October 17, 2024

” ታፍኖ ከተወሰደ ከ5 ቀናት በኋላ ተገድሎ አስክሬኑ ወንዝ ተጥሎ ተገኝቷል ” – የትግራይ ነፃነት ፓርቲ

የትግራይ ነፃነት ፓርቲ የአመራር አባሉ ታፍኖ ከተወሰደ በኃላ ተገድሎ አስከሬኑ ወንዝ ተጥሎ እንደተገኘ ገለፀ።

ፓርቲው ታፍኖ የተወሰደውን የአመራር አባሉን ላለፉት ከ5 ቀናት ሲፈልግ የቆየ ቢሆን ተገድሎ አስክሬኑ ወንዝ ተጥሎ ማግኘቱ አሳውቋል።

የፓርቲው ሊቀ-መንበር ዶ/ር ደጀን መዝገበ ” አሰቃቂ ድርጊቱ የተፈፀመው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ ነው ” ብለዋል።

ተገድሎ የተገኘው የፓርቲው አመራር አባል በወረዳው የፓርቲው አስተባባሪ መሆኑን ገልጸው ፥ ” ታፍኖ ከተወሰደ ከ5 ቀናት በኋላ ተገድሎ ሬሳው በወንዝ ተጥሎ ተገኝቷል ይህ ጭካኔ የተሞላበት አረመንያዊ ድርጊት ነው ” ሲሉ አውግዘውታል።

ሊቀ-መንበሩ በዞኑ የሚገኙ አባላቱ ” ‘ ፓርቲው መደገፍ ህወሓት መቃወም አቁሙ አለበለዚያ ትገደላላችሁ ‘ የሚል ማስፈራርያ ደርሶዋቸዋል ” ሲሉ ‘ ህወሓትን ክሰዋል።

ህወሓት ለቀረበበት ክስ እስካሁን የሰጠው መልስ የለም።

” ተግባሩን የህወሓት አባላት ነው እየፈፀሙ የሚገኙት ” በማለት ያቀረቡትን ክስ ያጠነከሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ” በ19 የፓርቲው አባላት አፈና ፣ ደብደባና ግድያ ደርሷል ” ማለታቸው ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ዘግቧል።