የኢንተርኔት መቋረጥ

17 ጥቅምት 2024, 07:07 EAT

በአፍሪካ የኢንተርኔት ነጻነት እየተሻሻለ ቢሆንም ኢትዮጵያ በግጭቶች እና በባለሥልጣናት እርምጃ ምክንያት በይነ መረብ ነጻ ያልሆነባት አገር መሆኗን ፍሪደም ሐውስ የተባለው የመብቶች ተቋም ያወጣው ሪፖርት አመለከተ።

ተቋሙ በአውሮፓውያኑ 2024 የዓለም የኢንተርኔት ነጻነትን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያን ጨምሮ አስራ ሰባት የአፍሪካ አገራትን የነጻነት ይዞታን ያጠና ሲሆን፣ በዚህም ኢትዮጵያ ዝቅተኛውን ነጥብ አስመዝጋባለች።

ጥናቱ ከአፍሪካ አገራት መካከል አንጎላ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሊቢያ፣ ማላዊ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌን የዳሰሰ ነው። በዚህም መሻሻሎች እንዳሉ የጠቀሰ ቢሆንም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ አገራት የበይነ መረብ ነጻነት ተሸርሽሯል ብሏል።

ጥናቱ የአገራቱን የኢንተርኔት ነጻነት ይዞታ በ100 ነጥቦች የመዘነ ሲሆን፣ ዝቅተኛውን ወይም “ነጻ ያልሆነ” የሚል ደረጃን ያገኘችው ኢትዮጵያ 27 ነጥቦችን አግኝታለች። ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ከፍተኛውን 74 ነጥብ በማግኘት የኢንተርኔት ነጻነት ያለባት አገር እንደሆነች ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ፍሪደም ሐውስ ካጠናቸው የአፍሪካ አገራት መካከል ሰባቱ እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት መሻሻሎችን ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ስድስቱ ግን በኢንተርኔት መብት ይዞታቸው ላይ ማሽቆልቆል መመዝገቡን ሪፖርቱ አመልክቷል።

በተለይ ግጭቶች ባሉባቸው አገራት ውስጥ የኢንተርኔት ነጻነት እክሎት እየገጠሙት መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ባለሥልጣናት በአገራቸው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ሰበብ በማድረግ የኢንተርኔት ግንኙነትን ያቋርጣሉ እንዲሁም የበይነ መረብ ጋዜጠኞችን ያሳድዳሉ ብሏል።

ኢንተርኔት የተጋረጠበት ስጋት

የኢንተርኔት ነጻነት መገደብ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስጊነቱ ጨምሯል።

ናይጄሪያ ሌጎስ ውስጥ 45 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝም የኢንተርኔት መስመር ተዘርግቷል። በባሕር ውስጥ ተጉዞ እስከ ከተማዋ ይደርሳል።

‘ቱ አፍሪካ’ የተባለው በባሕር ውስጥ የሚተላለፍ የኢንተርኔት መስመር ላለፉት አራት ዓመታት በቢሊዮን ዶላሮች ወጪ እየተዘረጋ ነው።

አውሮፓን፣ እስያን እና አፍሪካን ያስተሳስራል።

ይህ መስመር የተሻለ የኢንተርኔት ዝርጋታን የሚያረጋግጥ፣ የመረጃ ፍሰት ነጻነትን የሚያስጠብቅ እንዲሁም በ46 የተለያዩ መስመሮች ለ33 አገራት የሚደርስ ነው ተብሏል።

የተወሰኑ የመስመሩ ክፍሎች ቢሠሩም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት የሚጀምረው በቀጣይ ዓመት ነው። አሁን በአፍሪካ ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ በባሕር ወለል ላይ ከሚገኙት ኬብሎች በአጠቃላይ የሚበልጥ አገልግሎት ይሰጣል።

ሜታ፣ ቻይና ሞባይል እና ቮዳፎንን ጨምሮ ሌሎችም የቴክኖሎጂ ተቋማትን ያሳተፈ እንዲሁም ከፍተኛ ወጪ የፈሰሰበት ፕሮጀክት ነው።

‘ቱ አፍሪካ’ ከዓለም ሕዝብ 70 በመቶውን በኢንተርኔት ለማስተሳሰር ዕቅድ ይዟል።

ኢሜል ለመላክ፣ በበይረ መረብ ቪድዮ ለመመልከት እና ለሌሎችም አገልግሎቶች ከባሕር በታች የተዘረጉ መስመሮችን እንጠቀማለን።

አንዳንድ አገራት በቀላሉ ሊቋረጡ የሚችሉ ኬብሎች ላይ የተመሠረተ የኢንተርኔት መስመር ዝርጋታ አላቸው።

ቱአፍሪካ የተባለው በባሕር ውስጥ የሚተላለፍ የኢንተርኔት መስመር ላለፉት አራት ዓመታት በቢሊዮን ዶላሮች ወጪ እየተዘረጋ ነው።
የምስሉ መግለጫ,ቱአፍሪካ የተባለው በባሕር ውስጥ የሚተላለፍ የኢንተርኔት መስመር ላለፉት አራት ዓመታት በቢሊዮን ዶላሮች ወጪ እየተዘረጋ ነው።

ዓሣ ከማስገር ጋር በተያያዘ በሚያጋጥም ጉዳት፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በመሬት መንሸራተት እንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሆነ ተብሎ በሚፈፀም ጥቃት የኢንተርኔት አገልግሎት ሊቋረጥ ይችላል።

ዋነኛው ስጋት የሚመነጨው ግን ከመንግሥታት ነው።

‘ቶፕ10ቪፒኤን’ ባወጣው መረጃ መሠረት በአንድ አካባቢ ወይም አገር ውስጥ ኢንተርኔትን ማቋረጥ በአሁኑ ወቅት እየጨመረ መጥቷል።

ሜታ፣ ቻይና ሞባይል እና ቮዳፎንን ጨምሮ ሌሎችም የቴክኖሎጂ ተቋማትን ያሳተፈና ከፍተኛ ወጪ የፈሰሰበት ፕሮጀክት ነው።
የምስሉ መግለጫ,ሜታ፣ ቻይና ሞባይል እና ቮዳፎንን ጨምሮ ሌሎችም የቴክኖሎጂ ተቋማትን ያሳተፈና ከፍተኛ ወጪ የፈሰሰበት ፕሮጀክት ነው።

ፈተና ላይ ኩረጃን ለመከላከል ወይም የተቃውሞ ድምጽን ለማፈን በሚል ኢንተርኔት ከሚቋረጥባቸው አገራት መካከል ሕንድ በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።

በዚህ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያም የፈተና ኩረጃ እና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር በተደጋጋሚ ኢንተርኔት ማቋረጥ ከአፍሪካ ትጠቀሳለች።

ይህ በመንግሥታት የሚፈጸመው የኢንተርኔት አገለግሎትን የማቋረጥ ድርጊት በተወሰኑ አገራት ውስጥ ብቻ የሚያጋጥም ሳይሆን በርካቶች እንደፈለጉ የሚፈጽሙት እየሆነ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2019 እስከ 2023 ባሉት አምስት ዓመታት ኢንተርኔትን መዝጋት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መጥቷል።

በሕንድ ኢንተርኔት ማግኘት የሕዝብ መብት ሳይሆን የመንግሥት መገልገያ መሣሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።

ኢንተርኔት መዝጋት እየተባባሰ ከመምጣቱ አንጻር የተባበሩት መንግሥታት ኢንተርኔት ማግኘትን “ቅንጦት ሳይሆን የሰብአዊ መብት አካል” አድርጎ ሊፈርጅ እንደሆነ አስታውቋል።

በድረ ገጾች ላይ የሚደረግ ሳንሱርም እየጨመረ መጥቷል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የኢንተርኔት ነጻነት እየቀነሰ ይገኛል።

‘ፍሪደም ሐውስ’ የተባለው የመብት ተከታታይ ተቋም የሠራው ጥናት አገራትን በሳንሱር፣ በስለላ እና የኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት ከፋፍሎ ያስቀምጣል።

አጥኚዎች እንደሚሉት የኢንተርኔት ነጻነት ለ13 ተከታታይ ዓመታት ቀንሷል።

በቅርቡ የኢንተርኔት ነጻነት ከቀነሰባቸው አገራት መካከል ኢራን እና ሚያንማር ይገኙበታል።

ቻይና በበይነ መረብ እንቅስቃሴ ማነስ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ለምን ኢንተርኔት ይቋረጣል?

ኢንተርኔትን ለመዝጋት የሚውሉ መተግበሪያዎች እየተበራከቱ መሄድ እና መንግሥታት እነዚህን መተግበሪያዎች ለመጠቀም ያላቸው ፈቃደኛነት መጨመር እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል።

በናሽናል ዲፌንስ ዩኒቨርስቲ የጥናት ባለሙያ የሆኑት ጃኪ ኪር እንደሚሉት፣ ኢንተርኔት ከመንግሥታት ይዞታ ውጪ ያለ ዓለም አቀፍ መድረክ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

“ይሄ አስተሳሰብ ግን የምኞች ዓለም ነበር” ይላሉ ባለሙያዋ።

ይህ አስተሳሰብ የመጣው ኢንተርኔት እንዴት እንደሚሠራ በአግባቡ ካለመገንዘብ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን በአንድ ወቅት እንዳሉት ሰዎች ኢንተርኔት የሚጠቀሙበትን መንገድ መቆጣጠር “ተንቀሳቃሽ ነገርን ግድግዳ ላይ ለማቆም እንደመሞከር ነው።”

“መንግሥታት በይነ መረብን የሚቆጣጠሩበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም ነበር” ሲሉ ባለሙያዋ ያብራራሉ።

ኢንተርኔትን በመቆጣጠር ቻይናን የቀደማት የለም። ከፍተኛ ወጪ በማፍሰስ ሊታለፉ የማይችሉ ሶፍትዌሮች እና ሀርድዌሮች ተገንብተዋል።

ኢንተርኔትን ለመቆጣጠር ሰዎች በበይነ መረብ የሚመለከቱትን እና የሚያጋሩትን መከታተልም ጀምራለች።

ሌሎች አገራትም ቻይናን ተከተሉ።

ሩሲያ ባለፉት አራት ዓመታት በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ ኢንተርኔትን ከዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ትስስር የሚቆርጥ መተግበሪያ እየገነባች ነው።

ከዩክሬን ወረራ በኋላ በኢንተርኔት ነጻነት ሁለት ደረጃ ወደታች ወርዳለች።

‘አክሰስ ናው’ ለተባለው የመረጃ ተደራሽነት መበት ተቆርቋሪ ተቋም የሚሠሩት ማርዋ ፋታፍታ “ዲጂታል አምባገነንነት እየተስፋፋ ነው” ይላሉ።

ቱአፍሪካ ኢንተርኔት

‘ቱ አፍሪካ’ ኢንተርኔት ተደራሽ ከሚያደርግባቸው አገሮች መካከል ሳዑዲ አረቢያ ትገኝበታለች።

የመስመር ዝርጋተው ሪያድ የደረሰው ከወራት በፊት ነው። በሳዑዲ የተቃውሞ ድምጾችን ማፈን ወይም መቅጣት የተለመደ ነው። ከመንግሥት ጋር ስምምነት የፈረሙ ተቋሞች በሳዑዲ ግዛት ውስጥ መሥራት እንዳለባቸው የሚወስን ሕግ አለ።

ተመሳሳይ ሕጎች በቱርክ፣ በዮርዳኖስ፣ በሕንድ እና በጀርመንም ተደንግገዋል።

ይህ ማለት የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በሕግ ተገደው ወይም ለፖለቲካ ሲሉ በሳንሱር ውስጥ ሊሳተፉ ይችላሉ።

“ይህ አስጊ ነው ብዬ አምናለሁ” የሚሉት ባለሙያዋ፣ ተመሳሳይ የኢንተርኔት ገደቦች በመላው ዓለም እየተባባሱ እንደሚሄዱ ያስጠነቀቅቃሉ።

ቻይናን በመከተል አንዳንድ አገራት የምዕራባውያንን የኢንተርኔት ዝርጋታ ለመገዳደር ይሞክራሉ።

ሩሲያ አገር በቀል መተግበሪያዎች እንዲበለጽጉ የምትደግፈውም ለዚህ ነው።

‘ያንዴክስ’ የተሠራው ጉግልን ለማስቀረት ‘ሲጆን ቪኬ’ እያደረገ ፌስሱክ እየቀነሰ፣ ‘ሩቲዩብ’ ደግሞ ዩቲዩብን እየተኩ መጥተዋል።

ሕንድም በቻይና የተሠሩ መተግበሪያዎችን እያገደች ነው። በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።

አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት የኢንተርኔት ነጻነትን ለመጠበቅ ይሞክራሉ። አሜሪካ ደግሞ ቲክቶክን ለማገድ ወስናለች።

እንደ ‘ቴሙ’ እና ‘ሼይን’ ያሉ የቻይና መገበያያ መተግበሪያዎች ዕጣ ፈንታም ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል።

ዓለምን ወደ አንድ እያመጣ የነበረው ኢንተርኔት ከመቼውም በላይ በዓለም መካከል ክፍተት እየፈጠረ ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።