮኬት ወደ እስራኤል ያስወነጭፋል።

ሲንዋር 2021 ላይ በይፋ ለኢራን ምስጋናውን አቅርቦ ነበር። “ምስጋና ለኢራን ይሁን። ካለኢራን ድጋፍ የፍልስጤማውያን ትግል እዚህ ደረጃ ላይ ባልደረሰ ነበር” ሲል ተናግሯል።

እስራኤል ሲንዋርን ሳትገድል የምታርፍ አትመስልም።

በአውሮፓ ምክር ቤት የውጪ ጉዳዮች ከፍተኛ የፖሊሲ አጥኚ የሆኑት ሃግ ሎቫት ግን እስራኤል ሲንዋርን ብታስወግድ ለሚዲያ ፍጆት ካልዋለ በቀር በሐማስ እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጣው ለውጥ እምብዛም ነው ይላሉ።

እንደ ሐማስ ያሉ ድርጅቶች አንድ ኮማንደር ወይም መሪ ቢወገድ በሌላ ለመተካት ጊዜ አይወስድባቸውም። ምንም እንኳ ተተኪው እንደ ቀደመው መሪ ተመሳሳይ የሆነ ልምድ እና ተቀባይነት ይዞ ባይመጣም ድርጅቱን ወደፊት መውሰዱ ግን አይቀርም።

“እውነት ነው በሲንዋር ሞት ሐማስ ይጎዳል። ነገር ግን እርሱን በሌሎች መተካት የሚያስችል ቀድሞ የተዘረጋ አሠራር አለ” ይላሉ ሎቫት።

ተንታኞች የሚስማሙበት ዋናው ጥያቄ ግን እስራኤል አሁን እያካሄደች ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ ስታጠናቅቅ ጋዛ ምን ትሆናለች የሚለው ነው።

ጋዛን የሚያስተዳድረው ማን ይሆናል? ሐማስን ጨምሮ ጠላቶቿን ማስወገድ ትችላለች? ወይስ ወታደራዊው ዘመቻ የፈጠረው ስቃይ በእስራኤል ጥላቻ የበለጠ አደጋን ይዞ ይመጣል?