October 17, 2024 

” የቅልጥ ዓለቱ እንቅስቀሴ እስከቀጠለ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል አለው ” – ኤልያስ ሌዊ (ዶ/ር)

በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት አከባቢ በ ‘አዋሽ ፈንታሌ’ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል።

ንዝረቱ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰምቷል፡፡

ትናንት ምሽት የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት መሰማቱ ይታወሳል።

አሁንም ዳግም የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ መከሰቱ ታውቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃል፥ ” ከቀኑ 6 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ9 ሰኮንድ በአዋሽ ፈንታሌ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ ነው ” ብለዋል።

የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው ባለፈው በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ሲሆን በአካባቢው ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴ አሁንም እንዳልቆመ ተናግረዋል።

” አሁን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የንዝረት መጠኑ አነስተኛ ነው ” ሲሉ ገልጸው ” በአዋሽ ፈንታሌ እና ሳቡሬ ከተማ መካከል ላይ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ እስከቀጠለ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል አለው ”  በማለት ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ አስረድተዋል።